Print this page
Sunday, 18 March 2018 00:00

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ለሳምንት ያህል ተካሄደ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(48 votes)

 አዲስ ጠ/ሚኒስትር በመጪው ሳምንት እንደሚመረጥ ይጠበቃል


     ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ከስልጣናቸው እንደሚለቁ ከገለፁ አንድ ወር ቢሆናቸውም፣ ኢህአዴግ እስካሁን የሚተካቸውን ሹም አልመረጠም፤ ባለፈው እሁድ የተጀመረው የስራ አስፈፃሚው ስብሰባም እስከ ትላንት ድረስ አለመጠናቀቁ ታውቋል፡፡
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣን ለመልቀቅ ለኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታወቁት፣ የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢህአዴግ ም/ቤት ስብሰባ ተቀምጦ፣ ቀጣዩን የግንባሩን ሊቀ መንበርና የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስተር ይመርጣል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ከወር በኋላም ግንባሩ ተተኪያቸውን  አልመረጠም፡፡
ባለፈው እሑድ መጋቢት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. የተጀመረው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ፣ የኢሕአዴግ ም/ቤት ስብሰባ ባሳለፍነው ሳምንት እንደሚቀጥል ቢጠበቅም፣ የሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ እስከ ትላንት ደረስ ገና በመካሔድ ላይ እንደነበር ታውቋል፡፡
የኢሕአዴግ ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ሺፈራው ሽጉጤ፣ ከአምስት ቀናት የሥራ አስፈፃሚው ስብሰባ በኋላ ከትላንት በስቲያ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፤ የአባል ድርጅቶቹ የአፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ በስኬት ተከናውኗል፡፡ የአንድ አባል ድርጅት ሪፖርትም በትላንትናው ዕለት እንደሚታይ ጠቁመዋል፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነውን የግንባሩን ሊቀመንበር በቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ ላይ በሚደረገው የኢህአዴግ ም/ቤት ስብሰባ እንደሚመረጥ የጠቆሙት አቶ ሺፈራው፤ በሥራ አስፈፃሚው ውሳኔ ዙሪያም እንደሚወያይ አመልክተዋል፡፡
አባል ድርጅቶቹ ለግንባሩ ሊቀመንበርነት እጩዋቸውን ያቀረቡ ሲሆን የም/ቤቱን አብላጫ ድምፅ ያገኙ እጩዎች በሊቀ መንበርነትና በምክትል ሊቀ መንበርነት እንደሚሠየሙ የኢህአዴግ መተዳደሪያ ደንብ ይገልፃል፡፡ የግንባሩ ሊቀመንበርም የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ ይይዛል፡፡

Read 11191 times