Tuesday, 13 March 2018 12:52

“የሁከትና ብጥብጥ ተሳታፊዎችን በቁጥጥር ስር እያዋልኩ ነው” - ኮማንድ ፖስት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“የእስረኞች መለቀቅ በበጎ የሚታይ ነው፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ግን አሳሳቢ ነው” - የተመድ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን

በሁከትና ብጥብጥ የተሳተፉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑን የገለጸው ኮማንድ ፖስቱ፤ በሀገሪቱ አሁን የሚደረገው ተቃውሞ የቀለም አብዮት መልክ እየያዘ መምጣቱንና የመንግስት ስልጣን በሃይል ለመያዝ የመፈለግ አዝማሚያ እንዳለው አስታውቋል፡፡
ከሰኞ የካቲት 26 እስከ ረቡዕ የካቲት 28 በኦሮሚያ በተለይ ከአዲስ አበባ አምቦ ነቀምት ባለው አቅጣጫ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወሊሶ ጅማ መስመር፣ የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ተዘግተው መሰንበታቸውን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ጠቁመው፤ በአድማ የሰነበቱ ከተሞች ከረቡዕ አንስቶ በአብዛኛው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡
የንግድና የትራንስፖርት አድማ በተደረጉባቸው የኦሮሚያ ከተሞች በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱንና ፋብሪካ መቃጠሉን የጠቆመው ኮማንድ ፖስቱ፤ በ17 የፀጥታ ኃይሎችም ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል፣ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ፣ የሆስፒታልና የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ባቀረበው ዘገባ፤ ከአድማና ተቃውሞው ጋር ተያይዞ በተለያዩ ከተሞች 6 ሰዎች መገደላቸውን ጠቁሟል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ያለው ነገር የለም፡፡
በሰሞኑ የሀገሪቱ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬቴሪያት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ፤ በህዝብ የተመረጠን መንግስት በኃይል ለመጣል የሚደረግ እንቅስቃሴ መኖሩን ገልጸው፣ እንቅስቃሴውም የቀለም አብዮት መልክ እየያዘ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ እንቅስቃሴ አራት ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን፣ 10 ያህል ተሽከርካሪዎች መጎዳታቸውን የተናገሩት አቶ ሲራጅ፤ የቀበሌና ወረዳ ጽ/ቤቶች እንደተቃጠሉም ገልፀዋል፡፡ የንብረት ዘረፋና ከጸጥታ ሃይሎች ላይ መሳሪያ የመቀማት ሙከራ መደረጉ የተጠቆመ ሲሆን በጸጥታ ሃይሎች ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተነግሯል፡፡ ህብረተሰቡ መንግስት ተዳክሟል በሚል የሚናፈሰውን አሉባልታ ማመን እንደሌለበት የገለጹት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ፤ መንግስት እንዳሁኑም ተጠናክሮ አያውቅም ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያግዛል በሚል የጀመረውን የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታት እርምጃ እንደማይገታ ያስታወቁት አቶ ሲራጅ፤ በሌላ በኩል ኮማንድ ፖስቱ ከህብረተሰቡ የሚደርሱትን ጥቆማዎች መሰረት በማድረግ እንዲሁም በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከየት አካባቢና ምን ያህል እንደሆኑ አልጠቀሱም፡፡
በንግድና ትራንስፖርት የማቆም አድማ ላይ የሰነበቱት አብዛኞቹ የኦሮሚያ ከተሞች ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጀምሮ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው መመለሳቸውን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን በቡራዩና አዳማ አካባቢ ደግሞ በአድማው የተሳተፉ ነጋዴዎች “ህግ አላከበራችሁም” በሚል ንግድ ቤቶቻቸው እንደታሸጉባቸው ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ በወልቂጤ ከተማ ሲካሄድ የነበረው አድማ ቆሞ ከሐሙስ ጀምሮ መደበኛ እንቅስቃሴ መቀጠሉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባለፈው ሰኞ የካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም ባወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያው፤ ዜጎቹ ከአዲስ አበባ ውጪ እንዳይጓዙ ያሳሰበ ሲሆን ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው በሚገኙ ከተሞች የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴዎች መቆማቸውንም አስታውቆ ነበር፡፡
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዞይር ራድ አል ሁሴን ባለፈው ረቡዕ በተካሄደው 37ኛው የኮሚሽኑ መደበኛ ስብሰባ፤ የዓለም ሀገራት የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታን በቃኙበት ሪፖርታቸው፤ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከ7 ሺህ በላይ እስረኞችን መልቀቋ በበጎ የሚታይ ተቀባይነት ያለው እርምጃ መሆኑን ጠቁመው፤ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግን አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡
ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችና ለውጥ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው በእውነተኛና ሁሉን ያሳተፈ ውይይትና የፖለቲካ ሂደት ነው ብሏል - የኮሚሽኑ ሪፖርት፡፡
መንግሥትም በቅርቡ በተፈፀሚ የዜጎች ግድያ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን አጣርቶ ለህግ እንዲያቀርብ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል በሪፖርታቸው፡፡

Read 6243 times