Saturday, 28 April 2012 13:11

በበቆጂ ላይ ጥናታዊ ፊልም ተሠራ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ታላላቅ የኦሎምፒክ ጀግኖችን ባፈራችውና ኑሮን ለማሸነፍ ሁሉም ይሮጥባታል በተባለችው ትንሿ የገጠር ከተማ  በቆጂ፤  ደረጃውን የጠበቀ ጥናታዊ ፊልም እንደተሰራ ተገለፀ፡፡ በቆጂ ባለፉት 20 ዓመታት ስምንት የኦሎምፒክ፤ 32 የዓለም ሻምፒዮና ሜዳልያዎች እንዲሁም ከ10 በላይ የዓለም አትሌቲክስ ሪኮርዶችን ያስመዘገቡ ምርጥ አትሌቶችን አፍርታለች፡፡ ሰሞኑን በኒውዮርክ መካሄድ በጀመረው  በታዋቂው የትሬቤካ ፊልም ፌስቲቫል ላይ የተመረቀው የ100 ደቂቃው ጥናታዊ ፊልም “ታውን ኦፍ ራነርስ” ይሰኛል፡፡ ለቀረፃ አራት ዓመታትን የወሰደውን ይሄን ፊልም ዲያሬክት  ያደረገው ጄሪ ሮዝዌል የተባለ እንግሊዛዊ የፊልም ባለሙያ ነው፡፡   በሜት ፊልም አካዳሚ በፕሮዲውሰርነት እየተማረ የሚገኘው ዳን ደምሴ የፊልም ሥራውን ሃሳብ እንዳፈለቀ የተገለፀ ሲሆን፤ ሜት ፊልም ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር በትብብር እንደተሰራ ኦፊሴላዊ መግለጫው አመልክቷል፡፡ ፊልሙ በእንግሊዝ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች ይታያል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከፊልሙ ዕይታ በኋላ ለበቆጂ የአትሌቲክስ ክለቦች መጠነ ሰፊ የትብብር ግንኙነቶች ከተለያዩ የእንግሊዝ አትሌቲክስ ክለቦች ጋር መፍጠር እንደማያስችል ተጠቁሟል፡፡

አንዳንድ ዘገባዎች ፊልሙ ስለ በቆጂ የአትሌቶች መፍለቂያነት ጠለቅ ያሉ ትንተናዎች ቢኖረውም ወጣት አትሌቶች ህልማቸውን ለማሳካት በሚገጥማቸው ፈተና እና ውጣ ውረድ ላይ ጠንከር ያለ አቋም አላንፀባረቀም ብለዋል፡፡ የሯጭ ሴት ልጅ አባት የሆነውና በኬንያ ማእከል በስራ የቆየው የፊልሙ ዲያሬክተር ጄሪ ሮዝዌል፤ ተመሳሳይ ደረጃ ያለው ጥናታዊ ፊልም ሲሰራ “ታውን ኦፍ ራነርስ” አራተኛው እንደሆነ ታውቋል፡፡

በቆጂ ያፈራቻቸው አትሌት ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ ከ4ዓመት በፊት በቤጂንግ ኦሎምፒክ በ5ሺ እና በ10ሺ የድርብ ወርቅ ሜዳልያዎች ማጥለቃቸውን በሚያሳይ ትእይንት የሚጀመርው ፊልሙ፤ ሶስት የበቆጂ  ወጣት አትሌቶች የእነሱን ዱካ ለመከተል የሚያደርጉትን ጥረት ይተርካል፡፡ የኦሎምፒክ ተስፈኞች በሆኑት ሃዊ እና አለሚ የተባሉ ወጣት አትሌቶች ላይ ትኩረት ያደረገው ፊልሙ፤ የአፍሪካ ወጣቶች ህልማቸውን እውን ለማድረግ የሚከፍሉትን መስእዋትነት ያሳያል፡፡ በፊልሙ ላይ ምርጥ አትሌቶችን ፈልፍሎ በማውጣት የ30 ዓመታት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የአትሌቲክስ አሰልጣኝ እና አስተማሪ የሆኑት አቶ ስንታየሁ እሸቱ ከዋና ገፀባህርያቱ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የ54 ዓመቱ አቶ ስንታየሁ እሸቱ፤ በትልልቆቹ የዓለም እውቅ አትሌቶች ፋጡማ ሮባ፤ ደራርቱ ቱሉ፤ቀነኒሳ በቀለና  ጥሩነሽ ዲባባ የስኬት ጅማሮ ላይ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሲሆን በአሁኑ ግዜ እድሜያቸው ከ10 ዓመት ጀምሮ የሆኑ 200 ታዳጊ ሯጮችን በበቆጂ እያሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡  ለፊልሙ ማጀቢያ ሙዚቃዎችን የሰሩት የኢትዮ ጃዝ ፈጣሪው ሙላቱ አስታጥቄ፤ እማሆይ ፅጌ ማርያም ገብሩ እና የእንግሊዙ አቀናባሪ ቪንሰንት ዋትስ ናቸው፡፡ በ170 ማይል ርቀት ላይ የምትገኘው በቆጂ ከተማ የአየሯ አለመበከል፤ በገላጣ ሜዳ በኮረብታማ እና ለሩጫ በሚያመቹ መሬቶቿ ለአትሌቲክስ ስፖርት የተመቸች ከተማ መሃኗን በተመለከተ የተካሄዱ ምርምሮችን ያካተተው “ዘ ታውን ኦፍ ራነርስ” ወጣትና ታዳጊ አትሌቶች በስፖርት ስኬታማ ሆነው የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን ህይወት ለመለወጥ የሚያደርጉትን እልህ አስጨራሽ ጥረትም የሚዳስስ ነው፡፡ ሰሞኑን በእንግሊዝና አየርላንድ በሚገኙ ሲኒማ ቤቶች መታየት የጀመረው ፊልሙ፤ በሁለቱ አገር ሚዲያዎች የአድናቆት ዳሰሳ ተችሮታል፡፡ “ሩቅ አሳቢ እና ማራኪ ልምድ የሚገኝበት ፊልም” በሚል የፃፈው “ፋይናንሻል ታይምስ” ሲሆን “በሁሉም ደረጃዎች መሳጭ” በሚል የገለፀው ደግሞ “አፍሪካን ቻናል” ነው፡፡  “አራይዝ ማጋዚን” በበኩሉ፤ አስቂኝ እና ማራኪ  እንዲሁም ስሜት ቀስቃሽ እና መሳጭ ሃሳብ የያዘ ሲል አወድሶታል፡፡ “በኦሎምፒክ ዓመት የሚጠበቅ ሞራልን የሚያነቃቃ ልዩ ማስታወሻ” በሚል ያደነቀው ደግሞ “ዘጋርድያን” ነው፡፡

 

 

Read 1346 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 13:14