Print this page
Sunday, 04 March 2018 00:00

ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር አልታወቀም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

 ባሣለፍነው ሣምንት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የኢህአዴግ ሊቀ መንበርነት ምርጫ ላልተወሠነ ጊዜ መራዘሙን ምንጮች ለአዲስ አድማስ የጠቆሙ ሲሆን አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ ስልጣን እንደሚለቁ መግለፃቸውን ተከትሎ ግምገማ ሲያካሂዱ የሰነበቱት ደኢህዴን፣ ኦህዴድ እና ብአዴን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው የመመረጥ እኩል ዕድል እንዳላቸው ታውቋል፡፡
ህውኃት ለሊቀመንበርነት የመወዳደር ተመሳሳይ እድል ቢኖረውም እስካሁን ለመወዳደር ፍላጎት አለማሳየቱን የጠቆሙት ምንጮች፤ የኦህዴድ ሊቀ መንበር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም የደኢህዴን ሊቀመንበር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
36 አባላት ያሉት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ረቡዕ የካቲት 21 እና ሐሙስ የካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም ተሠብስቦ በአቶ ሃይለማርያም መልቀቂያ እና በተተኪው የግንባሩ ሊቀ መንበር ጉዳይ ላይ ይወያያል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ስብሠባው ላልተወሠነ ጊዜ መራዘሙን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
ምናልባት ከፊታችን ሠኞ በኋላ ስራ አስፈፃሚው ሊሠበሠብ ይችላል ያሉት ምንጮች፤ በመቀጠልም 180 አባላት (በአሁኑ ወቅት 175 ናቸው) ያሉት የኢህአዴግ ምክር ቤት የግንባሩን ሊቀ መንበር እንደሚመርጥ ጠቁመዋል፡፡ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንነትም በቀጣዩ ሣምንት ሊታወቅ እንደሚችል ለግንባሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልፀዋል፡፡
አቶ ኃይለማርያም ስልጣን እንደሚለቁ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ አስፈላጊውን የህግ ሂደት ለማሟላት አፋጣኝ የሹመት ሽግሽግ ያደረገው ኦህዴድ፤ አቶ ለማ መገርሣን በዶ/ር አብይ አህመድ በመተካት ለኢህአዴግ ሊቀመንበርነት ያዘጋጃቸው ሲሆን ብዙዎችም የኦህዴዱ አዲስ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው እንደሚመረጡም ገምተዋል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ሃይለማርያምን በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ የተካው ደኢህዴንም ሆነ አቶ ደመቀ መኮንን በሊቀመንበርነታቸው እንዲቀጥሉ የወሠነው ብአዴን ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የብአዴን መስራችና አመራር የሆኑት አቶ በረከት ስምኦን በጉዳዩ ላይ ለኢቢሲ በሠጡት መግለጫ፣ ለግንባሩ ሊቀመንበርነት የሚቀርቡ እጩዎች በ180ዎቹ የኢህአዴግ ም/ቤት አባላት በሚስጥር በሚሰጥ ድምፅ እንደሚለዩ አስታውቀዋል፡፡
በኢህአዴግ ም/ቤት ውስጥ በአሁኑ ወቅት ኦህዴድ 45፣ ደኢህዴን 45፣ ብአዴን 45 አባላት ሲኖራቸው ህወኃት በቅርቡ አምስቱን በማገዱ አሁን ያሉት 40 ናቸው፡፡ ለሊቀመንበርነት በሚደረገው ምርጫ ላይም በተለይ ህወኃት እስካሁን ለመወዳደር ፍላጎት አለማሣየቱን ተከትሎ፣ አባላቱ የሚሠጡት ድምፅ የሶስቱን ድርጅቶች እጩዎች ለመለየት ወሣኝ መሆኑን ለግንባሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
አለማቀፍ ተቋማትና የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትርነት ምርጫው ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እየመከሩ ነው፡፡
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ መልቀቃቸው ለሃገሪቱ ፖለቲካዊ መሻሻል ጠቃሚ መሆኑን የገለፀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ያለመምረጥ ጥረት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል።
ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፊት ለፊቱ ከባድ ኃላፊነት ይጠብቀዋል ያለው የአልጀዚራ ዘገባ፤ ኢትዮጵያውያን አሁን እያነሷቸው ካሉ ጥያቄዎች አንፃር፣ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም ብቻውን መሠረታዊ ለውጥ አያመጣም በማለት ሁሉንም ያሣተፈ የፖለቲካ ለውጥና ተሃድሶ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል፡፡
የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን አነጋግሮ በጉዳዩ ላይ ሠፊ ዘገባ ያጠናቀረው አልጀዚራ፤ አቶ ኃይለማሪያምን የሚተካውን ሰው የመምረጥ ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ያነጋገራቸው ምሁራን ማሳሰባቸውን አመልክቷል፡፡
ነዋሪነታቸውን በአሜሪካን ያደረጉትና በኢትዮጵያ ጉዳይ ፖለቲካዊ ትንታኔ በማቅረብ የሚታወቁት ሃሠን ሁሴን፤ በኦሮሚያ ያለውን ጥያቄ ከማስታገስ አንፃር የኦህዴድ ተወካይን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሾም የተሻለ አማራጭ መሆኑን ለአልጀዚራ ተናግረዋል፡፡
በጆርጅ ማሰን ዩኒቨርስቲ የግጭትና መፍትሄ ትንተና ተቋም ፕሮፌሰር የሆኑት ትሬስ ሊዮንስ በበኩላቸው፤ በኦሮሚያ ያለውን ተቃውሞ ለማረጋጋት የክልሉ ተወካይ ሃገሪቱን እንዲመራ ቢደረግ የተሻለ ይሆናል ብለዋል፡፡ አክለውም፤ በቀጣይ የሚመረጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ማንነት የሃገሪቱን ፖለቲካ ቀጣይ እጣ ፋንታ በፅኑ የሚወስን ነው ሲሉ ለአልጀዚራ ተናግረዋል፡፡
አስቸኳይ ስብሰባዎችን አካሂደው ሹም ሽር ያደረጉት ኦህዴድ፣ ብአዴን እና ደኢህዴን በበኩላቸው፤ የየራሳቸውን የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡
ብአዴን በአስቸኳይ ስብሰባው በተካሄደው ግምገማ፤ የአመራሩን የአስተሳሰብ አንድነት የበለጠ ማስጠበቁን የገለፀ ሲሆን በተለይ የወጣቶችን ችግር ለመፍታት ፈጣንና ተጨባጭ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ለሚዲያዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ያለው ብአዴን፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎችም ነፃ ምህዳር ለመፍጠር በትጋት እንደሚሰራ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ባለፉት አመታት ወጣቶችንና ምሁራንን የለውጥ ኃይል ማድረግ አለመቻሉንም ሊቀ መንበሩ አቶ ደመቀ መኮንን በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል፡፡
በኦህዴድ የስብሰባ ማጠቃለያ ላይ መግለጫ የሰጡት ም/ሊቀ መንበሩ አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፤ “ከአሁን በኋላ የምናካሂደው ጠንካራ ትግል ነው” ብለዋል። በድርጅቱ መግለጫ ላይም ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ተመልክቷል፡፡
ደኢህዴን በበኩሉ፤ “ዲሞክራሲ ለሀገራችን የህልውና ጉዳይ ነው፣ መሄድ በሚገባን ደረጃ አለመሄዳችንን ተገንዝቤያለሁ” ብሏል፡፡ የዲሞክራሲ ተቋማት፣ መገናኛ ብዙኃንና የሲቪክ ማህበራትን ከማበረታታትና ከመደገፍ ይልቅ አደናቃፊ ሁኔታዎች ነበሩ ሲልም የገመገመው ድርጅቱ፤ ይህን ሁኔታ ለመቀየርም ድርጅቱ ዝግጅት ማድረጉን በመግለጫው አትቷል፡፡

Read 11634 times Last modified on Saturday, 03 March 2018 13:05