Tuesday, 13 March 2018 13:47

አብዮታዊ ዘብ - (ወግ)

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

ዘበኑ እንዴት ይጋልባል ጎበዝ፤ፍሬ ያለው ነገር ሳልከውን መገባደጃዬ ላይ ተቃረብኩ እኮ፡፡ ያ የእነ በለው፣ የእነ ውቃው ዘበን እንደ ዋዛ ታሪክ ሆኖ ቀረ። በዚህ ቅጽበት፣ ለመፈክር እንደ ባንዲራ የምስቀለው ክንድ የለኝም፡፡ ክንዴ ታጥፏል፡፡ እረ ጎበዝ፣ ለካስ የዘበን ጀግና እንጂ የሰው ጀግና የለውም። ዘበን የበቀሉን ጅራፍ ሲያስጮህ፣ የትናንት በደልን እንደ መስታየት ወለል አድርጎ እያሳየ ነው፡፡ የቀበርኩት ትውልድ ጩኸት መውጪያ መግቢያ ሲያሳጣኝ፣ በጉብዝና ወራት የዘነጋሁትን ፈጣሪ ለመደለል የምንተፍረቴን ቀና እላለሁ፡፡ ለጊዜው እፎይ ማለቴን እንጂ ጠሎቴ ይስመር አይስመር ግድ አይሰጠኝም፤ ያለ እግዚሐር ሰላምታ ኑዛዜዬን ማስቀደሜ ውሉ ቢጠፋኝ ነው፡፡ ታሪኬን እንካችሁ፡-
የዛሬን መኮራመቴን አትዩ፣ ጦቢያን ከአድኅሪያን ጉያ ለመንጠቅ በተጠንቀቅ የቆምኩ ቆፍጣና አብዮታዊ ዘብ ነበርኩ፡፡ ጦቢያን የሚያህል ሰፊ ሀገር መጠበቅ እንዲህ እንደ ወሬው ቀላል አይምሰላችሁ። ምን ያደርጋል፣ ለጦቢያዬም ለእኔም ዘበን ፊቱን አጠየመብን፡፡ ያን ሁሉ ሞገድኝነት ውሃ በላው፡፡ በልቶ እንደማይጠጋው ብላቴና፣ ዕድገቴ ዕለት ተዕለት ቀነጨረ፡፡ጠሎቴ ሰምሮ የአንድ የባለጠጋ ደጃፍ ዋርድያ ሆኜ፣ ጥቂት ዓመታትን ተወዛወዝኩ፡፡
ሰፊ ሀገር ጥዬ በአንዲት ጠባብ ቅጥር ግቢ ወዲህ ወዲያ መንከላወስ የሰርክ ተግባሬ ሆነ፡፡ ቆፍጣና አብዮታዊ ዘብነቱ ሸሽቶኝ፣ ተልመጥማጭነቱ ተዋረሰኝ። የስንቱን አድኃሪያንን ጎፈሬ ያፈራረሰው መዳፌ፣ ለቁንኑ አሳዳሪዬ እጅ መንሻ ሆኖ አረፈ፡፡ የታሪክ ሒሳብ እያወራረድኩ እንደሆንኩ ይገባኛል። ራሴን ልፈጣጥም አስብና፣ የሴጣን ጆሮ ይደፈን ብዬ ወደ ፈጣሪዬ አማትራለሁ፡፡ ግንበኛ የናቋት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ትሆናለች የምትለው ጥቅስ መንፈሴን ትጠግነኛለች፡፡ ራስ ለመሆን ወደ ላይ ሽቅብ ባንጋጠጥኩ ቁጥር ግን ወደ ታች የሚደፍቀኝ ጣውንቴ ብዙ ነው፡፡
የቀን ጎዶሎ
የቀን ጎዶሎ ጥርቅምቃሞ ክፉ ዘበንን ይወልዳል ያለው ጦማሪ ተዘነጋኝ፡፡ አዎ፣ በቀን ጎዶሎ የቆሙበት መሬት ጉድባ ነው፡፡የነኩት እንደ እምቧይ ካብ፣ የቀረቡት እንደ አስማት ከዓይን ይሰወራል፡፡ እኔም ተራው ደርሶኝ፣ በቀን ጎዶሎ ወጀብ ክፉኛ ተመታሁ፡፡ በቁምም በዕውንም ባላሰብኩት ድንገቴ ገጠመኝ እጤዬ ዱብ አለ። አስታውሳለሁ፣ የላብ አደሮች በዓል የዋለበት ዕለት ነበር። ከግብዙ አሳዳሪዬ ወርሃዊ ዳረጎቴን ተቀብዬ፣ ውሃ ወደ ምወሳስድባት መሸታ ቤት ጎራ አልኩኝ። ከመሽታ ቤቷ እልፍኝ ዘወትር የማይጠፉት እመት አዛሉ በቦታቸው ተሰይመዋል፡፡ እመት አዛሉ በሙያቸው ማኅተም ያዥ ናቸው፡፡ ከካቲካላው ከወሳሰዱ ከአፋቸው ለሚወድቀው አይጨነቁም፡፡
“አንተ ሴት አውል፣ግራ ክንድ ለፍካሬ ብቻ ይሰቀላል ያለው ማን ነው?” አሉ፤ገና ተደላድዬ ሳልቀመጥ፡፡
ከተናግሮ አናጋሪ ሰውረኝ ብዬ የጠለይኩት ጠሎት ትውስ አለኝና ጥሞናን መረጥኩ፡፡
“አንዳንዴም እንዲህ ማኅተም ለመደለቅ ተጠቀምበት፡፡” አሉና፤ በግራ እጃቸው የካቲካላዋ ብልቃት የተወዘፈችበትን አግዳሚ ወንበር ክፉኛ ወገሩት፡፡
መሸተኛው በሙሉ አውካካ፡፡ አብዮታዊ ዘብነቴን ከእኔ ሌላ ሰው ሲነካብኝ ደርሶ ሆድ ይብሰኛል፡፡ አንደበቴን መለጎም ተሳነኝ፡፡ በውስጤ የሚገላበጠው ቅያሜ ቀለል እንዲልልኝ የመልስ ምት አስወነጨፍኩ፡፡
“ወትሮም ዕጣ ክፍሌ ከትልቅ ሰው ጋር ነው፡፡” አልኩኝ፤ ብሽቀት ባኳተነው ቅላጼ፡፡
“ኡኡኡቴ…….እጅህን ያዝንህ እንዴ…ወትሮም አድርባይ ባለሟል ከይህ በላይ ምን ምኞት አለው?” ተናግሮ አናጋሪዋ ባልቴት፣ ይበልጥ ተፈታተኑኝ፡፡
ተሳልቋቸው እንደ ካራ ውስጤን በላለተው፡፡ በተለይ አድርባይ የምትለው ከይሲ ቃል፣ በህሊናዬ ውስጥ ደጋግማ አቃጨለች፡፡ በርግጥ በእዛ በእነ በለው ዘበን፣ አለቆቼ ፊት ነጥብ ለማስቆጠር፣ በአብዮቱ ቀበኞች ላይ ለመዝመት ቅድሚያ ስሰለፍ ኖሬያለሁ። ቢሆንም ቢሆንም፣ በዚህ ዘበን፣ አድርባይነት ወይም ሞት ያሉ አድርባያዊያን ወፈ ሰማይ ናቸው፡፡ታዲያ የእኔ አድርባይነት ለምን ገኖ ይንጠባረቃል፡፡ ማንም ተነስቶ በኩራት እንደ መታወቂያ የሚመመዘው ማንነት መሆኑን ዘንግተውት ነው?
ያሸለበው የአብዮታዊ ዘብ ወኔዬ ድንገት እንደ እምቦሳ አምቡር እምቡር እያለ ታገለኝ፡፡ በመዳፌ የጨበጥኩትን መለኪያ፣ ከእነ ካቲካላዋ እንደ ሚሳዬል ወደ ባልቴቷ አስወነጨፍኩት፡፡ መለኪያዋ መስቀለኛቸው ላይ ውሃ እንደሆነች ድክምክም ብለው ከወንበሩ ላይ ክልተው አሉ፡፡ እኔም እጄን ለመንግሥት ሰጠሁ፡፡
እመት አዛሉ በተዓምር ቢተርፉም የእኔ ዕጣ ፈንታ ዘብጥያ ሆነ፡፡ካራ ይዘው ለወራት ሲያስፈልጉኝ እንደነበር ከወሬ አቀባይ ሰማሁ፡፡ የወህኒ ቤቱ ኑሮ ብዙም አልጠገገኝም፡፡ዓለም ሰፊ እስር ቤት ናት በሚለው የወህኒ ቤት ጥቅስ እየተጽናናሁ፣ እንደ ቀልድ የእስር ዘበኔን፣ እንደ ውሃ ጨለጥኩት፡፡
ከእስር ወደ እስር
ውጪው ሰፊ እስር ቤት ሆነብኝ፡፡ ወየት እንደምሄድ ግራ ገብቶኛል፡፡ በጉብዝናዬ ወራት ያላቆምኩት ጎጆ አሁን ከየት ይመጣል፡፡ ወህኒ ቤት የቋጠርኳትን ፈረንካ ምን ላይ እንደምበትናት አውጥቼ አውርጄ አንድ ሐሳብ ውል አለኝ፡፡ የጎዳና ላይ ንግድ፡፡ የጎዳና ንግድ እንኳን እንደ እኔ ላለው ኑሮና ዘበን ተጋግዘው ላጎበጡት አዛውንት ይቅርና፣ ለወደል ኮበሌም የሚዳላ አይደለም። እንደ ምንም ተፍገምግሜ መፋቂያ ለመቸርቸር ተሰነዳዳሁ፡፡ ችጋር እየፋቀኝ የመፋቂያውን ችርቻሮ ቀስ በቀስ ሰለጠንኩበት፡፡ ከመፋቂያው መሳ ለመሳ መነበብ የተሳናቸው የተገፉ መጻሕፍትን በአንድነት ቀይጬ፣ የጎዳናውን ንግድ አጧጧፍኩት፡፡
አላፊ አግዳሚው ቀን የጣላቸውን መጻሕፍት በግራ እጁ እንደ ሥጋ መዝኖ፣ ፊቱን ያደምንና ወደ ሥፍራቸው ይገፋቸዋል፡፡ ለመጻሕፍት ፊት የሚሰጥ መንገደኛ እምብዛም ነው፡፡ ባይሆን ለመፋቂያው እጁ ይፈታል። በማያወላዳ ቅንጥብጣቢ ጥቅማጥቅም የዕለት ጉርሴን ለመሸፈን የአቅሜን ተወተረተርኩ፡፡ ይህም ኑሮ ተሁኖ ተሙቶ፣ ሳይውል ሳያድር፣ ጣውንቶቼ ሊቀናቀኑኝ ከየጎሬው ብቅ ብቅ አሉ፡፡
የብቻዬ መነሃሪያ የነበረችው ሥፍራ ቀስ በቀስ በሰው ግሪሳ መወረር ጀመረች፡፡ ምጽዋት ጠያቂ ነዳያን ዙሪዬን ከብበው ደሴት አስመሰሉኝ። ከነዲያኑ መሀል ለፍቶ አዳሪነቴ እንዲታወቅልኝ ሌጣዬን እጮኻለሁ። በተጣራሪ ኩታገጠም ነዳያን በፉክክር ስሜት ለምጽዋት መንቁራቸውን ያላቅቃሉ። ለጉራማይሌው ጩኸታችን አላፊ አግድሚው በእየፊናው በእጄ ይላል። መናኸሪያችንን ጠብ ርቋት አያውቅም፡፡ ድንበር መገፋፋቱ በእኛ ይከፋል። እግዚሐር የፈጠረውን ምድር ለምጽዋት እንኳን አብቃቅትን መጠቀም ተስኖን እርስ በእርሳችን እንናከሳለን፡፡ ጥድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ፤ ነበር ያለው የሀገሬ ሰው፡፡
ዕለተ ሐሙስ ነበር፡፡ ልማደኛው ዋይታና ግርግር መናኸሪያችንን ተዋርሷታል፡፡ ከወትሮው በተለየ ግምኛ ነደደኝ፡፡ ጠቡን ላበርድ ወደ ሥፍራው ባለ በሌለ ኃይሌ ተንደረደርኩ፡፡ ህንጣ የሚያህል ሰው ከአሁን ከአሁን ፈረስኩ እያለ ይገለገላል፡፡ ከሥሩ በንዴት የሚርገፈገፉት ኮስታራ አዛውንት ሊተናነቁት ይጋበዛሉ፡፡
“አንተ አውቆ አበድ፤ እንዲህ ጫንቃችን ላይ እየጨፈርክ……… እስከመቼ!?” የእንቅልፍ ጠኔ ያጠናገረውን ፊታቸውን እያባበሱ፣ በጀግንነት ይንቀጠቀጣሉ፡፡
መሀላቸው ቆፍጠን ብዬ እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ አልኩ፡፡ጠቡ ያባነናቸው የሚመስሉ መለዮ ለባሽ ደንብ አስከባሪዎች ከየት መጡ ሳይባል ድንገት ተከሰቱ፡፡ጠቡን ገፍተው ከእኔ ጓዝ ላይ ሊዘምቱ በአንድነት ተመሙ፡፡ እኔም ጓዜን ልታደግ ፈለጋቸውን እያነፈነፍኩ በደመ-ነፍስ አመራሁ፡፡
“ደክሞ አዳሪ ነኝ” አልኩ፤እልህ በተናነቀው ስሜት፡፡
“እኛም ደክሞ አዳሪ ነን” ከላባው ደንብ አስከባሪ፣ ቀንዴን አለኝ፡፡
“ቆይ ... እኔ እንደሌላው ለምጽዋት አላንቋረርኩ?? ለምን በደሉ በእኔ ላይ እንዲህ ይከፋል?” ሀሞቴን ኮስተር ለማድረግ ተጣጣርኩ፡፡
“ማንቋረር መብትህ ነው” ሌላኛው እግረ ነጠላ፣ ተዘባበተብኝ፡፡
“አይ ጦባዬ አድባርሽ ምንው አልታረቅ አለኝ፣ ክንዴን ሳልንተራስ፣ የሰው እጅ ጠባቂ ልታደርጊኝ?” ባለሁበት እንደ ሀውልት ተገትሬ በውስጤ አጉተመተምኩ፡፡ ከኋላዬ የእሳት ጫሪያዋ ነዳይ ድምጽ ይሰማኛል፡፡
“ወትሮም ቲግደረደሩ ነው፣ ከእኛ ዘንድ ቢቀየጡ ይሻሎት ነበር” አለች፤ በደረቅ ሳቋ እየተርገፈገፈች፡፡
ድንገት የአብዮታዊ ዘብ ወኔዬ ሁለመናዬን ወረረኝ። ትዕግሰቴ የውሀ ሽታ ሆነብኝ። ተወንጭፌ አንደኛው አስተናባሪ ላይ እንደ እባብ ተጠመጠምኩበት፡፡ አናቴ ላይ የዱላ መንጋ ሲከታተልና ራሴን ስስት አንድ ሆነ፡፡ ደንብ በመተላለፍ ክስ ከምባዝንበት ሰፊ የዓለም እስር ቤት ተፈናቅዬ፣ በአንድ ክንድ ልክ ወደ ተከረከመች ወህኒ ቤት ላይ እንድሰፍር ተፈረደብኝ፡፡ ከእስር ወደ እስር ይሉሀል እንዲህ ነው…..፡፡



Read 1569 times