Tuesday, 20 March 2018 11:21

“የትውልድ አደራ” መፅሐፍ ተመረቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

በልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም የተፃፈው “የትውልድ አደራ” የተሰኘ ግለ ታሪክ መፅሐፍ በትላንትናው ዕለት በየኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ጽ/ቤት ተመረቀ፡፡ የልዑል ራስ መንገሻ ስዩምን የህይወት ታሪክ የሚተርከውን ይኼን መፅሐፍ፤ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በሥሩ በመሰረተው የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ አማካኝነት ማሳተሙ ታውቋል፡፡
በምርቃ ሥነስርዓቱ ላይ ፕ/ር ኢሜሪተስ ገብሩ  ታረቀ በመፅሐፉ ላይ አጭር ሙያዊ አስተያየት ያቀረቡ ሲሆን የደራሲው ዘመነኛ የሆኑት ደጃዝማች ወልደሰማዕት ገብረወልድ የዓይን ምስክርነት፣ ደራሲው ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ደግሞ አጭር ትውስታና ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኢሜሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ስለ መፅሐፉ በሰጡት አስተያየት፤ “መፅሐፉ የአንድ በሃያኛው መቶ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሚኒስትርነት፣ በአውራጃና ጠቅላይ ግዛት አገረ ገዥነት የረዥም ዘመን አገልግሎት የሰጡ ሹም ግለ ታሪክ ስለሆነ፤ ትልቅ ታሪካዊው ፋይዳ ያለው ነው” ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ቺሜሪተስ ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ በበኩላቸው፤ “ይህ መፅሐፍ ለታሪክ ጥናት አስተዋፅኦ የሚያደርግ ቀዳማይ ምንጭ ነው፡፡… አንደኛ፣ የመሣፍንት ልጆች አስተዳደግ ላይ ያለንን ግንዛቤ ያበለፅጋል፡፡ ሁለተኛ፣ የጠቅላይ ግዛት አስተዳደርን በሚመለከት በተለይ ለሀገራችን የልማት ታሪክ ጥናት አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ሦስተኛ፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኅብረት (ኢድኃን) አስመልክቶ የልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ዕይታን ያቀርባል” ሲሉ አስተያየታቸውን ገልፀዋል፡፡

Read 3212 times