Saturday, 03 March 2018 12:28

አንዳንድ እሳት አለ…

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

አንዳንድ እሳት አለ
ያላንዳች ማገዶ የተንቀለቀለ!
የእሳት እራት ፈጥሮ ነዶ የከሰለ፡፡
የእኛ እንደዚያ አይደለም
አድዋ ነው እሳቱ፣ ነደን አንጠፋም!
የአፍሪካ ኩራት ነን
ያውም ታሪክ ያለን
በኋላ-ቀር ጥይት፣ ወደፊት የተኮስን
በዚያም ያሸነፍን!...ትላንትም እኛ ነን
ዛሬም ያው እኛው ነን!!
እኛ ነደን ነደን ሲከፈት ምዕራፉ
እዩዋቸው ከዋክብት፣ ሊሞቁን ሲረግፉ!
ጠላቶች ይሽሹ፣ ታሪክ የሚፈሩ
አድዋን አኑረናል፣ ከነሙሉ ክብሩ!
አድዋ ፍም ነው ዛሬም፣ ያያት የቅድመ-አያት
አትጠራጠሩ እሳት አለው እትብት!
አድዋ ካአብራኩ ውስጥ
አያቴኮ አለበት
አባቴም አለበት
እኔም አለሁበት
የደሜ ፍርድ ነው!
ዐይናችን ውስጥ ነው፣ የአድዋ ንዳድ ያለው፡፡
በአፍ አይገባምኮ፣የደም ነው እትሙ
ባሩድ ነው ቀለሙ
መንጎሉ አጥንት ነው
ድርሳኑን ለአፍሪካ፣ የፃፈው በዚያ ነው፡፡
እሳቱ እሚኮራው፣ ያንን አንብቦ ነው!
ይቀጣጠል ቋያው
የልባችን ፅናት ፍቅር ነው ማገዶው!
ጠላቶች ይሸሹ ታሪክ የሚፈሩ
አድዋን አኑረናል ከነሙሉ ክብሩ
ክፍት አዕምሮ ያለው፣ ደጃፉን ያልዘጋ
ጀግንነት የባጀ፣ ይሰለፍ ከ’ኛጋ!
እኒያ ከዋክብቶች፤ ይሄንን ሰምተው ነው
        መላው የጠፋቸው!
የበለጠ ብርሃን፣ በእጃችን መኖሩን
         እንዲያምኑ መስክረው፤
አድዋን ደግመን ደግመን፣ እናንድድላቸው
ታሪክን ማንበቢያ፣ ጧፍ ይሁንላቸው!
ከላይ የወረዱ ከዋክብትን ውጠን
ሲሞላ ቀልባችን- ሲደርስ የልባችን
እኛው ራሳችን፣ ሰማይ እንሆናለን!
ይሄው ነው ትርክቱ፣ ሰበብ ምክንያቱ
ተወልደን ከእሳቱ
የማንንም እሳት የማንፈራበቱ! (ለአድዋ 2010)

Read 3756 times