Sunday, 04 March 2018 00:00

አውራ ዶሮ፤ በሰው ስጥ ሚስቱን ይጋብዛል!

Written by 
Rate this item
(16 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ነብሰ ገዳይ፣ ከአንድ ሟች ጋር ይጨቃጨቃል፡፡ በቀላል ጉዳይ ነው ጭቅጭቃቸው!
ገዳይ - “ሰማይ ከጠቆረ ይዘንባል” ይላል፡፡
ሟች - “ዳመና - ግላጭ ሲሆን ነው የሚዘንበው፡፡ ይሄ የውሸት ጥቁረት ነው” ይላል፡፡
ገዳይ - “የለም ይሄ የውሸት ጥቁረት አይደለም፡፡ እኔ አያቴ የነገሩኝ፤ ጥቁር ዳመና ስታይ በጊዜ ተሰብሰብ፡፡ ምክኒያቱም አንተም ጥቁር ስለሆንክ ቁጠኛ ነህ - ትዘንባለህ!”
ሟች - አያትህ፤ ዝም ብለው የልጃቸው ልጅ ስለሆንክ ሲያሞካሹህ ነው!
ገዳይ - “አንተ ማን ነህና ነው፣ ለአያቴ እንዲህ ያለ ግምት የምትገምተው? የት ታውቃቸዋለህ? ደደብ” ይላል፡፡
ሟች - “ደደብስ አንተ! ከስንት ዘመን በፊት ያረፉ አያትህን ንግግር ለዛሬ ይሰራል ብለህ ያሰብክ!”
ገዳይ - “ለዚህ ድፍረትህ ደህና ዋጋ ያስፈልግሃል - አንድ ጥይት!” ብሎ ሽጉጥ አውጥቶ፣ ግንባሩን ይለዋል፡፡
ሟች - ድፍት ይላል፡፡
የጥይቱን ጩኸት የሰማ አንድ ባላገር፣ ወደ ቦታው ሲመጣ፣ ሟችንና ገዳይን ያያል፡፡
ፖሊስ መጣ፡፡ ገዳይን ያዘው፡፡ ባላገሩን በምስክርነት ጠራው፡፡ ችሎት ፊት፣ ዳኛ ለምስክሩ ጥያቄ ያቀርባሉ፡-
“ያየኸውን ተናገር!”
ምስክር - “ሁኔታው ሲፈፀም ባቅራቢያው ነበርኩ”
ዳኛ - “ከዚያስ?”
ምስክር - “የጥይት ጩኸት ወደተሰማበት ሄድኩ፡፡ ሟች ግንባሩን ተመቶ ተዘርሯል፡፡ ገዳይ ባካባቢው በግዳይ ጥያለሁ መንፈስ ይንጎራደዳል! ገዳይ መሆኑ ያስታውቃል!”
ዳኛ - “ግን ተኩሶ ሲገድለው በዐይንህ በብረቱ አይተሃል?”
ምስክር ዝም ይላል፡፡
ዳኛ - “ስለዚህ ተኩስ ሰማህ እንጂ ሲተኩስና ሲመታው አላየህም፡፡”
ምስክር - “አዎን አላየሁም”
ዳኛ - “እንግዲያው ለምስክርነት አትበቃም!”
ምስክር፤ ከችሎቱ ወጥቶ ባለው ረዥም ኮሪደር እየሄደ፤
“አይ ዳኛ! አይ ፍርድ!” እያለ ሳቁን ይለቀዋል፡፡
ዳኛው ለህግ አስከባሪው፤ “አምጣልኝ ይሄን አጋሠሥ! ፍርድ ቤቱን ደፍሯል!”
ተጠርቶ ተመለሰ!
ምስክር - “ደሞ ለምን ተጠራሁ?”
ዳኛ - “ፍርድ ቤቱን በመድፈር ስለተከሰስክ ነው”
ምስክር - “ምን አድርጌ?”
ዳኛ - “በፍርድ በቱ በመሳለቅ ስለሳቅህ ነው!”
ምስክር - “ይሄን በምን አወቁ፤ ጌታዬ?”
ዳኛ - “እኔ ራሴ ሰምቼሃለሁ!”
ምስክር - “ስስቅ አይተዋል?”
ዳኛ - “አላየሁም”
ምስክር - “እንግዲያው እርሶም ለምስክርነት አይበቁም!”
ዳኛው አፈሩና አሰናበቱት!!
*      *     *
ሁኔታዎች ለፍርድ ሳይመቹ ሲቀሩ በራስ ላይ እንደ መተኮስ ያለ አደገኛ ችግር ውስጥ ይከትታሉ - ፈረንጆቹ እንደሚሉት፤
ቡመራንግ (boomerang) ይፈጠራል! አትፍረድ ይፈረድብሃል እንደተባለው ነው! ምንጊዜም፣ በተለይ አመራር ላይ ሆነን፣ የምንሰራቸው ስህተቶች፣ ከማንኛውም ዜጋ፣ ከፍ ባለ ደረጃ ተጠያቂዎች ያደርጉናል፡፡ ይህም በመሠረቱ የህሊና ተጠያቂነትን መደላድል ያደረገ ጠንካራ ዕውነታ ነው፡፡ በሥልጣን ላይ እያለን የምንሠራው ደግ ነገር፣ የስኬታችን ቁልፍ በመሆን እንደሚያስመሰግን ሁሉ፤ የምንሠራው መጥፎ ነገርም እንደ ጥቁር ጥላ በሄድንበት ቦታ ሁሉ እየተከተለ፣ የህሊና-ውጋት (guilt) እንደሚሆንብን አንርሳ! በሥልጣን ላይ ስንሆን ወደ እኛ የሚጠቁሙ ስህተት ፈላጊ ጣቶች አያሌ ናቸው፡፡ Fault-finder society እንደሚሉት ነው፡፡ ስለዚህም ራሳችንን ነጭ ወረቀት ላይ እንዳለ ነጥብ ቆጥረን፣ ከህዝብ ዐይን መሠወር እንደማንችል እናስብ! ያለፈው መንግሥት፤ “ከሠፊው ህዝብ እሰወራለሁ ብሎ ማሰብ፣ ግመል ሠርቆ እንደ ማጎንበስ ነው” ይል ነበር፡፡ አሊያም እንደ ሰጎኗ አልታየሁም ብሎ አንገትን አሸዋ ውስጥ መቅበር ይሆናል፡፡
አንድ ህዝብን ለመምራት ሥልጣን የያዘ ሹም፤ ከሁሉም በላይ ወቃሽና ከሳሹ ህሊናው ነው። ቀጣዩ ወቃሽና ከሳሽ የታሪክ መዝገብ ነው፡፡ ይህንን አስምሮ የማይጓዝ ባለሥልጣን፤ በማን-አለብኝ ይሞላል፡፡ ሁሉን ምንግዴ ይላል፡፡ ብሰርቅ፣ ብመዘብር፣ ህዝብን ብበድል፤ ወንበሬ እስካለ ድረስ የሚነካኝ የለም፤ ብሎ ይኩራራል፡፡ እንዲህ ያለው ሹም ውሎ አድሮ ከአምባገነንነት ሰፈር እንደማይወጣ ታሪክ ያሳየናል፡፡ መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድ እንዳለ ግን አሁንም ታሪክ በየዘመኑ ሲያሳየን ከርሟል፡፡ ያንን ልብ ማለት ከብዙ መዘዝ ያድናል፡፡ ሥልጣን ጣፋጭ ሰዓት እንዳለው ሁሉ፣ መራራ ቀንም አለው፡፡ የሥልጣን አሳሳች ባህሪ (intriguing nature) እስከ መጨረሻዋ የመውደቂያችን ደቂቃ የማንወድቅ መምሰሉ ነው፡፡ ይህን የተገነዘበ የፖለቲካ ሰው፣ በብልህነት እየታረመ ይጓዛል፡፡ እያንዳንዷን እርምጃውን በህዝብ ፍቅር ይለካል፡፡ በሀገር ጥቅም ይመዝናል፡፡ ከቶውንም የሥልጣን ዘመናችንን፣ በራስ በመተማመን ዘዴ መምራት፣ በሌሎች ላይ ተማምኖ ስህተት ላይ ከመውደቅ ያድናል፡፡ በሌሎች ሀብት መመካት፣ በሌሎች ጭንቅላት ማሰብ፣ በሌሎች ጥላ ስር ለመኖር መሞከር፣ ራሳችን ባላፈራነው ድል መኩራራት፣ የማታ ማታ ልጓሙን ሲስቡብን መላወሻ ማጣትን ያስከትላል፡፡ ይህን ቆም ብሎ አለመመርመርና የሌለንን አቅም ያለን ማስመሰል፤ አባዜው መቶ ከአምሳ ነው፡፡ “አውራ ዶሮ፤ በሰው ስጥ ሚስቱን ይጋብዛል” የሚለው ተረት ትርጉም የሚኖረው ይሄኔ ነው፡፡ ራስን ለኃላፊነት ማብቃትና በራስ መተማመንን የመሰለ ኃይል የለም!

Read 8885 times