Tuesday, 13 March 2018 13:15

“ኢንቨስትመንት” - የተጠላ ቃል ሆነ? እና የስራ እድል ከየት ይመጣል?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

ሰዎች ሰርተው በክብር እንዲኖሩ፣ ኢንቨስትመንትና የስራ እድል ቢስፋፋ አይሻልም?
የኢህአዴግ መግለጫዎች ውስጥ፣ “ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት” የሚል ሃሳብ አለመጠቀሱ፣… በኢህአዴግ ድርጅቶች መግለጫ ውስጥ፣ እንደ ዋና ጉዳይ አንድም ጊዜ ሳይነሳ መቅረቱ የጤና ነው? አይደለም። የቀውስና የትርምስ ነው። በኢንቨስትመንት የስራ እድል ካልተስፋፋኮ የመዳን ተስፋ አይኖርም።
አሳዛኙ ነገር፣… ገንነው የሚራገቡ የተቃውሞ ድምፆችም፣ የተሻለ ሃሳብ አላበረከቱም። የኢንቨስትመንት ነገር፣ ያን ያህልም ጉዳያቸው ሲሆን አይደመጥም። በፋብሪካ የአለም ጭራ በሆነች አገር ውስጥ፣ ፋብሪካ የማቃጠል ወንጀሎች እንደዘበት ሲፈፀሙ ነው ያየነው። ኢንቨስትመንት ተጠላ?
አማራጩስ? “የሃብትና የንብረት ክፍፍል” ነው? ማለትም የመንግስት ተመፅዋች መሆን!
የመንግስት ተመፅዋቾች ቁጥር በሚሊዮኖች እየጨመረ ነው። በ7 ሚ. ቋሚ ተረጂ የገጠር ነዋሪዎች ላይ፣ ሚሊዮን ተረጂ የከተማ ነዋሪዎችን ለመጨመር፣ የቢሊዮን ብሮች በጀት ተመድቧል - በአብዛኛው በብድር በመጣ ገንዘብ። 1.6 ሚ. የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችንም፣ የመንግስት በቋሚነት እንዲመግባቸው!
ወይስ የመንግስት ቢዝነሶችንና ፕሮጀክቶችን ማስፋፋት ነው አማራጩ? በ2 ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብለው ለ10 ዓመት እንዲጓተቱ፣ በ2 ቢ. ብር ይገነባሉ ተብለው 8 ቢ. ብር እንዲፈጁ? ከ960 የመንግስት ድርጅት መኪኖች መካከል፣ 470ዎቹ በተንዛዛ ቢሮክራሲ ለወራት ጋራዥ ውስጥ እንዲወዘፉ?
“ከተሞች ተለጠጡ፤ በእርሻ ቦታ ፋብሪካዎች ተተከሉ” የሚሉ የስካር ሃሳቦችና ተቃውሞዎችም አሉ!
ስለየትኛዋ አገር ነው የሚያወሩት? ስለኢትዮጵያ ከሆነ፣… የኢትዮጵያ ትልልቅ ከተሞች፣ ትንንሽና የገጠር ከተሞች፣ የትራንስፖርትና የፋብሪካ ተቋማት፣ እንዲሁም የማዕድን ቦታዎችም በሙሉ ተደምረው፣ ገና ኢምንት ናቸው። ከእርሻ ቦታ ጋር ሲነጻፀሩ፣… ተደማምረው 1% ያህል እንኳ እንደማይሞሉ ማየት በቂ ነው።
ፋብሪካ የሚዘጋ መንግስት!... የከተማው ሲሶ ያህል “ፓርክ” ይሁን የሚልና ፋብሪካዎችን እስከመዝጋት የሚደፍር የመንግስት ቢሮክራሲም አለላችሁ። በየጎዳናው የሚዘረገፍ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ በሚታይባት አገር፣ “በፋብሪካ ጭስ ሳቢያ የአለም ሙቀት በዓመት በ0.01 oc ይጨምራል” ብሎ ፋብሪካዎችንና የስራ እድልን መዝጋት!
ባለፉት ሁለት የቀውስና የውጥረት ዓመታት ውስጥ፣ በርካታ የኢህአዴግ መግለጫዎችን ሰምተናል። እንዴት፣ “ኢንቨስትመንት” የሚል ቃል ጨርሶ ይጠፋል? በኢህአዴግ ድርጅቶች በርካታ መግለጫዎች ውስጥ፣ በስራ አስፈፃሚም ሆነ በማዕከላዊ ኮሚቴ ተከታታይ ውሳኔዎች ውስጥስ፣ “ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት” የሚል ሃሳብ እንዴት አይኖርም? “ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት” እንደ ዋና ጉዳይ ሳይጠቀስ፣ አንድም ጊዜ በቁም ነገር ሳይነሳ መቅረቱ የጤና ነው? የጤና አይደለም። አገርን ለተጨማሪ ቀውስና ለለየለት ትርምስ የሚያጋልጥ በሽታ ነው። ይህንን የማይገነዘብ ገዢ ፓርቲስ እስከመቼ ይዘልቃል? በኢንቨስትመንት የስራ እድል ካልተስፋፋኮ፣ ከቀውስ የመውጣትና ከትርምስ የመዳን ተስፋ አይኖርም።
አሳዛኙ ነገር፣… ገንነው የሚራገቡ የተቃውሞ ድምፆችም፣ ብዙም የተሻለ ሃሳብ የሚያቀርቡ አልሆኑም። የኢንቨስትመንት ነገር፣ ያን ያህልም ጉዳያቸው ሲሆን አይደመጥም። በተቃራኒው፣ “ጭፍን ፀረ ኢንቨስትመንት ስሜት” ነው እየበረከተ የመጣው። በፋብሪካ የአለም ጭራ በሆነች አገር ውስጥ፣ ፋብሪካ የማቃጠል ወንጀሎች እንደዘበት ሲፈፀሙ እያየን!

እህስ? የመንግስት ተመፅዋችነት ማስፋፋት ይሻላል?
በየዓመቱ በቋሚነት የመንግስትን ድጋፍ የሚጠብቁ ከ7 ሚሊዮን በላይ የገጠር ነዋሪዎች አሉ። “የምግብ ዋስትና” ተብሎ ቋሚ በጀት የሚመደብላቸው ናቸው። ገሚሱ በጀት በብድር የሚመጣ መሆኑንም አስታውሱ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ፣ የከተማ ነዋሪ ተረጂዎችን ለማበራከት፣ የቢሊዮን ብሮች በጀት እየተመደበ ነው - በአብዛኛው በብድር የመጣ። ይህም ብቻ አይደለም።
“የተማሪዎች ምገባ” በሚል የተጀመረው የመንግስት እርዳታ፣ በዓመት ውስጥ ወደ ስድስት እጥፍ እንዲስፋፋና 1.6 ሚሊዮን የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን እንዲያካትት በጀት ተመድቧል - ከአገሪቱ የኢሌመንታሪ ተማሪዎች መካከል 15% ያህል ማለት ነው። በሚቀጥሉት ዓመታትስ? 30%፣… 50% እያለ አገሬውን በሙሉ ተመፅዋች ማድረግ እንደ ስኬት ሊቆጠር ነው?
ስኬትማ፣… በራሳቸው ጥረት ንብረት ማፍራትና ኑሯቸውን ማሻሻል፣ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ማለምለም የሚችሉ፣ ልጆቻቸውን መመገብ የማይቸግራቸው ዜጎች ሲበራከቱ ብናይ ነበር። በተመፅዋችነት ሳይሆን፣ “ሰርቼ ነው የምኖረው” ብለው በኩራትና በክብር ሕይወታቸውን የሚያጣጥሙና ለተጨማሪ ስኬት የሚበረታቱ ሰዎች ሲበራከቱ ማየት ነው - የአገር ስኬት። በሌላ አነጋገር፣… በራሳቸው ጥረት ሃብትና ንብረት የሚያፈሩ ታታሪ ሰዎች እንዲበራከቱ፣… በየጊዜው የሚፈጠሩ እልፍና እልፍ የስራ እድሎችም ይበልጥ እንዲሻሻሉ… ማድረግ ነው ሁነኛው መፍትሄ። ሌላ ዘዴ የለም። የግል ኢንቨስትመንትና የስራ እድል እንዲስፋፋ መፍቀድ፣ መጣር ነው ብቸኛው መፍትሄ።

ወይስ የፌደራልና የክልል የመንግስት ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት የድሃ አገር ሃብትን ማባከን ነው አማራጩ?
የመንግስት ቢዝነስና ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ፣ በተቃራኒው ከባድ የሃብት ብክነትና ኪሳራ እንደሚያስከትሉ፣ በደርግ ጊዜ እና ባለፉት 10 ዓመታት አይተነዋል። አዎ፣ ካሁን በፊት እንደጠቀስኩት፣ በፌደራል መንግስት አማካኝነት የተገነቡና ብዙ የተወራላቸው ግድቦች፣ የዚህ ብክነትና ኪሳራ ምስክሮች ናቸው - በ2 ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብለው 10 ዓመት የፈጁ፤… 2 ቢሊዮን ብር በማይሞላ ወጪ ይገነባሉ ተብለው ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ የፈጁ ግድቦች ናቸው። ነገር ግን፣ እንደ እንግዳ ክስተት መታየት የለባቸውም። ለምን?
በመንግስት ድርጅት የሚገነቡ የመንግስት ፕሮጀክቶች፣ ሁሌም የብክነትና የኪሳራ አውድማ ከመሆን አያመልጡም - በየትኛውም ፓርቲ፣ በየትኛውም መንግስት፣ በየትም አገር፣ በየትኛውም ዘመን።
ከስምንት ዓመት በፊት ብቻ አይደለም፣ ብክነትና ኪሳራው! አምናና ዘንድሮም ተመሳሳይ ነው። የዓመታት ልዩነት፣… ለውጥ እንደማያመጣ፣ የያኔውንና አዲሰኛውን መረጃ በማስተያየት ማረጋገጥ ይቻላል። በስራ ላይ ከነበሩ የውሃ ስራዎች ኢንተርፕራይዝ 960 መኪኖች መካከል፣ 470 መኪኖች በጥቃቅን ብልሽቶችና በተንዛዛ አሰራር፣ ለበርካታ ወራት ጋራዥ ውስጥ ተወዝፈው ነበር የተገኙት። ያልተበላሹትም ቢሆኑ፣ አንዳንዶቹ በሾፌር እጥረት፣ አንዳንዶቹ በጭቃ ተይዘው… ብቻ የመንግስት ቢሮክራሲ ጣጣው ተቆጥሮ አያልቅም። 50% ያህሉ ግን ጋራዥ ውስጥ ለወራት ይወዘፋሉ።
ይህንን መረጃ፣ በሌላ ድርጅት ከተደረገ አዲስ ጥናትና መረጃ አመሳክሩት። እንደገና 50% ያህል መኪኖች ጋራዥ ውስጥ! ከ118 የስኳር ኮርፖሬሽን ከባባድ መኪኖች መካከል፣ 64 በጥቃቅን ብልሽት ለወራት ጋራዥ ውስጥ የተቀመጡ ናቸው። ግን፣ ጋራዥ ያልገቡ መኪኖች በሙሉ፣ አገልግሎት ይሰጣሉ ማለት አይደለም። የመንግስት ፕሮጀክት ለወራት ሲጓተት፣ በርካታ ሚሊዮን ብሮች የፈሰሰባቸው “ኤክስካቫተሮች” ያለ አገልግሎት ለወራት ይቀመጣሉ። እነዚህ መረጃዎች፣ በፌደራል ኦዲተር የጥናት ሪፖርት ጭምር የተረጋገጡ ናቸው። ግን የፌደራል መስሪያ ቤቶች ብቻ አይደለም ችግሩ።
የፌደራልም ሆነ የክልል፣… ለነገሩ የትም አገር በየትኛውም ዘመን ቢሆን፣… የመንግስት ቢዝነስ፣… በተለይ በተለይ ደግሞ፣ በግል ኩባንያ ኮንትራክተርነት ሳይሆን በመንግስት ድርጅቶች አማካኝነት የሚገነቡ የመንግስት ፕሮጀክቶች፣… ለዓመታት ከመጓተት፣ እጥፍ ድርብ ሃብት ከማባከን አያመልጡም። ለዚህም፣ በየክልሉ የተገነቡ የኮንዶምኒዬም ቤቶችን ማየት ይቻላል - ለበርካታ ዓመታት ያለገዢ ተቀምጠው፣ የባንክ ወለድ ብቻ የሚከመርባቸው ሲሆኑ አይተናል።
በግድብ፣ በመስኖና በእርሻ ማሳ ዝግጅት ላይ ይሰማራሉ ተብለው በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልሎች… የተቋቋሙ የየክልሉ የመንግስት ድርጅቶች፣… ልክ እንደ ፌደራል ኢንተርፕራይዝ፣ እንደ ስኳርና ብረታብረት ኮርፖሬሽን፣… በርካታ ፕሮጀክቶችን ለዓመታት እያጓተቱ፣ በርካታ ቢሊዮንና ሚሊዮን ብር ሃብት አባክነዋል።
እና፣ በኢንቨስትመንት የስራ እድልን ከማስፋፋት ይልቅ፣… ማለትም፣ ሰው የመሆን ክብርና ኩራትን የሚያጎናፅፍ፣ የሚሊዮኖችን ኑሮ የሚያሻሽል የነጻ ገበያ ጉዞን ከማመቻቸት ይልቅ፣… ሰው የመሆን ክብርና ኩራትን በሚያሳጣ መንገድ ለዚያውም ላያዛልቅ ነገር፣ የመንግስት ተመፅዋችነትን ማንሰራፋት ይሻላል? የመንግስት ፕሮጀክቶችንና ቢዝነሶችን እየፈለፈልን፣ በክልልና በፌደራል የመንግስት ድርጅቶች አማካኝነት፣ የድሃ አገር የቢሊዮን ብሮች ሃብትን ማባከንና የስራ እድልን ማምከን ይሻላል?

ወይስ፣ ፋብሪካን እየዘጉ፣ ከተማን እያጥላሉ ወደ እንጦሮጦስ መንደርደር ይሻላል?
በአንድ በኩል፣ የከተማው ሲሶ ያህል “ፓርክ” ይሁን የሚልና ፋብሪካዎችን እስከመዝጋት የሚደፍር የመንግስት ቢሮክራሲ እናያለን። በየጎዳናው የሚዘረገፍ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ በየእለቱ በምናይባት አገር ውስጥ፣ “በፋብሪካ ጭስ ሳቢያ የአለም ሙቀት በዓመት በ0.01 oc ይጨምራል” ብሎ ፋብሪካዎችንና የስራ እድልን መዝጋት፣ ምን የሚሉት ስካር ነው!
የፋብሪካ ጭስ ከጠማቸው የአለማችን 10 አገሮች መካከል፣… ማለትም ከአለማችን 10 ድሃ አገሮች መካከል፣ አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ሳያውቁ ቀርተው ነው? በጦርነት ከፈራረሱት ከኮንጎና ከሶማሊያ፣ ከቡሩንዲና ከሴንትራል አፍሪካ ተርታ፣ በኋላ ቀርነት የምትመደብ አገርኮ ናት አገራችን - ገና የኢንዱስትሪ ቡቃያ በወጉ ለማየት ያልበቃች።
የካርቦን ጭስ የሌለበት አገር ለማየት የሚናፍቁ አንዳንድ የአውሮፓና የዩኤን ወገኞች፣… ከምር የሚናፍቁ ከሆነ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያ መጥተው የመኖሪያ ፈቃድ መጠየቅ ይችሉ ነበር። የእነዚህን ወገኞች ወሬና ኮንፈረንስ፣… “ፐርዳይምና ፈንድ”… እየሰሙና እየተቀበሉ የገዛ ራሳቸውን ህሊና የሚደፍኑ የአገራችን ባለስልጣናት፣ የገዢ ፓርቲም ሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንም ሆኑ ጋዜጠኞች፣ ወደህሊናቸው ቢመለሱና፣ የአገራቸው የኢትዮጵያ ኢምንት ፋብሪካና ኢንዱስትሪን ከነጭራሹ የማጥፋት ዘመቻቸውን ትተው፣… ኢንቨስትመንትና ፋብሪካ እንዲስፋፋ ቢጥሩ አይሻልም?
አለበለዚያኮ፣ የእስካሁኑ ዘመቻቸው፣ አገሪቱን ወደ ገደል የመገፍተር ዘመቻ ነው። አገሪቱ እንደሆነች፣ በድህነት፣ በኢንቨስትመንት እጥረት፣ በስራ እጦት፣… የትርምስና የመጠፋፋት አፋፍ ላይ ደርሳለች። ኧረ ወደ ህሊና እንመለስ።
ግን፣ ይህ ብቻ አይደለም አደጋው።
በሌላ በኩልም፣ ሌሎች የጥፋት ዘማቾች አሉላችሁ። እንደ ጅምር ተስፋ ሳይሆን፣ እንደ ከባድ አደጋ፣ “ከተማ ተስፋፋ። የገጠር መሬት ላይ ፋብሪካ ተገነባበት” እያሉ የሚጮሁ ሞልተዋል - ከገዢው ፓርቲም ሆነ ከተቃዋሚዎች። ከተማን አጥላልተው፣ ፋብሪካን ተጣጥለው፣ አገሪቱን ወደ ገደል መግፋት ማንን ይጠቅማል?
እዚህ ላይ፣ ፋብሪካንና ከተማን ለማጥላላት የሚቀርቡ ሰበቦችን በግልፅ ማየትና መለየት ያስፈልጋል። አዎ፣ ያለፈቃዱና ያለፍላጎቱ፣… ያለ በቂ ካሳና ዋጋ ከመኖሪያው የሚፈናቀል አንድም ሰው መኖር አልነበረበትም። አዎ፣ በከተሞች በተለይ በአዲስ አበባ፣ በርካታ ሺ ቤተሰቦች ከመሃል ከተማ ተፈናቅለዋል። የከተማ ነዋሪዎች ላይ ከተከሰተው የመፈናቀል ችግር ጋር ባይስተካከልም፣ በገጠርም በርካቶች ያለ በቂ ካሳ ተፈናቅለዋል። መሆን አልነበረበትም። ሊስተካከልም ይገባዋል።
መፈናቀልን የሚያስወግድ ሁነኛው መፍትሄማ፣ “መሬት የመንግስት ነው” የሚለው የሶሻሊዝም ኋላቀር ህግ ተሽሮ፣ “አገልግሎት ላይ የዋለ መሬት ሁሉ የነዋሪዎቹ የግል ይዞታ ነው” በሚል የካፒታሊዝም መርህ፣ ህጋዊ ስርዓት ማበጀት ነው። ነገር ግን፣ ይህንን ሁነኛ መፍትሄ ብዙዎቹ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች አይወድዱትም። በቃ፣ መሬት የመንግስት ነው በሚለው አቋማቸው ድርቅ ብለዋል - በዚህ አቋም አማካኝነት ነው ሰዎች አላግባብ የሚፈናቀሉት። ግን፣ ለሰዎች መፈናቀል ሰበብ የሚሆን አቋም ይዘው፣ “ሰዎች ተፈናቀሉ” በማለት መደስኮር፣… ሌላ ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል። አንድም ግብዝነት፣ አንድም አላዋቂነት፣ አንድም መሰሪነት።
ነገር ግን፣ የኢትዮጵያ ችግር ከዚህም የበለጠና እጅግ የሰፋ ነው። ከተማና ኢንዱስትሪ በአግባቡ በኢንቨስትመንት አማካኝነት እየተስፋፉና እየተሻሻ አለመሆናቸው፣… ትልቅ የዘመናችን ፈተና ነው - ለአገራችን ለኢትዮጵያ። የአለም ባንክና ኢትዮጵያ በጋራ ያደረጉት አዲስ የሳተላይት ጥናትን ማየት ይቻላል። ኢትዮጵያ፣ ገና የአለም ጭራ ናት - ከተማና ኢንዱስትሪ ያልተስፋፋባት። ከተሞችና ኢንዱስትሪዎች የያዙት ቦታ፣ ኢምንት ነው - ከቁጥር የማይገባ።
“ትልልቅ ከተሞች” ብቻ አይደሉም፤ ትንንሾቹም ተጨምረው፤ የገጠር መንደሮችም ጭምር ተደምረው፤ የትራንስፖርት፣ የፋብሪካና የማዕድን ስራ የሚካሄድባቸው ቦታዎችም ታክለው፣… ከአገሪቱ ጠቅላላ ስፋት ምን ያህሉን ይይዛሉ? በእስካሁን አዝማሚያው የሚቀጥል ከሆነ፣ 1% ለመሙላት መቶ ዓመትም የሚበቃው አይመስልም። ከ110 ሚሊዮን ሄክታር፣ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ለመድረስ… በ6 እጥፍ ለማደግ፣ ከእስከዛሬው ሁሉ በሚበልጥ ፍጥነት ከተሜነት ቢስፋፋ እንኳ… ወደ 50 ዓመት ይፈጅበታል - 1% ለመድረስ! እስካሁን የ1% ሩብ ያህል ቦታ አልያዙም
ትልልቅ ከተሞች፣ ትንንሽና የገጠር ከተሞች፣ የትራንስፖርትና የፋብሪካ ቦታዎች፣ የማዕድን ቦታዎችም ተደምረው፣ ምን ያህል ገና ኢምንት እንደሆነ ለማየት፣ ከእርሻ ቦታ ጋር ሲነጻፀሩ 1% ያህል እንኳ እንዳልሆነ ማየት በቂ ነው።
እና፣… “ከተማ ተስፋፋ፣… የእርሻ መሬት ፋብሪካ ተተከለበት” በማለት፣… አገሪቱ ከዳር እስከ ዳር በፋብሪካና በከተማ የተስፋፋባትና የበለፀገች ማስመሰል፣… እና ደግሞ ይህንን እንደ ብቸኛና ቁጥር 1 ችግር ፈርጆ የውግዘት መዓት ማዥጎድጎድን ስራዬ ብሎ መያዝ… ሌላ ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል? አንድም ግብዝነት፣ አንድም አላዋቂነት፣ አንድም መሰሪነት።

Read 2773 times