Sunday, 18 March 2018 00:00

ህገ ወጥ የተባሉ በሺዎች የሚጠቆሩ ቤቶች ሰሞኑን በድንገት እንዲፈርሱ ተደርጓል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ሰፈራ ወይም ኪዳነምህረት በሚባለው አካባቢ በህገ ወጥ መንገድ ተገንብተዋል የተባሉ በርካታ ቤቶች ያለ ማስጠንቀቂያ በድንገት እንደፈረሰባቸው የተናገሩት ነዋሪዎች በዚህም የተነሳ መጠለያ አልባ በመሆን ለችግር መጋለጣቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
አርብ የካቲት 30 2010 ዓ.ም በአካባቢው ከአንድ ወር ወደዚህ የተሰሩ ቤቶችን ለማፍረስ በሚል የተሰማራው አፍራሽ ግብረ ኃይል፤ ነባሮችንና አዲስ የተሰሩትን ሳይለይ በጅምላ በቡልዶዘርና በዶዘር ማፍረሱን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
በዚህ ህገ ወጥ የተባሉ ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች መፍረሳቸውን የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የማፍረስ ዘመቻው ምንም ያልተዘጋጀንበት፤ ማስጠንቀቂያም ያልተሰጠበት በመሆኑ ህይወታችን ተመሰቃቅሏል፣ ለበረንዳ አዳሪነትም ተጋልጠናል” ብለዋል፡፡
በ1999 ዓ.ም ከአካባቢው አርሶ አደሮች ላይ 150 ካ.ሜትር ቦታ በመግዛት ሶስት ክፍል ቤት መስራታቸውን የገለፁ አንድ አባወራ፤ ቤቱ ህጋዊ ይሆንላችኋል ተብለው አስፈላጊ የግዢ ውል ሰነዶችን ለክፍለ ከተማው አስገብተው በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በድንገተኛ እርምጃው እንደፈረሰባቸው አስታውቀዋል፡፡
ዙሪያውን በፀጥታ ኃይሎች የተከበበ በመሆኑ እቃቸውን ማውጣት እንኳ እንዳልቻሉ የገለፁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ አፍራሽ ግብረ ኃይሉ ቆርቆሮዎችን ከጣራ ላይ በፍጥነት በሰው ኃይል በመንቀል፣ ግድግዳውን በጅምላ እንዳፈረሱ ተናግረዋል፡፡ ፍራሽ ቆርቆሮዎቹንም በአይሱዙ ተሽከርካሪ ተጭኖ እንደተወሰደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል፡፡  በቦታው ከ10 ዓመት በፊት ከአርሶ አደር ላይ ቦታ ገዝተው መኖሪያ ቤታቸውን ሰርተው ከ7 ቤተሰቦቻቸው ጋር ይኖሩ እንደነበር የገለፁት ሌላው ቅሬታ አቅራቢ፤ ህጋዊ ትሆናላችሁ ተብለን የልማት መዋጮ ስናዋጣ ነበር የከረምነው ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ በስልክ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ኃላፊ ኮማንደር አሳዬ አምባዬ፤ ህገ ወጥ ቤቶችን የማፍረስ ስራ መሰራቱን ገልፀው ለተጨማሪ መረጃ በቢሮአችን በአካል ተገኝታችሁ መውሰድ ትችላላችሁ ብለዋል፡፡

Read 8074 times