Sunday, 18 March 2018 00:00

በ”ጣናን እንታደግ” ታላቁ ሩጫ፣ ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ 1.3 ሚ. ብር፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ 200 ሺ ብር ለገሱ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

“ጣናን እንታደግ” በሚል መርህ ባለፈው እሁድ በተደረገው 7ኛው የባህርዳር ታላቁ ሩጫ ላይ ታዋቂው ባለሀብት አቶ በላይነህ ክንዴ፣ በስማቸው 1. ሚ ብር፣ በቅርቡ ባቋቋሙት ጎልደን ባስ ትራንስፖርት ስም 300 ሺህ ብር የለገሱ ሲሆን ታዋቂው አትሌት ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ 200 ሺህ ብር ለግሳለች፡፡ ገንዘቡ በአስጊ ሁኔታ እምቦጭ በተሰኘው መጤ አረም የተጠቃውን ጣና ሀይቅን ለመታደግ የተጀመረውን እንቀስቃሴ ይደግፋል ተብሏል፡፡
10.ኪ.ሜ በሸፈነው በዚህ “ጣናን እንታደግ” ሩጫ ላይ በእንግድነት የተገኘችው እውቋ አትሌት ሻለቃ ደራርቱ ቱሉም፣ በታሪክ ትልቅ ቦታ ያለው ጣና ሀይቅን ለመታደግ የበኩሌን አደርጋለሁ በማለት 200 ሺህ ብር መለገሷ ብዙዎችን አስደስቷል፡፡ በሩጫው ላይ ለሯጮች የተዘጋጁትና “ጣናን እንደታደግ” የሚል ፅሁፍ የተፃፈባቸው ቲ-ሸርቶች ገቢ እንዲሁ ለጣና ይውላል ተብሏል፡፡
በ7ኛው ታላቁ የባህርዳር ሩጫ ላይ የከተማው ስፖርት አፍቃሪዎች፣ በክልሉ የሚገኙ የአትሌቲክስ ክለቦች የተውጣጡ ሯጮች፣ ከፌደራል አትሌቲክስ የተውጣጡና ከተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተሳተፉ በርካታ ሰዎች ሩጫውን አድምቀውት እንደነበር ታውቋል፡፡ በዕለቱ የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉም ሆነ ዝግጅቱ እንዲሳካ ለተባበሩ አካላት ዋንጫና ልዩ ልዩ ሽልማቶች የተበረከተላቸው ሲሆን አሸናፊ ሯጮች የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት ማግኘታቸው ታውቋል፡፡

Read 2020 times