Print this page
Tuesday, 13 March 2018 13:23

ግልጽ ደብዳቤ ለሐይማኖት አባቶች

Written by  አያሌው አስረስ (መምህርና ጋዜጠኛ፤ የቅንጅት የቀድሞ የአዲስ አበባ ተመራጭ)
Rate this item
(7 votes)

በአለፉት 45 ቀናት ውስጥ ሁለት ጊዜ ያህል በቴሌቭዥን መስኮት ቀርባችሁ ስለ ሰላም አስፈላጊነትና ጠቃሚነት ምክር ሰጥታችኋል፡፡ ያንን ምክር ከተከታተሉት ሰዎች አንዱ እኔ ብሆንም ድፍረት ባይሆንብኝ፣ ነገሩ ቆቅ ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሆኖ ታይቶኛል፡፡ ስለ ሰላም እያስተማራችሁ ያላችሁት፣ የሰላምን ዋጋን የሚያውቀውን፣ የሚፈልገውን፣ ሰላም በሚፈልገው መንገድ ማግኘት አልሆንለት ብሎ የሚይዘው የሚጨብጠው ያጣውን፣ ቁጣውን በልዩ ልዩ መንገድ እየገለጠ ያለውን ሕዝብ ነው፡፡
መንግሥት ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት ብሎ በቅንነት አገርንና ሕዝብን የሚያገለግልበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ፣ ትክሻው አብጦ ክንዱ ፈርጥሞ ለሕዝብ አስፈሪ የሚሆንበት፣ ዜጎችን እንደ አንበሳ እየሰበረ፣ ‹‹አቶ እንዳሻው›› ሆኖ አገዛዙን የሚያጠነክርበትም ጊዜ አለ፡፡
በእኛ አገር መንግሥት የአምላክን ያህል ይፈራል ይከበራል፡፡ መንግሥት የተናገረው የእግዚአብሔርን ቃል ያህል ይታመናል፡፡ ስለዚህም ሕዝብ መንግሥትን ወዶ ይሸከማል፡፡ እስከ መጨረሻው ድረስ ሔዶ ያለውን ፈቃደኝነት፤
‹‹እናቴና አባቴን በግዜ ቀብሬ
መንግሥት እጦራለሁ ወገቤን አስሬ›› በማለት ይገልጻል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ አቋም ዘለዓለማዊ ሆኖ አይኖርም፡፡ ሕዝብ መንግሥቱን እንደ አልደገፈ ሁሉ ‹‹አጠገቤ አትድረስ፣ ዓይንህን አያሳየኝ›› የሚልበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ በንጉሡ ስም ይምል የነበረው ተማሪ፤ የንጉሡን መንግሥት ለመጣል የመጀመሪያ ተሰላፊ መሆኑ ነው፡፡
አሁን እነዚህ ሁለት ጊዜዎች በሀገራችን እየታዩ፣ በመንግሥትና ሕዝብ ከዚህ ቀደም በነበሩበትና በቆዩበት የግንኙነት መንገድ ሊቀጥሉ አለመቻላቸው በግልጽ እየተንጸባረቀ ነው፡፡ ይህ እውነት ከአባቶች ግንዛቤ የራቀ አይሆንም ብዬ አምናለሁ፡፡
ሕዝቡን መልካም አስተዳደር እንደነፈገው፣ መንግሥት በመንግሥትነቱ አገርና ሕዝብን መምራት አለመቻሉን እራሱ በአደባባይ እየተናገረ ነው፡፡
በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ምኀዳሩ መጥበቡን መንግሥት አምኗል፡፡ ይህ ማለት መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መገደቡን፣ በግልጽ አማርኛ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት መግፈፉን እራሱ በራሱ ላይ እየመሰከረ ነው ማለት ነው፡፡
ለልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ማካሔጃ ከተመደበው ባጀት በሚሊዮን እና በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የወጪ ማስረጃ ሊቀርብለት አልቻለም ብሎ ዋናው ኦዲተር መ/ቤት የየድርጅቶችን ስም እየጠራ ሲያስረዳ፣ ፊት ለፊት መንግሥት የሕዝብን ሃብት መጠበቅ አለማቻሉን እያሳየ፣ ባንጻሩም የሕዝብ ንብረት ዘረፋ መጧጧፉን እያስረዳ ነው፡፡
የሀገር ቤቱ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ (ሰመጉ) ወይም የውጮቹ የሰብዓዊ መብት የመከበርን ጉዳይ የሚከታተሉ ድርጅቶች እነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አይደሉም መንግሥታዊ የሆነው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ‹‹የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተገቢው በላይ ኃይል ተጠቅመዋል›› ብሎ ሪፖርት ማቅረቡ፣ መንግሥት በዚህ ጥፋት አንድም ሰው የሕግ ተጠያቂ አለማድረጉ ሲታይ፣ መንግሥት ለአረቀቀውና ላጸደቀው ሕገ መንግሥት የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል አክብሮት እንደሌለውም ማሳያ ነው፡፡
የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተዘዋውረው በጎበኟቸው ማረሚያ ቤቶች፣ በታራሚዎች ላይ ልዩ ልዩ በደል እንደሚፈጸም የሚያሳይ ሪፖርት ይዘው ተመልሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ ማረሚያ ቤቶች የማሰቃያ ቦታ መሆናቸውን መግለጥ ነው፡፡
እንዲህ እንዲህ አይነት ዝርዝሮችን በማቅረብ መንግሥት፣ በመንግሥትነት ማእረግና ተግባር አለመገኘቱን፣ ከሚዛን መውረዱን በማሳየት የሕዝብ ተቃውሞ ምክንያታዊ መሆኑን አስረግጦ ማስረዳት ይቻላል፡፡
ሕጋዊ ሆነው የተቋቋሙ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም አቅማቸው የፈቀደውን ያህል በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ መንግሥት ሲያደርግ በመኖሩ፣ ወደ ሕዝቡ መውረድና ተከታይ ለማፍራት ባለመቻላቸው የሕዝብን ጥያቄ ይዘው ሊቆሙ ሕዝብም እምነቱን በእነሱ ላይ ሊያሳርፍ አልሆነለትም፡፡ ይህን ተልዕኮ ይወጣሉ ብሎ የሚጠብቃቸው አይደሉም፡፡
መንግሥት ማንኛውም ቅሬታ ያለው ወገን በሕግ አግባብ በሰላማዊ መንገድ ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል በየጊዜው ቢገልጥም ፣ ሕጋዊ መንገዱን አስቀድሞ ስለዘጋውና በመጠኑ ክፍት በነበረበት ጊዜ (ከ1997 ዓ.ም በፊት) ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ሔዶ ያመጣው ለውጥ ስላልነበር፣ የራሱን መንገድ እንዲከተል ገፍቶታል፡፡ አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ እንዳሉት ‹‹ሕዝብ ፍትሕ በእጄ›› እያለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተቃዋሚው ክፍል አንድ ቦታ እንዳይሰባሰብ፣ መጣሁልህ ወይም መጣሁብህ የሚባል ኃይል እንዳይኖር በማድረጉ ሁልጊዜ ያልተጠበቀ አደጋ እንዲደርስ የሕዝብ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ በሥጋት ላይ እንዲወድቅ አድርጓል፡፡
በ2008 ዓ.ም መጨረሻ በተለይም ደግሞ 2009 ዓ.ም በኦሮሚያ፣ በአማራ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተቀሰቀሰ የሕዝብ አመጽ የብዙ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ ብዙ ፋብሪካዎች ወድመዋል፤ በግለሰቦች ንብረትም ላይ ጉዳት ደርሷል፤ 45 ሺህ ያህል ሰዎችም ለእስር ለመዳረግ በቅተዋል፡፡መንግሥት ከዚህ አመጽ ጀርባ የሻዕቢያ ተላላኪ ያላቸው ኦነግና ግንቦት ሰባት እንዳሉበት ቢገልጥም፣ በወቅቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጅ ውጭ የወሰደው የመፍትሔ እርምጃ አልነበረም፡፡ ለእነዚህ ድርጅቶች የድርድር ጥያቄ አልቀረበም እንጂ ቢቀርብ ለመቀበል፣ ሁለቱም ድርጅቶች በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ በመሆናቸው የመፍትሔ ማግኛ መንገዱን እንደሰማይ የራቀ ሆኖአል፡፡ መንግሥት ለሁለተኛ ጊዜም የአስቸአኳይ ጊዜ አዋጅ   አውጇል፡፡ ኃይል ግን ችግሩን ይፈታል ብዬ አለምንም፡፡
እያንዳንዱ ሰው በግሉ፣ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ሊያሳኳቸው የሚፈልጓቸው የአጭርና የረዥም ጊዜ እቅድ አላችው፡፡ አለማን ከግብ ማድረስ የሚቻለው ደግሞ አገርና ሕዝብ ሰላም ሲያገኝ ነው፡፡ ሰለም መውረድ አለበት!!!
ዛሬ ኢትዮጵያ እንደ አጽቢ አደራ መነኮሳት ፊት ለፊት መጥተው እርስ በእርስ መጠፋፋትን የሚያስቀሩ፣ በተፋጠጡ ኃይሎች መኃል ቆመው እርቅ እንዲወርድ የሚጠይቁ፣ እርቁ አደጋ ላይ ሲወድቅ እንደ አንኮበር ካህናት ‹‹ይፍቀዱልን ያኛውን ወገን እናነጋግር›› የሚሉ፣ ለያዙት ጉዳይ የጸኑ የሐይማኖት አባቶችን ትፈልጋለች፡፡ ምኒልክ ወደ አስር አመት ለሚጠጋ ጊዜ ሲጠሩበት የቆዩበትን ‹‹የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት›› የሚለውን መጠሪያ እንዲተዉ፣ የአጼ ዮሐንስን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትነት እንዲቀበሉና አጼ ዮሐንስም ምኒልክን ንጉሠ ሸዋ ብለው እንዲያነግሡ ያደረጉት የሐይማኖት አባቶችና ሁለቱ ማለትም አጼ ዮሐንስና ንጉሥ ምኒልክ በየበኩላቸው ተደራዳሪ አድርገው የላኳቸው መኳንንት ናቸው፡፡ እናንተ ይህን ማድረግ አያቅታችሁም፡፡
አበው፤ ‹‹እርቅ የፈለገን ንጉሥ እረኛ ያስታርቀዋል›› ይላሉ፡፡ እናንተ የእምነት አባቶች ናችሁ፤ የምእመናን እረኞች ናችሁ፡፡ ከመንግሥት ፊት የምትቆሙት የሕዝቡን የጥያቄ መልስ፣ እከሌ ከእከሌ ሳትል ተደራደርና አገር ሰላም ይሁን፤ እኛ ደግሞ ለማደራደር አለን ለማለት ነው፡፡
ይህ የታሪክ ጊዜ የናንተ ነው፤ ታሪክ ትሠሩ ዘንድ ከፍ ባለ አክብሮት አሳስባለሁ፡፡

 

Read 6347 times