Sunday, 18 March 2018 00:00

የቅኔና የፍልስፍና ፉክክር (፪)

Written by  በካሣሁን ዓለሙ
Rate this item
(0 votes)


    “--ሶቅራጥስ ግን በምልዓተ ዓለሙ (Universe) ጉዳንጉድ ውስጥ ገብቶ ከመዛቆን ይልቅ የራስን ማንነት ማወቅ ይቀድማልና መጀመሪያ ‹የራስህን ዐለማወቅ ዕወቅ› በማለት እና ዕውቀትን በተጨባጭ የእሰጥ አገባ (Dialogue) ስልት ማንጠር እንደሚገባ በተግባር በማሳየት፣ በትምህርቱም ቅኔን ጥንት ከነበረው ልዕልና አዋርዶ ከተረት ጋር ተፎካካሪ አድርጎታል፡፡--”
ካሣሁን ዓለሙ
(የ‹ቅኔ ዘፍልሱፍ› መጽሐፍ ደራሲ)
ባለፈው ሳምንት ቅኔና ፍልስፍና በመደነቅ መሠረታቸው እና የተፈጥሮን (የእውነትን) ምሥጢር ለመግለጥ በመጣራቸው አንድነት ቢኖራቸውም በስልታቸው ቅኔ ሰምና ወርቅን (ኅብርነትን)፣ ፍልስፍና ደግሞ አመክንዮን (ምክንያታዊነትን) በመመርመሪያነት ስለሚወስዱ መለያየታቸውን፤ ኹለቱም ግን የተፈጥሮን ቅንብር የሚያመጥኑ መሠረታዊያን ጥበባት መኾናቸውን፣ ተመልክተን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ የቅኔን ጥንታዊ ጥበብነትና ከሶቅራጥስ ጀምሮ በምዕራባዊያን ፈላስፎች ዘንድ ያለውን የዕይታ ኹኔታ በጥቅሉ ለማየት እንሞክራለን፡፡
የቅኔ ጥበብ ጥንታዊነት
የቅኔና የፍልስፍናን ታሪካዊ ዳራ ስንፈትሽ፣ የፍልስፍና ውልደት ሳይበሠርና የሰው ልጅ ዕውቀት በትምህርት ሥርዓት ዘርፍ (ቅርንጫፍ) ሳይከፋፈል በፊት ቅኔ በብቸኝነት ኹሉንም ትምህርት በአንድነት አምቆና ከተፈጥሮ ኅብርነት ጋር ተናቦ (አናቦ) የሚገኝ ጥበብ ነበር፤ ተመራማሪዎቹም ይኽ የዚኽኛው የትምህርት ዓይነት ነው፤ ያኛው ከዚያኛው ጋር ይያያዛል/ይለያል በማለት አይከፋፍሉም ነበር፡- ከአርስጣጣሊስ (አርስቶትል) ጀምሮ ነው ዕውቀት በክፍል በክፍል እየተመደበ ድንበር የተበጀለት። በጥንት ዘመን የአብዛኞቹ ጠቢባን የምርምር ማዕከልም ከተጻፈ ላይ መፈለግ ሳይኾን የተፈጥሮን ህላዌና የፍጥረታትን መስተጋብር ማስተዋልና መመርመር ነበር፡፡ ይኽንን ነው የሰው ልጅ በፊደላት ቀርጾ፣ በዚያም ወደ ጽሑፍ ገልብጦ ተወራራሽ ጥበብ ያደረገው፡፡ ተፈጥሮ ደግሞ በኅብርነት፣ በዕምቅነት፣ በዜማ… ቅኔ የተሠራች መኾንዋን ትመሠክራለች፤ ምስክርነቷን ያስተዋለና በአግባቡ ያዳመጠ ባለቅኔ ይኾናል፡፡ ስለኾነም በየትኛውም ሥፍራ ቢኾን በጥንት ጊዜ  የሰው ልጅ የዕውቀቱ መሠረት ቅኔ ነበረ፡፡
ከተጻፉ የሰው ልጆች ጥበባት መካከልም በየትኛውም ሥፍራ ቅኔ (ከግጥም ጋር ተያይዞ) በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡- ፍልስፍና ከቅኔ ጋር ሲነጻጸር ‹መጤ› ዕውቀት ነው፡፡ ምልዓተ-ዓለምን (Universe) በህልውና አስገኝቶ በሚጠብቀው ፈጣሪ፣ የምሥጢር ቋት በኾነው የሰው ልጅና በቅኔ በተሠራችው ተፈጥሮ መካከል ባለው መስተጋብር የቅኔ ጥበብ ምሥጢር ከሳች በመኾን ስለሚያገለግል የሰው ልጅ የፈጣሪውን ሥራ ለማወደሻና የተፈጥሮን ምሥጢር ለመግለጫ ጥበብ አድርጎ መጠቀም የጀመረው ቅኔን ነው፡- ከጥንቱ ከመሠረቱ፡፡
ቪኮ የተባለው ጣሊያናዊ ፈላስፋ፤ የሰው ልጅ በማኅበረሰብ ተደራጅቶ የሐሳብና የባህል መስተጋብር ማድረግ የጀመረው በቅኔ መኾኑን ይሞግታል (Donald P. Verene (1970), Man and Culture: A Philosophical Anthology, pp 71-75)፡፡ ብርሃኑ ገበየሁም ‹ግጥም በሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፍ፣ በዕለት ከዕለት ሕይወት የሚዘወተር የቋንቋ አጠቃቀም ጥበብ› (ብርሃኑ ገበየሁ፣ የአማርኛ ሥነ ግጥም፣ ገጽ 5) መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ይኽ አገላለፅ ለግጥም የተጠቀሰ ቢኾንም ከቅኔ ጋር የተያያዘ ነው፡- እንኳን ድሮ አሁንም ኹለቱን ግጥምና ቅኔን አንድ አድርጎ መግለጽ የተለመደ ነውና፡፡
በጥንት ሥልጣኔ በፈለቀባቸው ሀገራት ቅኔ የዕውቀቶች መሠረት ነበር እንዳልነው፣ ይህ አባባለችን በብዙ ጥንታዊያን አገሮች ተንፀባርቆ እንደሚገኝ መታዘብ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በምሥጢራዊ ጥበባት (በዚኽ አገባብ ምሥጢር ማለት አንድም ገና ያልተረዱት፣ በደረጃ ያልደረሱበት ጉዳይ/ነገር ማለት ነው፤ አንድም ከጥልቀቱ የተነሣ ተመራምረው ሊደርሱበት የማይችሉት ማለት ይኾናል) የበለጸጉት ጥንታዊያን ግብፆች፣ ሜሶጶጣሚያኖች፣ ቻይኖችና ሕንዶች፣ ግሪኮች፣ ሮማዊያን፣ እሥራኤላዊያን፣ ከዚያም ዐረቦች ሐሳባቸውን በቅኔ በመግለፅና በመጻፍ የተካኑ ነበሩ፡፡ በጥንታዊ ግብፅ ሥልጣኔ ፒራሚዶች ላይ ተጽፈው የተገኙ ጽሑፎች ምሥጢር ያዘሉ ቅኔዎች ናቸው፡፡ ይህም ልክ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የዶግማ ትምህርት በምሥጢራዊ ደረጃዎች እንደሚከፋፈለው (ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ቁርባንና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን በሚል) በጥንታዊ ግብፅ ካህናትም የዕውቀት የምሥጢር ደረጃ ክፍፍል ነበራቸው (ልክ እንደ አገራችን የአስማትና የመድኃኒት ጥበባት የጥንታዊ ግብፅ ሊቃውንት እነሱ ብቻ የሚያውቁት፣ ከካህናቱም መካከል የተወሰኑት ብቻ በሚሥጢር የሚጠብቁት)፤ መልዕክቶችንም የሚያስተላልፉት በተሸፈነ (ምሥጢር የማያውቅ ሰው እንዳይገባው በማድረግ) ስለነበር የግብፅ ካህናት በሰምና ወርቅ ጥበብ የተካኑ እንደነበሩ መገመት ይቻላል፤ ለዚያም ነው የግብፅ ሊቃውንት የምሥጢር ካህናት (Mystery Priests) ይባሉ የነበሩት፡፡ ለዚኽ አንድ ምሳሌ እስቲ እንመልከት፡፡
 በጥንታዊት ግብፅ በ3ኛው ሥርወ መንግሥት ዘመን (2668-2649 ከክ.ል.በ) ኢምሆጠጵ (Imhotep)፣ ሆር-ዠድ-ኢፍ (Hor-Djed-Ef)፣ ካገምኒ (Kagemni) እና ጵጣህ-ሆጠጵ (Ptah-Hotep) በመባል የሚታወቁ ፈላስፎች ነበሩ፣ ሊቅነታቸውም በፕራሚድ ላይ ተጠቅሶ የሚገኘው በቅኔ መልክ ነው፡፡ እንዲህ ይላል የእንግሊዘኛው ትርጉም፡-
Books of wisdom (i.e. philosophy) were their pyramids,
And the pen was their child . . .
Is there anyone here like Hor-Djed-Ef?
 Is there another like Imhotep?
They are gone and forgotten,
But their names through their writings cause them to be remembered.
‹የጥበብ መጽሐፎች (ፍልስፍና) ፒራሚዶቻቸው ነበሩ፤
ብዕሩም ልጃቸው ነበር፤
እውን ሆር-ዠድ-ኢፍን የመሰለ ሰው ይኖራል?
ኢምሆጦጵን የመሰለስ ሌላ ይገኛል?
እነሱም  ከዚኽ ዓለም ያልፋሉ፤ ይረሳሉ፤
በሥራቸው አማካይነት ግን ስማቸው ሲታወስ(ሱ) ይኖራል(ሉ)፡፡›
(A companion to African philosophy፣ ገጽ 35-36)  
ይኽም ለጥንታዊት የግብፅ ሊቃውንት የሚገነቧቸው ፒራሚዶች የምሥጢራት መዝገቦቻቸው መኾናቸውን ይመሰክራል፤ ሐሳባቸውን ይገልጹ የነበረው በቅኔ መኾኑንም መረዳት ይቻላል፡፡ አጠቃላይ በፕራሚዶች ላይ ተጽፈው የሚገኙት የሚሥጢር ቃላትም በቅኔያዊነት የተቀመጡ ናቸው፤ ለዚያም ነው ምሁራኑ ምሥጢራቸውን ለማወቅ በጥናት የተጠመዱት፡፡
ከግብፆች ሥልጣኔ በኋላ የተከተሉት የሜሶጶጣሚያ፣ የሕንድ፣ የቻይና እና ሌሎች ሥልጣኔዎችን ስንመለከትም ምሥጢራዊ ጥበባት የዕውቀታቸው ደረጃ ማስመስከሪያዎች እንደነበሩ እንረዳለን፤ ይኽ ደግሞ የጠቢቦቻቸው ዋና ጥበብ ወደ ቅኔ ያደላ እንደነበር ማሳያ ነው፡፡ አብዛኞቹ ጽሑፎች የተመዘገቡት በቅኔ ወይም በግጥም መልክ ነው፡፡ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱሱን ዳዊትን ብንወስድ በመዝሙሩ ‹ለእግዚአብሔር ተቀኙለት› እያለ ሲዘምር ነበር፤ ጠቢቡ ሰለሞንም ሰባት የጥበብ ቤት አዕማዳትን ያቆመው በቅኔ መነጽር እንጂ በልሙጥ ዕይታ አይደለም፤ ስለኾነም እሥራኤላውያን ቅኔን ጥልቅ ስሜትንና ግንዛቤን ለመግለጫና ለጥበብ ማሳያ ያደርጉት ነበር፤ የመጽሐፍ ቅዱስ የመዝሙር (የኢዮብ፣ የሲራክ፣ የሰሎሞን፣ የዳዊት፣…) መጻሕፍትም የተቃኙት በቅኔ ነው፡፡
እንዲሁም የግሪኩ የሆሜር ቅኔዎችም ለጥንታዊ ዕውቀት ቅኔነት ምሥክር መኾን ይችላሉ፡፡ ከሆሜር ጀምሮ እስከ ሶቅራጥስ ድረስም ግሪክን ያጥለቀለቃት ዋና ጥበብ ቅኔ ነበር፤ የቅኔን ዋና ገዥነት ገልብጠው ፍልስፍናን የዘመናት የዕውቀቶች ንጉሥ እንዲኾን አድርገው በግሪክ ምድር የሾሙት ሶቅራጥስ፣ ፕላቶንና አርስጣጣሊስ ናቸው፡- በተለይ ሶቅራጥስና ፕላቶን፡፡ ይህንን ጉዳይ በቀለ ተገኝ በትርጓሜ መጽሐፉ ሲገልጽ፤ ‹በጥንቱ፣ በመካከለኛዎቹና በአዲሱ ዘመናት ቢባል ፕሌቶና አርስቶትል (አፍላጦንና አርስጣጣሊስ) በዓለም የሥልጣኔ ጎዳና ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ደንቅረውበት የአለፉት የማይነቃነቅ ዕንቅፋት ሌሎች ፈላስፎች ከደቀኑበት መሰናክል ሁሉ የበለጠ ከባድና ጎጂ ነበር፡፡› ይላል (በቀለ ተገኝ፣ 1985፣ የምዕራባዊያን ፍልስፍናና ሥልጣኔ ታሪክ (፩)፣ ገጽ 273)፡፡ ስለዚኽ በጥንት ዘመናት ከፍልስፍና ይልቅ ቅኔ እውነተኛ ስሜትን መግለጫና መመሰጫ፣ የኹሉም ጥበባት ሊቀመንበር ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡
የቅኔ ዕይታ ከሶቅራጥስ ጀምሮ   
የመፈንቅለ ቅኔ ዋና ቀስቃሽና ተዋናይ አበ ሊቃናት ሶቅራጥስ ነው፤ ከእሱ ጀምሮ ያለው የቅኔ ግንዛቤና አስተምህሮ በንትርክ የተሞላ ነው፤ ይህንንም በኹለት ዕይታዎች በመቃኘት መመልከት ይቻላል፡- (፩) ከታሪካዊ ዳራው አንጻር እና (፪) ፈላስፎቹ ከሚሰጡት ደረጃ አኳያ፡፡ የቅኔን ታሪካዊ ዳራ በሦስት ደረጃዎች መክፈል እንችላለን፡- (፩) ከጥንት እስከ ሶቅራጥስ ድረስ ያለው (ቅኔ የዕውቀቶች ሊቀመንበር የነበረበት) ዘመን፣ (፪) ከፕላቶን እስከ አውጉስጢን ድረስ ያለው (ቅኔ ከፍልስፍና ጋር ጦርነት ውስጥ የገባበትና በተረትነት የተጣለበት) ዘመን እና (£) ከአኳይነስ ጀምሮ እስከ ሄደገር ድረስ ያለው (የቅኔ ልዕልና ትኩረት ያገኘበት) ዘመን በሚል ማጠንጠኛ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ከሄደገር በኋላ ያለው ዘውግ የተደበላለቀ ቢመስልም ዘመኑ የፍልስፍና እና የቅኔ አታካራ ዐዲስ የዕውቀት ዕይታን እንዳመጣ እየተሞገተበት ያለ ዘመን ነው፤ ‹ፍልስፍና እና ቅኔ መጣላት ሳይኾን የእርስ በርስ ተዋሕዶ ነው ያደረጉት› የሚል መከራከሪያ አምጥተዋል፡- ፍልሱፋኑ፡፡
ከሶቅራጥስ በፊት የነበረውን ዘመን ቅኔ ብቸኛ የዕውቀት መሪ የኾነበት ዘመን ነበር፡፡ ቅኔ የግሪኮችን አእምሮ ተቆጣጥሮም ቅኝ ግዛቱ አድርጓቸው ነበር። እንዲሁም ቅኔ ከተፈጥሮ የተቀዳና የአማልክት ድምፅ በመኾን የሚሰማ ጥበብ እንደኾነ ይታሰብ ነበር፡፡ ሶቅራጥስ ግን በምልዓተ ዓለሙ (Universe) ጉዳንጉድ ውስጥ ገብቶ ከመዛቆን ይልቅ የራስን ማንነት ማወቅ ይቀድማልና መጀመሪያ ‹የራስህን ዐለማወቅ ዕወቅ› በማለት እና ዕውቀትን በተጨባጭ የእሰጥ አገባ (Dialogue) ስልት ማንጠር እንደሚገባ በተግባር በማሳየት፣ በትምህርቱም ቅኔን ጥንት ከነበረው ልዕልና አዋርዶ ከተረት ጋር ተፎካካሪ አድርጎታል፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት በቀጣይ ዘመናት ቅኔ ተፈጥሯዊነቱን ለማስጠበቅ ቢፍጨረጨርም ‹የእነ ደሳለኝ› መፈንጫ፣ ከዚያም ባለፈ እንደተረት መተረኪያ መንገድ ኾኖ ከመቆጠር አላመለጠም (ያረጀ ሰው ተረት ያበዛል ብለው ነዋ!)፡፡
ኾኖም ግን በቶማስ አኳይነስ ቆስቋሽነት በጂያምባቲስታ ቪኮ መሪነት ቅኔን ለማንገሥ የመፈንቅለ ፍልስፍና ሙከራ ተደርጓል፤ በዚህ ሙከራም ሙሉ ነፃነት ባይገኝም ቅኔ ታሞ ከተኛበት ሆስፒታል ‹አለሁ አልሞትኩም› ብሎ በመነሣት አገግሞ ለመነሣት ችሏል፡፡
ይሁንና በጥንቱ የተረትነት ፍረጃ የተነሣ የቀድሞውን ሥልጣን ስላጣ፣ እንደ የፊውዳል ሥርዓት ተቆጥሮ ከንግሥና ‹ሲንቦልነት› ያለፈ ከፍልስፍና ጋር የሥልጣን ተካፋይና ተፎካካሪ ጥበብ የመኾን ዕድል አልተሠጠውም፡፡ ኾኖም በቪኮ የተጀመረው ቅኔን ከፍ ከፍ የማድረግ ጥረት በእነ አማኑኤል ካንት፣ በእነ ሄግል፣ በእነ ኬርኬርጋድ፣ በእነ ኒቼ፣ በእነ ሄደገር፣… ቀጥሏል።  በዚህ የተነሣ ከቪኮ በኋላ ያለው የቅኔ አስተምህሮም ቅኔን ወደ ፍልስፍና ከፍ ከፍ የማድረግ፣ የቅኔና የፍልስፍና ዝምድናን ለማጠንከር ማሸማገል፣ የቅኔንም ጥበብ ወደ ጥንተ መሠረቱ ተመልሶ ለመከለስ የመሞከር ጥረት ተስተውለዋል፡፡
እነዚህን የጠቀስናቸውን ነጥቦች ዘርዘር አድርጎ በማሳየት የፈላስፎችን (ሐሳቢዎችን) መከራከሪያዎች የሚዳስስ መጣጥፍ በሚቀጥለው ጊዜ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ እስከዚያው ይቆየን! ያቆየን!

Read 3053 times