Tuesday, 13 March 2018 12:50

በአንድ ሳምንት ውስጥ ሦስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
አሜሪካ- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ሩሲያ- በኒውክሌር ማብልያ፣ አረብ ኤምሬትስ- በወደብ አጠቃቀም አተኩረዋል ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ አበባ የሦስት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ተቀብላ አስተናግዳለች። የተባበሩት አረብ ኤምሬት፣ የአሜሪካና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሮች፡፡ ሳምንቱ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው ብለዋል- የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ። ሚኒስትሮቹ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በንግድ፣ በኢንቬስትመንት፣ በፀጥታና ደህንነት ጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር የተነጋገሩ ሲሆን በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ መወያየታቸውም ታውቋል፡፡ የተባበሩት አረብ ኢምሬት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን፤ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በወደብ አጠቃቀምና እንዲሁም በሰራተኞች አያያዝና ልውውጥ ላይ ሲነጋገሩ፣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በዋናነት በፀጥታና ደህንነት፣ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ እንዲሁም የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በኒውክሌር ግንባታ፣ በኢንቨስትመንት መወያየታቸው ተጠቁሟል፡፡ ረቡዕ አመሻሽ ላይ አዲስ አበባ የገቡት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሠን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደሚያሳስባቸውና መንግስት የቆይታ ጊዜውን ያሣጥረዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው፤ ከቲለርሠን ጋር በቀጠናዊ ፀጥታና ሠላም፣ በኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ትብብር እንዲሁም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች ላይ መነጋገራቸውን ገልፀዋል፡፡ የሠው ህይወት እየቀጠፈ ባለው የፀጥታ ችግር ተነጋግረናል ያሉት ቴለርሠን፤ የዜጎች መብትን ከመገደብ ይልቅ የበለጠ የሚረጋገጥበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ሽግግርን እንደግፈዋለን ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ሠላማዊ የስልጣን ሽግግር በለጋነት ለሚገኘው የሃገሪቱ ዲሞክራሲ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡ በሃገሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግስታቸው በእጅጉ እንደሚያሣስበው የጠቀሡት ቲለርሠን፤ አሣሣቢ የሚያደርገውም በመሠረታዊ የሠብአዊ መብቶች ላይ ገደብ ስለሚያበጅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይም የሠብአዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው፣ የህግና ስርአት መከበር አስፈላጊ ቢሆንም የፀጥታ ሃይሎች የሃይል እርምጃዎችን ከመውሠድ እንዲቆጠቡ ተነጋግረናል ብለዋል-ቲለርሰን፡፡ በሃገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ለማምጣት ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች አስፈላጊ መሆናቸውን እንዲሁም፣ ገደቦችን ከማበጀት ይልቅ ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር የሚደረግ ፖለቲካዊ ውይይት ጠቃሚ መሆኑን መነጋገራቸውንም አስታውቀዋል። ዜጎችም ለዲሞክራሲ መረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ሂደትን የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ፣ አመፅ ብቻውን መፍትሄ እንደማይሆን በመረዳት፣ በሃገሪቱ የተሻለውን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ “ሃገሪቱ ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ እንረዳለን” ያሉት ቲለርሠን “ዜጎች ሠላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄያቸውን ማቅረብ አለባቸው፤ መንግስትም መብትን ከመገደብ ይልቅ የበለጠ ማስፋት ነው ያለበት” ብለዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቆይታም እንደሚያጥር ተስፋ አደርጋለሁ ያሉት ቲለርሠን፤ “በቆይታው ወቅትም በዜጎች ላይ የሠብአዊ መብት ጥሠት ሊያስከትል ይችላል” የሚለውን ስጋት በሚያስወግድ ሁኔታ ሊተገበር እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡ አሜሪካ በኢትዮጵያ የሚደረገውን ዲሞክራሲን የማሣደግ ሒደትም እንደምትደግፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ለምን መረጡ? የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኛ የቀረበላቸው ቲለርሠን፤ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት 100 ዓመታትን የዘለቀ መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅትም በተለይ በአካባቢ የፀጥታ ጉዳይ ኢትዮጵያ አጋር መሆኗን በመጥቀስ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ለጋ ዲሞክራሲ ማገዝ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመነጋገር ነው ብለዋል፡፡ በቆይታቸውም በዲሞክራሲ ጉዳይ፣ በፀጥታና ደህንነት፣ በኢኮኖሚያዊና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ዙሪያ በሠፊው መነጋገራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ ወታደሮቿን በሠላም አስከባሪነት በመላክ ለቀጠናው ሠላምና ደህንነት የምታበረክተውን አስተዋፅኦ እንዲሁም ስደተኞችን ተቀብላ ማስተናገዷ ከፍተኛ ዋጋ የሚሠጠው መሆኑን ቲለርሠን በመግለጫቸው አውስተዋል፡፡ በሣምንቱ መጀመሪያ ላይ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የዩናይትድ አረብ ኢምሬት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ በዋናነት በሁለቱ ሃገራት መካከል ለወደፊቱ በሚኖረው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲሁም ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች ወደ ሃገሪቱ አቅንተው ደህንነታቸው ተጠብቆ በሚሠሩበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውና መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም አስታውቀዋል፡፡ በተመሣሣይ ከወራት በፊት የጉብኝት ፕሮግራም የተያዘላቸው የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሠርጌ ላቭሮቭም በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጉብኝታቸው ወቅትም ሩሲያ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ በኢትዮጵያ ለመገንባት የተስማሙ ሲሆን ሩሲያ ለኢትዮጵያ የ163 ሚሊዮን ዶላር እዳ ስረዛ ማድረጓም ታውቋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬት፣ የአሜሪካ እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጉብኝት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ሳምንቱ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው ብለዋል፡፡ የሩሲያና የአሜሪካ አምባሳደሮች በአንድ ሆቴል ማደራቸውን ጠቁመው፤ በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣታቸውም ጉዳይ “የተለየ ምስጢር የለውም፤ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው” ብለዋል። ከተባበሩት አረብ ኤምሬት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በተደረገ ውይይት፤ የሶማሊያን ሉአላዊነት በማይነካ መልኩ ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ላይ የ17 በመቶ ድርሻ ኖሯት፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬት ጋር ለመጠቀም ስምምነት ላይ መደረሱን ዶ/ር ወርቅነህ አስታውቀዋል፡፡ “የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በዋናነት ስለ ሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ሊጠይቁ አይደለም የመጡት፤ መደበኛ ዲፕሎማሲውን የማጠናከር ስራ ሊሰሩ ነው ጉብኝት ያደረጉት” ያሉት ዶ/ር ወርቅነህ፤ ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በተደረገው ውይይትም የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ጉዳይ እንዲሁም ኒውክሌርን ለሰላማዊ ጉዳይ በማዋል ጉዳይ ላይ መወያየታቸውን አስረድተዋል፡፡
Read 3344 times