Sunday, 18 March 2018 00:00

ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ የአ/አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅን ጠርቶ አነጋገረ

Written by 
Rate this item
(19 votes)

 · “አገሪቱ ጭንቀት ላይ እያለች መጸለይ እንጂ መጉላላት አይገባችሁም”
            - ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር
     · “ሙስናን ቀጣዩ ትውልድ ይቀርፈው ይሆናል” - ፓትርያርክ አባ ማትያስ

   የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ በኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ያይኑን በጽ/ቤቱ ጠርቶ፣ ከቤተ ክርስቲያን በሕገ ወጥ መንገድ በተባረሩ 250 ያህል አገልጋዮችና ሠራተኞች የመብት ጥሰት ጉዳይ አነጋገረ፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር፤ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ በጽ/ቤታቸው ጠርተው ባነጋገሩበት ወቅት፣ የካህናቱ አቤቱታ ተቀባይነት እንዳለው አስታውቀው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተለያዩ አድባራት ጥቅማችን ሳይጠበቅ፣ ጉዳያችን በአግባቡ ሳይመረመር በሕገ ወጥ መንገድ ታግደናል፣ ተሰናብተናል፣ ተዛውረናል፤ ሲሉ ለኮሚሽኑ ያመለከቱት 250 ያህል ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች፣ በሀገረ ስብከቱ ያለውን የመልካም አስተዳደር እና የሙስና ችግር በማጋለጣችን በደል ተፈጽሞብናል ብለዋል - ለኮሚሽኑ በጽሑፍ ባቀረቡት አቤቱታ፡፡
ይህን የካህናቱንና የሠራተኞችን አቤቱታ የተቀበለው ኮሚሽኑ፤ ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሓላፊዎች ጋር ለአራት ሰዓታት በጉዳዩ ላይ እንደተነጋገረ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የሥራ ሓላፊዎቹን በተናጠል ኮሚሽኑ ካነጋገረ በኋላም ከአቤቱታ አቅራቢዎቹ ጋር በመሆን በጉዳዩ ላይ መወያየታቸው ታውቋል፡፡
ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔርም ለአቤቱታዎቹ መፍትሔ እንደሚሰጡ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ቃል እንደገቡላቸው በመጠቆም፤ “ሀገሪቱ ጭንቅ ላይ እያለች መጸለይ እንጂ መጉላላት አይገባችሁም፤ ጉዳያችሁ በአጭር ጊዜ መፍትሔ ያገኛል፤” ብለዋል- በስብሰባው የተሣተፉ ካህናት ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም፤ አቤቱታ አቅራቢዎቹ እንደ ቅሬታቸው እየታየ ምላሽ ይሰጣቸዋል፤” ያሉ ሲሆን፣ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ግን፤ የችግሩ ፈጣሪ ከሆነው የሀገረ ስብከቱ አመራር የምንጠብቀው መፍትሔ የለም፤ ብለዋል፡፡
አክለውም፤ “ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ ጉዳያችን እንዲጣራ እንጂ ሀገረ ስብከቱ ችግሩን የመፍታት አቅም የለውም፤” ሲሉ  በአስተዳደሩ ተስፋ መቁረጣቸውን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ በበኩላቸው፤ ሀገረ ስብከቱ ለአንድ ጊዜ ዕድል ይሰጠውና መፍትሔውን ያብጅ፤ የሚል ውሳኔ መስጠታቸው ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከትን በበላይነት የሚመሩት ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ በዓለ ሢመታቸውን ምክንያት በማድረግ በቅርቡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የሙስና ጉዳይ ከ5 ዓመት በፊት ቀላል መስሎኝ ነበር፤ ነገር ግን በኋላ ቀላል እንዳልሆነ ተረድቻለሁ፤ ብለዋል፡፡
ሙስናው በኔትወርክ የተሳሰረና እንደ ሸረሪት ድር ያደራ መሆኑን በመጥቀስም፣ በሀገረ ስብከቱ መጠነኛ ለውጥ ቢታይም ሙስና አሁንም መንሰራፋቱን ጠቁመው፤ “ምናልባት በቀጣይ ትውልዱ ይቀርፈው ይሆናል፤” በማለት ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

Read 9715 times