Tuesday, 13 March 2018 13:44

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

“እማማ ሻማውን አብሪ …”

ከአርብ እስከ ሐሙስ በነበረው የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሦስት ትልልቅ በዓላት ነበሩ፡፡ … ታላቁ የዐድዋ ድል መታሰቢያ፣ የኦስካር ሽልማት ስነ - ስርዓት የተከናወነበትና የሴቶች ቀን የተከበረበት … ማርች 8!!
ሶስቱም ውስጥ ታላላቅ ሴቶች አሉ፣ ሶስቱም ውስጥ አሸናፊነት አለ፡፡ … የዐድዋ ድል የተገኘው በዋናነት በሴቶች ብርታት ነው፡፡ ጣይቱ ብጡል ዋናዋ ተዋናይ ብትሆንም በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ውሃ በመቅዳት፣ ምግብ በማብሰል፣ ጠጅ በመጣል፣ ቁስለኛን በማከምና በመንከባከብ፣ በዘፈንና በሽለላ ዘማቹን በማበረታታት ለድል አብቅተውናል። ሁለተኛው ደግሞ እሁድ ምሽት በተካሄደው የኦስካር ሽልማት ስነ - ስርዓት ስቲፈኒ ሃዱሽ አሸንፋ በቀዩ ምንጣፍ ላይ በሃበሻ ልብስ ሽር ብትን ማለቷ ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ ማርች 8፣ የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበር ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአስራ ሰባት ዓመቷ አሜሪካዊ ተማሪ ኤማ ጎንዳሌዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመረጡ አንድ መቶ ሃያ ተፅዕኖ ፈጣሪ የዘመኑ ሴቶች ውስጥ በቁጥር አንድ ደረጃ ተመርጣለች፡፡
ወዳጄ፡- ሴቶች ሁሌና የትም አሉ፡፡ … ይኖራሉም፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሴቶች የማይሳተፉበት፣ ድጋፋቸውን የማይሰጡበት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አይሳካም፡፡ ስልጣኔያችንን ወደፊት በሚያራምዱ የሳይንስ የጥበብና ፍልስፍና፣ የአዳዲስ ቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና ግኝቶች፣ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚደረጉ ትግሎች … የሴቶች ሚና ከፍተኛ ቢሆንም ገና ብዙ መንገድ መጓዝ እንደሚቀር አያጠራጥርም፡፡
በህብረተሰብ ዕድገት መንገድ ላይ ወይም በመጣንባቸው የታሪክ ጉዞ ውስጥ ሴቶች የወንዶችን ፍላጎት ለመፈፀም፣ ወንዶችን ለማገልገል የተፈጠሩ፣ እንደ ግል ንብረት ይቆጠሩ የነበሩት፣ በአጉል ልማድና ወግ የተተበተቡ፣ ጎታችና ኋላ ቀር ማህበረሰቦች ውስጥ በሴቶች ላይ የነበረው ፆታዊና መደባዊ ጭቆና የከፋ ነበር፡፡ የተጫነባቸው ቤተሰብአዊ ኃላፊነትና የስራ ድርሻ ሊሸከሙት ከሚችሉት በእጅጉ የከበደ ነበር፡፡ አሁን፣ አሁን ግን እነዚህ ሁኔታዎች ከዕውቀት መስፋፋትና ከስልጣኔ ዕድገት ጋር እየተሻሻሉ ፆታዊ ጭቆና እየደበዘዘ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጭቆና እየጎላ፣ ትግሉም አቅጣጫውን እየቀየረ የመምጣት አዝማሚያ እያሳየ ነው፡፡
አንዳንድ የመብት ተሟጋቾች የወንድ የበላይነትና የሴቶች የበታችነት የሚባለውን ጉዳይ … ወንድና ሴት ሆኖ ከመፈጠር ጋር የተገናኘ የልዩነት ሚዛን ሳይሆን፣ በተሳሳተ ግንዛቤ ላይ የዳበረና የደረጀ አጉል ባህል የፈጠረው አስተሳሰብ ነው ይላሉ፡፡ ይህንንም አስተሳሰብ በሰለጠነና ሁሉን አቀፍ በሆነ አዲስ ቅኝት በመለወጥ ጭቆናን ከፆታ ጋር የሚያዛምደውን እምነት መቀየር ይቻላል፣ ዕኩልነትን በመተሳሰብ መሰረት ላይ ማቆም አያስቸግርም፣ ፆታ ተፈጥሯዊ ፀጋ እንጂ አንዱን አስልጦ ሌላውን የሚያሳንስ ምክንያት ሊሆን አይገባም፤ ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ … የግድ እንደ ምክንያት ቢቆጠር እንኳ ሴቶች ባላቸው ስራና ማህበራዊ ኃላፊነት ላይ ልጆች የመውለድ፣ የማጥባትና የመንከባከብ ፀጋቸው ከተፈጥሮ ጋር ስለሚያቀራርባቸው የበላይነቱ የነሱ መሆን አለበት በማለትም ይከራከራሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሴቶች እንደ ማናቸውም ፍጡር፤ ተፈጥሮ በራሷ ህግ ምክንያት የሰውነት አካላቸውም ሆነ ስነ ልቦናቸው ለሚሰማሩበት የስራ ድርሻ እንዲመጥኑ አድርጋ በልክ ያነፀቻቸው በመሆኑ ወንዶች የሚሰሩትን ሁሉ መስራት አይጠበቅባቸውም፡፡ ሁሉን መስራት እየቻሉ ባላቸው ጭቆና ምክንያት እንዳይሰሩ ተደርገዋል ማለቱ አያስኬድም፣. ተፈጥሮ ለሁሉም ዕኩል ዓይን አላት፣ ወንድነት የራሱ ምክንያት፣ ሴትነት የራሱ ምክንያት አላቸው፤ “ዓይብና ቅልጥምም ወዴት ግጥምጥም” በማለት ይሟገታሉ፡፡
ከነዚህ አስተሳሰቦች ጋር በአንዳንድ ጎን የሚስማሙ፣ በሌላው ደግሞ የሚቃረኑ፣ የራሳቸው ፍልስፍናና ምክንያታዊነት ያላቸው እሳቤዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡ ሶቅራጥስ (ፕሌቶ)፣ ካንትና ፍራንሲስ ቤከንን የመሳሰሉት ቀደምት ፈላስፋዎችና እንደ ሲግመንድ ፍሮይድ አይነቶቹ የዘመናዊ ሳይኮሎጂ ሊቃውንትም በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን እሳቤዎች በመጽሃፎቻቸው አስፍረዋል፡፡
የጉዳዩ ባለቤቶች ነን ከሚሉት ውስጥ ደግሞ ፈላስፋዋ ሼሪ አርትነርን ጨምሮ ሱዛን ቦርዶ፣ ስምኦን ዶቩዋ፣ ኬት ሚሌት፣ ካሮል ጁሊያን፣ ኤቨሊን ኬለንና የመሳሰሉት የሴቶችን ጭቆናና የመፍትሄውን አቅጣጫ በየፅሁፎቻቸው በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
ከሴቶች ጉዳይ ባለፈ አለማችን ለሰው ልጆች የተሻለ የመኖሪያ ቦታ እንድትሆን የታገሉ በእግረ መንገድም የሴቶች ችግር ከሌሎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ጋር ያለውን ጥብቅ ተያያዥነት በድርሰቶቻቸው የገለፁ ሴት ልብ ወለድ ፀሐፍት ብዙ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ አየን ራንድ፣ ማርጋሬት ሚቸል፣ ቮርጂኒያ ዎልፍ፣ በርታ ክሌይ፣ ዳኒኤላ ስቲልና ሌሎች ይገኙበታል፡፡
ማርጋሬት ሚቸል በአስራ ስምንት መቶ አጋማሽ አካባቢ በነበረው የአሜሪካ እርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ የገለፀችበት Gone with the wind (“ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ርዕስ ነቢይ መኮንን ወደ አማርኛ መልሶታል) መጽሃፍዋ ውስጥ የታሪኩ ማጠንጠኛ የሆነችው በቀውሱ ምክንያት ሊፈርስ የነበረ ትልቅ ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነት የወደቀባት፣ የወደደችውን ማግባት ያልቻለች፣ ያገባችው በሳምንት ውስጥ የሞተባትን ገፀ ባህርይ ምሳሌ በማድረግ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በተለይ በሴቶች ላይ የሚያሳድሩትን እንግልት በገፀ ባህሪዋ አስታክካ እንዲህ በማለት ገልፃለች፡-
“She is not a girl who could dance and flirt with other dancing and flirting girls, she is not a women who could sit with other women and criticise the dancing and flirting girls, and she is not old enough to be a widow” ፍዳ የተጫነባት ባለታሪኳ ስካርለት አሃራ የአስራ ስድስት ዓመት ወጣት ነበረች፡፡
ወደኛ ሀገር ስንመለስ፤ ሴቶች የወንድ አገልጋይና ልጅ አሳዳጊ ብቻ ሆነው እንዳይቀሩ፣ ከማጀት ወደ አደባባይ እንዲወጡ፣ ወንዶቻቸው ከትምክህት ተላቀው አጋሮቻቸው እንዲሆኑ፣ የሚደርስባቸውን ፆታዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች ተቋቁመው በአገር ልማት ተግባራት ተሳትፎ እንዲያደርጉና ትምህርት እንዲማሩ በማሳመን ጥርጊያ ያሰናዱ፣ የብርሃን ጮራ የፈነጠቁ፣ የስልጣኔ ብርሃን እንዲገባ መስኮት የከፈቱ፣ ፆዊ በደል ለደረሰባቸው ጥብቅና የቆሙ፣ ሃኪም ቤት አቋቁመው ቁስላቸውን ያጠገጉ፣ የውርደት እንባቸውን ያበሱ፣ ሲርባቸው አጉርሰው፣ ሲታረዙ አልብሰው፣ መጠለያና መጠጊያ የሆኑ፣ በሙዚቃ፣ በቴአትር፣ በሲኒማ፣ በስነ ፅሑፍና በግጥም ብሶታቸውን የከወኑ፣ በሬዲዮናቸው የአየር ሰዓት መድበው፣ ፕሮግራም አዘጋጅተው ያስተማሩ ትልልቅ ሴቶች ነበሩ፡፡ … አሁንም አሉ!!
በፋሽስት ወረራ ወቅት በዱር በገደል በመንከራተት፣ ከአርበኛው ጎን የተዋደቁ፣ የሚስጢር መልዕክት በማቀበል የነፃነት ትግሉን ያፋፋሙ ጀግና ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ በነፃነት ማግስት አንዳንዶቹ “አቶ” ተብለው ሲጠሩ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡
ወዳጄ፡- የአገራችን ሴቶች በማናቸውን ጉዳይ ብቁ ሆነው ራሳቸውን እንዲችሉ በግልም ሆነ በማህበሮቻቸው በኩል ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ ሴቶች የህግ ባለሙያዎች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ደራስያን ማህበር፣ ሴቶች ይችላሉ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር፣ የሴታዊነት ንቅናቄና የመሳሰሉት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላችንን ማዋጣት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ማርች, ኤይትን ስናስታውስ ለነሱ እያጨበጨብን ነው!!
ወዳጄ፡- የዛሬው የሃሳብ መንገድ ርዕሳችን “እማማ ሻማውን አብሪ…” የሚል ነው፡፡ ይህን ያለው በሰሞኑ የኦስካር ሽልማት ስነ - ስርዓት ላይ በምርጥ አክተርነት አሸናፊ የሆነው ጌሪ ጎልድማን ነበር፡፡ ጌሪ የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ለሆኑት እናቱ “Mama light the candle, am bringing oscar” ብሎ ነበር፡፡ … አቤት ግጥምጥሞሽ!!
ሠላም!!

Read 1579 times