Sunday, 04 March 2018 00:00

“አድዋ የኢትዮጵያዊነት ማረጋገጫ ማህተም ነው”

Written by 
Rate this item
(8 votes)

 · አድዋን በዘመኑ ፖለቲካ መቃኘት ታላቅ የታሪክ በደል መፈጸም ነው
  · ጀግኖች አባቶቻችን ጣሊያንን ያሸነፉት በጦር በጎራዴ አይደለም
  · ኢትዮጵያ ከተፈጠረች ጀምሮ በነፃነት የቆየች ሃገር ነች
  · ከ40 በላይ በአድዋ ላይ የተፃፉ መፅሐፍትን ይዘን ነው የሄድነው
  · “መታወቂያዬ ላይ ብሔሬ ከሚፃፍ፣ የደም ዓይነቴ ቢፃፍ ይሻለኛል”
  · ታሪክ ማለት ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም

  25 ወጣቶች የተሳተፉበትን የዘንድሮ “ጉዞ አድዋ” የመራው ታዋቂው የፊልም ባለሙያ ያሬድ ሹመቴ፤47 ቀናት ስለፈጀው “ጉዞ አድዋ”፤ ከኢትዮጵያዊነትና የአንድነት ስሜት ጋር ያለውን ቁርኝት፣ጀግኖች አባቶቻችን ጣሊያንን የተዋጉት በጦር በጎራዴ አለመሆኑን --- ወዘተ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባለፈው ረቡዕ ባደረገው የስልክ ቃለ ምልልስ አብራርቷል፡፡ መንግስት የአድዋ በዓልን በፖለቲካ ቅኝት ውስጥ አስገብቶ ለመዘከር ከሞከረ ታላቀ የታሪክ በደል መፈጸም መሆኑንም ይናገራል - ያሬድ ሹመቴ፡፡ ሌሎችም ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ እነሆ፡-

   የዘንድሮ “ጉዞ አድዋ” ምን ይመስላል?
ጉዞው ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ የተደረገ ነው፡፡ በዚህ ጉዞ የተሳተፉት ደግሞ 25 ተጓዦች ናቸው፡፡ 21 ወንዶችና 4 ሴቶች ናቸው የተሳተፉት፡፡ ጉዟው በአጠቃላይ 47 ቀናትን ፈጅቶብናል፡፡ የአድዋ ታሪክ የተሰራባቸውን ቦታዎች በሙሉ ተጉዘንባቸዋል፡፡ አባገሪማ ማሪያም፣ ሸዊቶና ሰሎዳ ይጠቀሳሉ፡፡
በጉዞ ላይ የሕብረተሰቡ አቀባበልስ እንዴት ነው?
በአጠቃላይ 1060 ኪ.ሜትር የሸፈነ ጉዞ ነው። ከአዲስ አበባ ከወጣን ጀምሮ በየቦታው በጣም አስደሳች አቀባበል ነው የተደረገልን፡፡ የህዝቡ ስሜት የተለየ ነበር፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ለየት የሚያደርገው፣ በኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ሃሳብ ውስጥ የአድዋ ድል፣ እንደ መፍትሄ እየተቆጠረ ነው፡፡ ብዙ ቦታ ላይ የአንድነት ስሜትን የመናፈቅና አንድነቱን ወደ ኋላ ሄዶ የመመኘት ነገር አስተውለናል፡፡ በብዙ ሰዎች ላይ እንዳየነው፤በአቀባበሉ ወቅት ዝም ብሎ መቀበል ብቻ ሳይሆን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ አንድነትን በመናፈቅ የተደረገ ነው፡፡
ወደፊት ይህን ጉዞ አስፍቶ የመቀጠል እቅድ አላችሁ?
እኛ ከ5 ዓመት በፊት የጀመርነው በ5 ሰው ነበር፡፡ አሁን 25 ሰው ደርሰናል፡፡ በ5 ዓመት ውስጥ የተጓዡ መጠን በ5 እጥፍ አድጓል፡፡ በቀጣይ እያሳደግነው ከሄድን፣ አድዋን የሚያህል ግዝፈት ያለው ህዝብ የሚሳተፍበት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ዋናው እኛ የምንፈልገው ነገር፣ አድዋ ጥልቀቱን ዝም ብሎ በስሜት ብቻ የሚረዱት ሳይሆን በዕውቀት ሲረዱት የበለጠ ጥልቀት ያለው ሆኖ ይገኛል፡፡ ፍቅር ደግሞ ከስሜት ይልቅ በዕውቀት ሲሆን የበለጠ የጠለቀ ይሆናል፡፡ ከዚህ አንፃር እኛ ከእግር ጉዞው በመለስ፣ በየሄድንበት ቦታ ስናርፍ፣ ንባብ ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ ታሪክ ማወቅ ላይ ነው ትኩረታችን፡፡ ከ40 በላይ በአድዋ ላይ የተፃፉ መፅሐፍትን ይዘን ነው የሄድነው፡፡ በየቦታው እያጣቀስን ነው ታሪክን የምንረዳው፡፡ ከዚህ ቀደም ንባቡን የማነበው እኔ ነበርኩ፤ ዘንድሮ ተስፋዬ ሞላ የተባለ ተጓዥ፣ በአንባቢነት አገልግሏል፡፡
በዚህ መንገድ እያነበብን 122 ወደ ኋላ፣ 1060 ወደፊት እየገሰገስን ነው ጉዟችንን ያጠናቀቅነው። አድዋን እስከ ዛሬ በስሜት ብቻ ስለምንረዳው፣ ብዙ የተዛቡ ምስሎችን በአዕምሮአችን ቀርፀናል። ለምሳሌ በጦር በጎራዴ አባቶቻችን እንደተዋጉ ነው ሁሉም የሚናገረው፡፡ አድዋን ያሸነፍነው ግን በጦርና በጎራዴ አይደለም፡፡ ከጣሊያን ጋር የሚገዳደር መሳሪያ ይዘን ነው፡፡ በጦር በጎራዴ የሚለው ታሪክ አድዋን አይገልፀውም፡፡ አድዋ ላይ ጠንካራ ዝግጅት አድርገን የተሰለፍነው፡፡ ለምሳሌ እኛ በጦርነቱ የተጠቀምነው መድፍ፣ ከፈረንሳይ የተገዛ 4500 ሜትር መተኮስ የሚችል ሲሆን ጣሊያን በአንፃሩ ይዞት የነበረው መድፍ 3800 ሜትር ርቀት የሚተኩስ ነበር፡፡ ስለዚህ ጣሊያኖች የያዙትን ምሽግ በተለይ እንዳየሱስ ላይ የነበረውን ውጊያ በቀላሉ መምታት ተችሎ ነበር፡፡
ጣሊያኖችን በጦር ዝግጅትና በኃይል አሰላለፍ ጭምር በልጠናቸው ነበር የሄድነው፤ እነሱ በንቀት ነበር የተመለከቱን፡፡ አረመኔ፣ ያልተማረ፣ ንቃተ ህሊና የሌለው ህዝብ ብለው፣ምኒልክን በቀፎ ይዘን እንመለሳለን በማለት በንቀት ነበር የተመለከቱት። እኛ ደግሞ አክብደን፣ በቂ ዝግጅት አድርገንበት ነው የገጠምናቸው፡፡ ከ100 ሺ በላይ የተሰለፈ ጦር፣ ሁሉም የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ነበረው፡፡ በአተኳኮስ ሥርአትም ቢሆን አዝማቻቸው ጀነራል ባራቴሪ የመሰከረው ነው፡፡ “ኢትዮጵያውያን ተዋጊዎች፤ ሁለት ወታደር በአንድ ጥይት የሚገድል ሰራዊት ነው  የነበራቸው፤ እኛ ግን ዝም ብለን ነበር የምናባክነው” ብሏል፤ ባራቴሪ፡፡ እነዚህን ታሪኮች ሚዲያውም ቢሆን አርቆ ማቅረብ መቻል አለበት፡፡ ጎራዴ የሚጠቀሙት ጠላት ቀረብ ሲል ጥይት ላለማባከን በሚደረግ ፍልሚያ ላይ ነበር፡፡ አባቶቻችን ዝም ብለው አይደለም የዘመቱ፤በበቂ ዝግጅትና እውቀት  ነው፣ ጦርነቱን በድል የተወጡት፡፡
የአድዋ ድል ላንተ ምንድን ነው?  
እንደሚታወቀው ማዘጋጃ ቤት የልደት ሰርተፊኬት ይሰጠናል፡፡ ይሄኛው ድል ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ማህተም የተረጋገጠበት፣ ኢትዮጵያዊነት የሚለው ቁመና ገዝፎ እንዲታይ፣ አካል ኖሮት እንዲጨበጥ ያስቻለ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነት ማረጋገጫ ደግሞ አድዋ ነው። ግዝፈት ያለው ታሪክ እንጥራ ብንል፣ ትልቁ የታሪካችን ማህተም አድዋ ነው፡፡
የአድዋ ድል፣ የግዝፈቱን ያህል ትኩረትና ክብር አግኝቷል ብለህ ታስባለህ?
ለአድዋ ታሪክ ትኩረት ተሰጥቷል ብዬ አላምንም፡፡ ግን ትንንሽ ፍንጮች እየታዩ ነው። አሁንም ቢሆን ግን በተለያየ መንገድ ድሉን የፖለቲካ አሽከር ለማድረግ ነው የሚሞክረው። በዘመኑ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ አድዋን ለመቃኘት መሞከር ትልቅ የታሪክ በደል ነው፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች በሚል ቅኝት አድዋን ልንዘክር ስንሞክር፤ አንድ ህዝብ ተብሎ የተቀመጠን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከፋፍሎ ማስቀመጥ ነው፡፡ ይሄ ያኔ የነበረውን ታሪክ አይወክልም፡፡ አሁን መንግስት የፖለቲካ አቅጣጫ አስይዞ ሊጠቀምበት እንደፈለገ ነው የሚታየው፡፡ ይሄ ደግሞ በትክክል የአድዋን ድል የሚመጥን አይደለም፡፡ መንግስት ድሉን ሊይዘው የሚገባው ከፖለቲካ ነፃ በሆነ፣ ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለትውልድ በሚጠቅም መንገድ ነው፡፡ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ብርሃን ሊሆን በሚችል መንገድ አድዋን ለመዘከር ቢሞከር መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
 ለምሳሌ የአባይን ጉዳይ ብንመለከት ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ በግጥሙም በዘፈኑም በእንጉርጉሮውም ይዞ ነው የኖረው፡፡ አሁን ግን “አባይ” ፖለቲካ ሆኗል፡፡ አሁን አባይ የሚል ቃል ከተፈጠረ ፖለቲካ ነው፡፡ የመንግስት የፖለቲካ ቃል ሆኖ እንዲቀር ነው የተደረገው፡፡ አድዋም የዚህ እጣ እንዳይደርሰው ያሰጋኛል፡፡ መንግስት የያዘበት አካሄድ፣ ወደዚያ እንዳያመራ ያሰጋኛል፡፡ መንግስት አድዋን ለመዘከር ሲያስብ፣ ወደ ራሱ ስቦ ሳይሆን፣ ወደ እውነተኛ ታሪኩ ራሱ ተስቦ መሆን አለበት፡፡ እርግጥ አሁን እኛም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ድጋፍ እያገኘን ነው፡፡ በተለይ ዶ/ር ሂሩት ወ/ማሪያም ወደ ሚኒስትርነቱ ከመጡ በኋላ ምሁራን ታሪኩን የሚመጥን ጉዳይ እንዲያቀርቡ በተለይ በሙዚየም ግንባታ ላይ ትክክለኛ ታሪኩን የሚመጥን ነገር ለመስራት የሚደረገውን ጥረት ማድነቅ ያስፈልጋል። ይህ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስራ ግን በኋላ ቅኝቱ ተለውጦ ወደ ፖለቲካ ቅኝት እንዳይገባ፣ ከወዲሁ ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ዝም ብሎ “የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል የአድዋ ድልን ..” የሚል መግለጫ ማውጣቱ ልክ ያልሆነ ነገር ነው፡፡ የአድዋ ድል የአባቶቻችን የጀግንነት ስራ በመሆኑ፤ “እንኳን ደስ ያለን፤ በአባቶቻችን እንኮራለን” ነው ሊባል የሚገባው፡፡ ወደ ራስ ቅኝት ማምጣት ብሔራዊ ስሜት አይፈጥርም፡፡ የዋህ ባለቅኔ ከወርቁ ይጀምራል ይባላል፡፡ መንግስት እንደዚያ አይነት አካሄድ አለው፡፡ ታሪኮች በራሳቸው ቆመው መዘከር ነው ያለባቸው፡፡ ከራስ ጋር እያገናኙ ፖለቲካዊ ቅኝት ለማስያዝ መሞከር ስህተት ነው፡፡
የአድዋ ድል ተገቢውን ክብር ያለማግኘቱ፣ ያጎደለብን ነገር ያለ ይመስልሃል?
በሚገባ አጉድሎብናል፡፡ አድዋ ብቻ ሳይሆን የአምስቱ ዓመት የአርበኝነት ታሪክም ራሱን የቻለ የኢትዮጵያውያን ትልቅ ተጋድሎ ነው፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የደርግ ነገር እንዳይነሳ ተዳፍኖ ቀረ እንጂ ኢትዮጵያውያን በሶማሌ ወረራ ያደረጉት ተጋድሎ እንዴት ይዘነጋል፡፡ ስንት የጀግንነት መስዋዕትነት የተከፈለበት አይደለም እንዴ?! ያውም ሀገርን በወረረ ኃይል ላይ “ህፃናት አምባ” የሚባል ማዕከል የተቋቋመው፣ የጦር ተጎጂ ወላጆች ህፃናትን ማሳደጊያ ነበር፡፡ የፖለቲካ ነገር ሆኖ ፈረሰ እንጂ ህያው ምስክር የነበረ ነው፡፡ ታሪክ ማለት ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም፡፡ በዚህ ረገድ ደርግ ትንሽም ቢሆን አድዋንም ሆነ ሌሎች የታሪክ ተጋድሎዎችን ለማንሳት ይሞክር ነበር፡፡ ከኢህአዴግ በኋላ ግን ህዝቡ ታሪክ ጠባቂ ባይሆን ኖሮ፣ አድዋ እንደውም የተሸነፍንበት ታሪክ ሆኖም ሊፃፍ ይችል ነበር፡፡
እንደምናውቀው በዚህች ሀገር ብሄራዊ መግባባት ያስፈልጋል ሲባል ነበር፡፡ መንግስት፤ ሃሳቡን አልቀበልም፤ ማን የተጣላ አለና ነው ብሔራዊ መግባባት የምትሉት ሲል ነበር፡፡ ዛሬ ራሱ የብሄራዊ መግባባት አጀንዳ  አራማጅ ሆኗል። ዋናውና ትልቁ ነገር፤ አንድ ህዝብ የሆነን፣ በህገ መንግስት ሳይቀር “ህዝቦች” እየተባለ እየተጠራ፣ በልዩነት ላይ ብቻ ብዙ ርቀት ከተሰራ በኋላ እንደገና የተበተነውን ለመስፈት መሞከር ማለት፣ የቡቱቶ ቀሚስ በመርፌ እንደ መጥቀም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ልዩነት ላይ ያተኮረ ስራ ተሰርቷል። አሁን ይሄን ዝም ብሎ ለመስፋት ከመሞከር በመጀመሪያ እስካሁን የነበረው ነገር ልክ አይደለም ብሎ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ዛሬም የአንድነትና የህብረት ስሜት ላይ ያተኮሩ በርካታ እድሎች አሉን፡፡ ነገስታቱን ለመኮነን ሲባል ጨቋኝና በዳይ አድርጎ በማቅረብ ህዝቡን ካጣላን በኋላ፣ ታሪክን እንዴት ማክበር ይቻላል? አንድን ንጉስ ታሪኩን አጥላልቶ፣ በሱ ዘመን የተሰራን ታላቅ ታሪክ እንዴት የማክበር ሞራል ይኖራል? ይሄ ስህተት መሰራቱን  ማመን ያስፈልጋል፡፡
በነገስታቱ ዘመን፣ ዛሬ የምንኮራባቸው፣እነ አክሱም ጎንደር፣ ላሊበላ የመሳሰሉት ተሰርተዋል። በዘመነ መሳፍንት ጊዜ ግን ህዝቡን ምናልባት ጦረኝነት ከማስተማር የዘለለ ለታሪክ የሚቀመጥ ነገር አልተሰራም። ምናልባት ህዝቡን፣ ለአድዋ የጦርነት ባህል ያለማመደው፣ ዘመነ መሳፍንት ሊሆን ይችላል፡፡ በተረፈ ግን መቧደንና መለያየት፣ በታሪካችን ውስጥ አውዳሚ ሆኖ ከማለፍ ውጭ ያመጣልን በጎ ነገር የለም፡፡
 በአሁን ጊዜ በህዝቡ ውስጥ ህብረትና አንድነት ጠፍቶ፣ ልዩነትና መከፋፈል ነግሷል እየተባለ ነው፡፡ አንተ ምን ትላለህ?
ይሄን በምሳሌ ልናገር፡- ሰይጣን፤ “እኔ ነኝ አምላካችሁ” ባለ ጊዜ፣ ”አይደለም አምላካችን እግዚአብሔር” ነው ያሉት፣ ከእነ ቅዱስ ሚካኤል ጎን የተሰለፉት መላዕክት ሲሆኑ፣ “ልክ ነህ አንተ ነህ አምላካችን” ያሉት ደግሞ ከሳጥናኤል ወገን ተሰልፈው ነበር፤ መሃል ላይ ደግሞ መናፍስቶች አሉ፡፡ እነዚህ መናፍስቶች አቋም አልነበራቸውም። ብዙ የመናፍስት ባህሪ ያላቸውን ግለሰቦች ዛሬም እናያለን፡፡
አሁን አብዛኛው ሰው፣ ዘመኑ በፈጠረው የንግግር ዘይቤ ውስጥ ራሱን የሚያስቀምጥ ነው። በግልፅ እናውራ ከተባለ፤ የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ የሞተ ነበር የሚመስለው፡፡ በሌላ በኩል የአንድነት አመለካከቶች ደብዝዘዋል ተብሎ ተሰግቶ ነበር፡፡ የኦሮሚያው ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ስለ ኢትዮጵያዊነት አንድነት ሲናገሩ፣ ህዝቡ ተቀበላቸው። ይሄ የህዝባችንን ትክክለኛ ቁመና ያሳየናል፡፡ ጥግ መያዝ፣ የፍርሃት ውጤት ነው፡፡ የዘረኝነት ሃሳብ የሚመጣውም ከፍርሃት ነው፡፡ ፍርሃት በሰፊው ተሰብኳል፤”እነ እከሌ ሊበሉህ ነው፣ እነ እከሌ አጥፍተውህ ነበር” በሚል የተፈበረከ፣ የህብረት ፀር የሆነ ፍርሃት ነው የተፈጠረው፡፡ እምነት ማጣትና መጠራጠር፣ መፍራትን ይወልዳል፤ፍርሃት ደግሞ ዘረኝነትን ይወልዳል፡፡ አሁን ይሄ እየተቀየረ፣ በፍርሃት ወደ ጠባብ ቡድናቸው ገብተው የነበሩ፣ አንድነቱ ሲሰበክ፣ ወደ ፊት እየወጡ ነው፡፡ አሁን ተስፋ ሰጪ ጊዜ ላይ እንዳለን ይሰማኛል፡፡ መንግስትም ይሄን የሰውን የህብረት፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የሰላም ፍላጎት የተረዳው ይመስለኛል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አሁንም የተፈበረከ ጥላቻ ላይ የሚተጉ አሉ። አሁን የአንድነትና የህብረት መንፈስ ጠፍቷል ከተባለ፣ የጠፋው አስቀድሞ በተሰራው ስራ ምክንያት ነው፡፡ ይሄ ትውልድ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በተለይም በመሪነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች፤ በህብረትና በአንድነት ላይ መስራት አለባቸው፡፡
ከመታወቂያህ ላይ “ብሔር” የሚለውን ለማስጠፋት ሙከራ ስታደርግ ነበር፡፡ ጉዳይህ ምን ላይ ደረሰ?
እኔ በመታወቂያዬ ላይ ብሔር የሚል ነገር እንዳይሰፍር ስጠይቅ ሁለት ነገሮችን አስቤ ነው። ብሄር የሌለበት መታወቂያ ከሰጡኝ ለመያዝ፣ ካልሰጡኝ ግን መታወቂያ የሚባል ነገር ላለመያዝ አስቤ ነው የተንቀሳቀስኩት፡፡ ስለዚህ አሁን እኔ የቀበሌ መታወቂያ የለኝም፡፡ በፓስፖርት ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ የራሴን እርምጃ ወስጃለሁ ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ እኔ ይቅርታ ይደረግልኝና አዲስ አበባ ባለቤቷ ማን እንደሆነ የማይታወቅ ግራ የምትገባኝ ከተማ ናት፡፡ ማን እንደሚመራት የማይታወቅ፣ ማን ለጥያቄህ መልስ እንደሚጥ የማይታወቅባት? እኔ በበኩሌ፤ የአዲስ አበባ ህዝብ ጥያቄ ገብቶት ለማስተዳደር የተቀመጠ ሰው አለ ብዬ አላምንም፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ የዘረኝነት ጥያቄ የለውም፡፡ አብዛኛው የአዲስ አበባ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ በኢትዮጵያዊነቴ እወቁኝ ነው የሚለው፡፡ ያንን መልስ ከመስጠት ይልቅ ህዝቡን ወደ ክፍፍል የሚወስድ ስራ ነው የሚሰራው። በገባሁባቸው ቢሮዎች ያስተዋልኩት ነገር፣ የበላይ ሰው የሚባለውን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። መልስ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባት ከዚህ የአድዋ ጉዞ በኋላ ከንቲባው ቢሮ ሄጄ፣ መልስ ለማግኘት እሞክራለሁ፡፡ እስካሁን የሄድኩባቸው ብዙ መንገዶች፣ እስከ ፌደራል ድረስ ውጤት አላስገኘልኝም፡፡
የመጨረሻ ጥያቄዬን ለከንቲባው ለማቅረብ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ መልስ የማላገኝበት ምክንያት ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ ምክንያቱም እኛ አዲስ አበባ ላይ ያነሳነው ጥያቄ፤ ኦሮሚያ ላይ ምላሽ አግኝቷል። ኦሮሚያ ላይ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪነት እንጂ ብሄርን የሚጠቅስ መታወቂያ መስጠት አቁመዋል፡፡ አቶ ለማ መገርሳ ራሳቸው፣ ይሄን ነገር ሲናገሩ ሰምቻቸዋለሁ፡፡ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር የህዝብ ለህዝብ ዝግጅት በነበረበት ወቅት፣ ራሳቸው አቶ ለማ መገርሳ፤ብሄርን መታወቂያ ላይ መፃፍ እንደቀረ ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሄ ኦሮሚያ ላይ ምላሽ ያገኘ ጉዳይ አዲስ አበባ ላይ ምላሽ የማያገኝበት ምክንያት አይኖርም፡፡ እኔ መታወቂያዬ ላይ ብሔሬን ከሚፅፉ፣ የደም ዓይነቴን ቢፅፉ ይሻለኛል፡፡ ምክኒያቱም ቢያንስ መንገድ ላይ አደጋ ደርሶብኝ ደም ቢያስፈልገኝ፣ በደም ልገሳ ለመዳን ይረዳኛል፡፡

Read 8007 times