Sunday, 18 March 2018 00:00

የአዕምሮ ቋንቋም ሆነ ዋጋ ነፃነት ነው

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

… መንገድ መዝጋት፣ ኢንተርኔት መዝጋት፣ ጉሮሮ መዝጋት፣ ባንክ ቤት መዝጋት፣ ጋዜጣ መዝጋት ከሚታየው በላይ የሆነ ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ … ሁሉም “አእምሮን ለመዝጋት” የሚደረጉ የማሸማቀቂያ እርምጃዎች ናቸው። … ነፃነትን ዘግቶ አእምሮን መክፈት
አይቻልም፡፡
            
    “የገንዘብ አገልግሎት፤ በጊዜ እና በቦታ (Time and Space) ላይ እሴትን ማንሸራሸር ነው፡፡ ገንዘብ የእሴት ማንሸራሸሪያ ሚዲየም ነው፡፡ ይኼ አገልግሎቱ ደግሞ ከፍላጎት ልውውጥ ጋር አንድ መሆኑን በቀጥታ ወደ መነሻው ሄደን ማግኘት እንችላለን” ይላል፤ ሉደዊግ ቮን ሚስስ (Ludwing Von Mises)
ይኼንን የቪየና ልሂቅ ሃሳብ ከፃፈው ጥራዝ (The Therory of Money and Credit) ላይ የነጠቅሁት የገንዘብን ምንነት ለመተንተን አይደለም፡፡ ከገንዘብ በበለጠ “Medium” የሚለውን ጭብጥ መረዳት ሁሉም ሚዲየሞች በምን ቋንቋ እንደሚናገሩ መረዳትም ነው፡፡ እሱ ይበልጣል፤ ወይንም ይቀድማል፡፡
ቋንቋ ሚዲየም ነው፡፡ ሀሳብን የማንሸራሸሪያ ሚዲየም፡፡ መንገድ ሚዲየም ነው - ከ “ሀ” ተነስቶ ወደ “ለ” ደርሶ ለመመለስ ያገለግላል፡፡ … ገንዘብ ሚዲየም ነው፤ ሁለት እሴቶች በተመን ተግባብተው መለዋወጥ የሚችሉበት ቋንቋ እንደ ማለት ነው፡፡ … ባህል “ሚዲየም” ነው፤ አንድ ህዝብ ተግባብቶ በአንድ ስፍራ ላይ መኖር የሚችልበትን ውል ይፈጥራል፡፡ … ስለዚህ ሚዲየምን በጥቅሉ መረዳት ይቀድማል ለእኔ፡፡
የመጀመሪያዎቹ ጋዜጠኞች ነጋዴዎች ነበሩ ይባላል፡፡ ይኼ አሉባልታም ሳይሆን ምክኒያታዊ የሚመስልም ነገር ነው፡፡ ነጋዴ በመንገድ አማካኝነት ከ “ሀ” የገዛውን እቃ ወደ “ለ” ወስዶ ይሸጣል፡፡ በመንገድ ሚዲየም አማካኝነት የገንዘብ ሚዲየምን ተጠቅሞ እሴት በተለያየ ስፍራ ላይ የያዙ ህዝቦች እንዲለዋወጡ ያደርጋል፡፡ እሴት ሲለዋወጡ በተጨማሪ የአንዱን ህዝብ ዜና ወደ ሌላው ይዞም ይመለሳል፡፡ …
አዲስ ሚዲየም መፍጠር ወይንም የነበረውን ሚዲየም መቆጣጠር የሀይል ምንጭን እንደ መቆጣጠር ነው፡፡ ቋንቋን ከፈጠረው በላይ በተገቢ ሚዲየም አስገብቶ የተገለገለበት በእሴትም ሆነ በኃይል የበለጠ ስልጣን ያለው ነው፡፡
ትንሽ ቀደም ሲል የዊኪ ሊኩ መስራች “መረጃን ይፋ በማድረግህ የአለምን ፀጥታና የፖለቲካ ሚዛን የበጠበጥክ ይመስልሃል ወይ” ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው መልስ፤ ብዙ ሳይንቲስቶች ስለ ፈጠሩት ፈጠራ የሞራል ጥያቄ ሲነሳባቸው የሚመልሱትን አይነት ነው። “እኔ የፈጠርኩት መንገዱን ነው” ነበር ያለው አሳንጅ፡፡ “እኔ መንገዱን ነው የፈጠርኩት፤ በመንገዱ ተጉዞ አንድ ሰው ህይወት ሊያድን ይችላል … ወይንም በመንገዱ ተጉዞ ህዝብ ሊፈጅ ይችላል። መንገዱ ለሁለቱም አንፃር ተጠያቂ ሊሆን አይችልም” ነበር ያለው፡፡
ሚዲየሞች ሁሉ መንገዶች ናቸው፡፡ መንገዶች ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህሪ ጋር ሲዳበሉ ነው መልካምም ሆነ እኩይ አንፃርን የሚይዙት፡፡ መጓዣውን ሚዲየም ያልጨመረ ምንም አይነት ጉዞ የለም፡፡ የድምፅ ባህርይ ከሚጓዝበት ሚዲየም ውጭ ተጨባጭ ትርጉም የሚሰጥም ተፅዕኖ የለውም፡፡ ድምፅ እርግብግቢት ነው። ብርሃንም እርግብግቢት ነው፡፡ ብርሃን ከድምፅ መፍጠኑ የሚታወቀው በሚዲየም ውስጥ ከሚያደርገው ጉዞ አንፃር ነው፡፡
የሰው ልጅ አእምሮ በአራት መሰረታዊ ሚዲየም ነው እውነታን የሚረዳው፡፡ ገብቶ መተርጎም የሚችለው በአራት አንፃር ነው፡፡ በጊዜ፣ ቦታ፣ ህልውና (being)፣ እና ግንኙነት፡፡ በጊዜ፣ በቦታ፣ በህልውና እና በማገናኘት ካልሆነ አእምሮ ማሰብ ወይንም እውነታን መረዳት አይችልም፡፡ የአእምሮ ቋንቋ በእነዚህ ሚዲየም መልክ የተገለፀ ነገርን ነው መተርጎም የሚችለው፡፡
ህግ መንገድ ነው፤ አግባብ የሆነውን ካልሆነው ለይቶ፣ አንድ ግለሰብ በስርዓት ውስጥ የሚጓዝበት መንገድ ነው። መንገድ የሚያሰፉ ህጎች አሉ፡፡ መንገድ የሚያጠፉም እንደዚሁ፡፡ … ጉሮሮ መንገድ ነው፡፡ አፍን ከሆድ እቃ ወይንም አፍና አፍንጫን ከመተንፈሻ ሳንባ የሚያገናኝ መንገድ ነው፡፡ የዚህ መንገድ ባለቤት ራሱ ግለሰቡ መሆን ቢኖርበትም ጉልበት ያለው ግን ከውጭ ሆኖ የሱን ጉሮሮ የመክፈትና የመዝጋት አቅም አለው፡፡ እንዲያውም በራሱ ጉሮሮ፣ ስለ ራሱ ጤና የሚያውቁለት ብዙውን ጊዜ ሌሎች ናቸው፡፡ “አውቅልሃለሁ” የሚሉት በግድም በውድም ሊሆን ይችላል፡፡
… መንገድ መዝጋት፣ ኢንተርኔት መዝጋት፣ ጉሮሮ መዝጋት፣ ባንክ ቤት መዝጋት፣ ጋዜጣ መዝጋት ከሚታየው በላይ የሆነ ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ … ሁሉም “አእምሮን ለመዝጋት” የሚደረጉ የማሸማቀቂያ እርምጃዎች ናቸው፡፡ … ነፃነትን ዘግቶ አእምሮን መክፈት አይቻልም፡፡
የሰው ልጅ ራሱን ለመግለፅ ሲፈልግ ሚዲየሞችን ይጠቀማል፡፡ ሚዲየሞቹን ተጠቅሞ ጥሩ እና ጠቅላይ ገለፃ ሲያደርግ፤ “ተጠበበ” ይባላል፡፡ የጥበብ ሚዲየሞች የየራሳቸው ቋንቋ አላቸው፡፡ … ከሚዲየሞቹ የሚቀድመው ግን የተጓዡ ቋንቋ ነው፡፡ ለምሳሌ ስዕል ሁለት ተፈጥሮዎችን ያማከለ ቋንቋ ነው፡፡ ፅሁፍ አብስትራክት መስተጋብሮች (relations) በአእምሮ የውበት ልክ ተቀምሮ የሚቀርብበት ቋንቋ ነው፡፡ ቋንቋው ከአእምሮ ጋር ሲሰምር “ውበት” ይሆናል፡፡
አእምሮ ዋናው መንገድ ነው፡፡ አእምሮን መክፈት ማለት … ከአእምሮ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሚዲየሞችን በጠቅላላ (along with their endless possibilities) መክፈት ማለት ነው፡፡ አእምሮ በጊዜ እና በቦታ ላይ በነፃነት መንሸራሸር የሚችልበትን የተፈጥሮ አቅም እንዲጠቀም በመክፈት ሁሉም ወይንም ከዛም በላይ የሆኑ አማራጮች እንዲንሸራሸሩ “ነፃ” መልቀቅ ነው፡፡
“ፎን ኒሰን ገንዘብ የእሴት ማንሸራሸሪያ ሚዲየም” ነው ቢሉም እኔ ግን ገንዘብ እሴት ሆኖ መንሸራሸር የሚችለው ራሱ አእምሮ እሴትን እንዲፈጥር ነፃ ሆኖ ሲለቀቅ ነው እላለሁ፡፡ በማይሰራ አእምሮ አማካኝነት የሚሰራበት ገንዘብ፤ ዞሮ ዞሮ ውጤቱ ብልፅግና ሳይሆን ቀውስ ነው፡፡
ድምፅ በሌለበት ስለ ሙዚቃ መረዳት እንደማንችለው፣ ነፃነት ሳይኖር የአእምሮ እሴትን ወደ ሌላ ሚዲየሞች ወይንም አማራጮች መመንዘር አንችልም፡፡ አእምሮ ቅድመ ሚዲየም (“a prior”) ነው፡፡
እና መጨረሻ ላይ መንገዶችን እንቆጣጠራለን የሚሉ ባለስልጣናትን “አእምሮ ነፃ ሳይሆን መንገድ ቢከፈትም ድሮውኑ አይጠቅምም ነበር” ማለት እፈልጋለሁ። አእምሮው ውስጥ ብርሃን እንዳይለኩስ የተከለከለን ሰው፤ በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ቤቱንና ሰፈሩን ብታጥለቀልቅለት አይጠቅመውም፡፡
አእምሮ መሰረታዊ ሚዲየም ነው፡፡ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ይኼንን ሚዲየም በፖለቲካ ያለ ሰውየው ፈቃድ ከውጭ መቆጣጠር ይቻላል፡፡ አእምሮውን በአግባቡ እንዳይገለገል ተገድቦ ያደገ ሰው፤ የገንዘብን አገልግሎት በጊዜ እና ቦታ ሚዲያው ውስጥ በአግባቡ ያንሸራሽራል ብዬ ለማመን አልችልም፡፡
እኔ ፎን ኒሰን የሚለኝን ለመስማት መጀመሪያ አእምሮዬ ነፃ መውጣት ነበረበት፡፡ … በተበላሸ መኪና ውስጥ ቁጭ ብዬ ሩቅ፣ በጎዳናው ላይ ስለ መጓዝ እንደ ማሰብ ነው፡፡ “ስለ ገንዘብ ትርጉም እና አገልግሎት” አሁን ላይ እያለሁ ማወቅ ብፈልግም ነፃነት ያጣ አእምሮዬ አይፈቅድልኝም። … የእኔ አእምሮ እንዳይሰራ የሚከላከሉት በአእምሮ ንቃት ደረጃ ነፃነታቸውን የተቀዳጁ አይደሉም። “እውር ባሮች በጨለማ ውስጥ እርስ በራሳቸው እና ከራሳቸው ጋር ሲታገሉ” … የሚለውን ኮንሰፕችዋል ስዕል “ነፃነት የማያውቁ ነፃ አውጪዎችን” ችግር ይገልፃል፡፡
የአእምሮ መንገድ ሳይከፈት ስለ ሌላ ሚዲየም የማሰቢያ መንገድ ፈፅሞ የለም፡፡ አእምሮን የሚከፍተው ነፃነት ብቻ ነው፡፡ ሌላው ሚዲየም ከዛ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ አማኞች መንፈሳዊ “Currency” ደም ነው ይላሉ፡፡ እኔ ደግሞ የአእምሮ ቋንቋም ሆነ ዋጋ ነፃነት ነው እላለሁኝ።  

Read 2297 times