Sunday, 04 March 2018 00:00

“ለ40/60 ቤቶች አልሙኒየም አቅርቦት የወጣ ጨረታ ቅሬታ አስነስቷል” ለሚለው ዘገባ ተሰጠ ማስተባበያ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ኩባንያችን መንግስት የገቢ ምርትን ለመተካት በሰጠው ትኩረት መሰረት፤ በአገሪቱ ቀዳሚውን የአልሙኒየም ማምረቻ ፋብሪካ በመገንባት ከ600 በላይ ለሚሆኑ ቋሚና ለበርካታ ሰራተኞች የስራ እድል በመፍጠር፣ የተለያዩ በሀገር ውስጥ የሚገኙ የአልሙኒየም ተረፈ ምርቶች መልሶ በማቅለጥ ጥራታቸውን የጠበቁ የአልሙኒየም ፕሮፋይሎች በማምረት፣ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ በማቅረብ የገቢ ምርትን በመተካት ትልቅ ድርሻ እየተወጣ ያለ ሀገር በቀል ተቋም ነው፡፡
ሆኖም ጋዜጣችሁ የካቲት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ባወጣው እትም፤ ለ40/60 ቤቶች አልሙኒየም አቅርቦት የወጣው ጨረታ ቅሬታ እንዳስነሳ ባወጣው ዘገባ ላይ “የጨረታው መስፈርት አንድን ድርጅት ታሳቢ ያደረገ ነው” የሚለው ሀሰተኛ መሆኑን ልንገልፅ እንወዳለን፡፡
በዘገባው ላይ አንድን ድርጅት ታሳቢ ያደረገ ነው የሚል ስም ባይጠቅስም ጉዳዩ ቀጥታ ኩባንያችንን “B&C Aluminum PLC” ለማለት እንደሆነ ግልፅ ነው፣
ቅሬታ አቅራቢዎቹ አንድን ድርጅት የወገነና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያላገናዘበና በአጠቃላይ ሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶችን ከጨዋታ ውጪ የሚያደርግ ነው፤ ጨረታው የአልሙኒየም ከምችትና ከኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች የተሰጠ የብቃት ማረጋገጫ እንዲያቀርብ መጠየቁ የተጠቀሰው ሀሰት መሆኑን እየገለፅን፤ የጨረታ ሰነዱ ላይ የተዘጋጀው መስፈርት ለማናቸውም በአልሙኒየም ዘርፍ ለተሰማሩ ድርጅቶች የሚሆንና ሁሉም ድርጅቶች የአልሙኒየም ናሙና ለፍተሻ ለኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት በማስገባት ደረሰኙን ብቻ ለአማራጩ ድርጅት እንዲያስገቡ ተጠይቋል፡፡ የውጪ ምንዛሬን በተመለከተ የጨረታ ሰነዱ ላይ የተገለፀ ነገር ባይኖርም፣ ኩባንያችን በሀገር ውስጥ በሚያመርተው ምርት አማካኝነት የሀገራችንን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል የበኩሉን ሚና መጫወቱ ከሚያስመሰግነው በቀር የቅሬታ ነጥብ ሊሆን አይገባም፤
“ታሳቢ የተደረገው ድርጅት ከውጪ በሚመጣ አልሙኒየም ተረፈ ምርት ሪሳይክል እያደረገ የሚያመርት ነው” ተብሎ የተገለፀው ሀሰተኛ መሆኑን እየገለፅን ኩባንያችን ምርቱን የሚያመርተው የተለያዩ ሀገር ውስጥ የሚገኙ የአልሙኒየም ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም እንደሆነ እንጠቁማለን፣
ከአምስት አመታት በፊት በክራውን እና በሰንጋ ተራ ለተገነቡ ቤቶች ተመሳሳይ የ1 ቢሊየን ብር ጨረታ መውጣቱንና ይኸው የተባለው ድርጅት አሸንፎ በጊዜው እንዳላጠናቀቀ ተገልጿል፡፡ ኩባንያችን በወቅቱ ከጨረታ እንዲወጣ የተደረገበት ሁኔታ የነበረ ሲሆን ሆኖም ለፌደራል የስነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ክስ በራሳችን ትግል በጨረታው ተሳትፈን ያገኘነው ፕሮጀክት ሲሆን የተጠቀሰው የገንዘብ መጠንም በፍፁም ከእውነት የራቀና ኩባንያችንም ስራውን እንዳላዘገየ እንገልፃለን፣
ቅሬታ አነሱ የተባሉ ግለሰቦች አንድ ጠንካራ የሚባል ድርጅት በቀን ከ30 ካ.ሜ በላይ መስራት እንደማይችል የተገለፀው በፍፁም ስህተትና የአፈፃፀም መጠን በኩባንያው የስራ ልምድ፤ የሰው ሀይል፤ የአመራር ብቃት፤ የማሽነሪዎች መኖርና በተለያዩ ነገሮች የሚወሰን ይሆናል፣
እንደሚታወቀው፤ የጨረታ ዋጋቸው የሚታወቁ የቴክኒካል ሰነድ ተገምግሞ ካበቃ በኋላ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በዚህ የጨረታ ሂደት ገና የቴክኒክ ግምገማው ያልተጠናቀቀ ስለሆነ ቅሬታ አቀረቡ የተባሉት ሰዎች የጠቀሱት የገንዘብ መጠን በተራ ግምት ላይ የተመሰረተ እንጂ በማስረጃ የተደገፈ አይደለም፣
በአጠቃላይ ኩባንያችን ህግን ተከትሎ የገቢ ምርትን ለመተካት በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ ያለ ተቋምና ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪን በማዳን ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ እያደረገ ያለ ተቋም ሲሆን ከላይ የተዘረዘሩት ሙሉ በሙሉ የኩባንያችንን ስም የማጥፋት ዘመቻ መሆኑን ልንገልፅ እንወዳለን፡፡
ከ B&C Aluminum PLC

Read 4901 times