Saturday, 14 April 2018 13:44

የአሜሪካ ኮንግረስ ያፀደቀውን የውሳኔ ሃሳብ ተቃዋሚዎች ደግፈውታል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)


        “በሀገሪቱ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል”

     ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰሞኑን በአሜሪካ የህግ መወሰኛ ም/ቤት የፀደቀውንና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲስተካከል የሚጠይቀውን HR128 እንደሚደግፉ የገለጹ ሲሆን  የውሳኔ ሃሳቡ መጽደቁ በአገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ተጨባጭ ተፅዕኖ ያሳርፋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
መንግሥት በበኩሉ፤ ”የውሳኔ ሃሳቡ ወቅቱን ያልጠበቀና ተገቢነት የሌለው” በማለት ያጣጣለው ሲሆን “የአገሪቱን ሉአላዊነት የማያከብር ነው” ሲልም ተቃውሟል፡፡
የአሜሪካንን የላይኛው ም/ቤት እና የፕሬዚዳንት ትራምፕን ውሳኔ በቀጣይነት የሚጠባበቀው HR128፤ በኢትዮጵያ ለሰብአዊ መብቶች መከበር የቆመ አስተዳደር እንዲመሰረት የሚጠይቅ ነው ተብሏል። በህግ መወሰኛ ም/ቤቱ አባላት ያለምንም ተቃውሞ የፀደቀው የውሳኔ ሃሳቡ፤ በኢትዮጵያ ባለፉት 3 ዓመታት በነበሩ ተቃውሞዎች፣ በመንግሥት የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በስፋት የሚጠቅስ መሆኑ ታውቋል፡፡  አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ ስድስት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ያቀረቡትን ማስረጃም ያካተተ ሰነድ ነው ተብሏል፡፡  
የውሳኔ ሃሳቡን አርቅቀው ያቀረቡት የኒውጀርሲ ግዛት የኮንግረስ አባል ክሪስ ስሚዝ ሲሆኑ የውሳኔ ሃሳቡን ይዘት ለኮንግረሱ (የህግ መወሰኛ ም/ቤት) ባቀረቡበት ወቅት፤ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በነበረው ተቃውሞ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እኩልነትን የጠየቁ ከ1 ሺህ በላይ ዜጎች፣ በመንግስት ያልተመጣጠነ ኃይል  መገደላቸውን ገልጸዋል፡፡
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ካሣ ተ/ብርሃን፤ ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ላይ መሆኗን በመጠቆም፤ ”ውሳኔውን ማፅደቅ ጊዜውን ያልጠበቀ ነው” የሚል ማመልከቻ ለኮንግረስ አባላቱ ቢያስገቡም ደብዳቤያቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
 ውሳኔውን አርቅቀው ለኮንግረሱ ያቀረቡት ስሚዝ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የስልጣን ሽግግር በተደረገ ቁጥር በርካታ ቃል የተገቡ ጉዳዮች ቢኖሩም በተግባር አለመፈጸማቸውን በመጥቀስ፤ የአምባሳደሩ መማመልከቻ ተቀባይነት እንዳያገኝ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
“መንግስት ተቃዋሚዎችን ለውይይት እየጠራ በጎን ስልጣኑን የማጠናከር ስራ ይሰራል” ሲሉ የወነጀሉት የኮንግረስ አባሉ፤ “ከዚህ በኋላ ይህ አይነቱ ተግባር ሊፈቀድ አይገባም” ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ በኮንግረሱ የፀደቀው የውሳኔ ሃሳብ፤ በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ይዞታ እንዲሁም የዲሞክራሲ ምህዳር፣ ከአሜሪካ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት አቋም አንፃር ተፈትሾ፣ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና እንዲደረግ የሚጠይቅ መሆኑ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ይዞታን አምርሮ የሚኮንነውና በ6 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የተደገፈው የውሳኔ ሃሳብ፤ አገር ውስጥ በሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሙሉ ድጋፍ ተሰጥቶታል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ለአሜሪካ ኤምባሲ በፃፈው ደብዳቤ፣ የውሳኔ ሃሳቡ ተገቢ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ከፀደቀ በኋላም ባወጣው መግለጫ፤ የውሳኔ ሃሳቡ በመንግሥት ላይ ጫና ያሳርፋል የሚል እምነት እንዳለው ገልጧል፡፡
መኢአድም በዚህ ረገድ ተመሳሳይ አቋም ነው ያንጸባረቀው፡፡ የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ አዳነ ጥላሁን የውሳኔ ሃሳቡ መጽደቁን ለምን እንደሚደግፉ ለአዲስ አድማስ ሲያስረዱ፤ “መንግሥት ሲፈፅማቸው ለነበሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዲሞክራሲና የፖለቲካ መድረኮች የማጥበብ እርምጃዎች እውቅና የሚሰጥ በመሆኑ እንደግፈዋለን” ብለዋል፡፡
መንግሥት ማሻሻያ እያደረግሁ ነው ቢልም፣ከዚህ በፊት የተፈፀሙ ግፍና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በቸልታ መታለፍ የለባቸውም የሚሉት አቶ አዳነ፤”በህዝብ ላይ ለደረሰ በደል ተጠያቂ አካል መኖር አለበት የሚል እምነት አለን፤ በዚህ መርህ መሰረት ለHR128 ድጋፍ እንሰጠዋለን” ብለዋል፡፡
የመድረክ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገብሩ ገብረማርያም በበኩላቸው፤ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ለተፈፀሙ በደሎች ተጠያቂ አካል ሊኖር ይገባል የሚል አቋም እንዳላቸው ጠቁመው፤ ”የውጭ አካላት በሚያደርጉት ምርመራና ይፋ በሚያወጡት ሪፖርት መሰረት፤ ለተፈፀሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ተጠያቂዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው” ብለዋል፡፡ በዚህም መድረክ ለውሳኔ ሃሳቡ ሙሉ ድጋፍ ይሰጠዋል ብለዋል፡፡
ኢራፓ በበኩሉ፤ ይህ የውሳኔ ሃሳብ መንግስትን ወደ ድርድር አስገድዶ ሊያመጣው ይችላል በሚል እሳቤ እንደሚደግፈው አስታውቋል፡፡ የውሳኔ ሃሳቡ የሰላማዊ ትግል አካል ነው ብሏል፤ ፓርቲው፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ፤ በኢትዮጵያ ይፈፀማሉ ያሏቸውን የመብት ጥሰቶች ለተለያዩ የአሜሪካ ባለስልጣናት ሲያስረዱ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለስልጣናቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን የቆሙበት እርምጃ ነው ብለዋል፡፡ “ውሳኔው በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችን ለማስፈታት እንዲሁም የፖለቲካ ውይይት እንዲደረግ የሚያስገድድ በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ የምንመለከተው ነው” ይላሉ፤ ሊቀ መንበሩ፡፡
“ልማታችን እውቅና ተሰጥቶታል እንደሚባለው ሁሉ፣ አሁን የሰብአዊ መብት ረገጣውም እውቅና ተሰጥቷል፤ይህ ትልቅ ውጤት ነው፤መንግስት ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብር ተጽዕኖ ያሳርፋል” ብለዋል - አቶ የሸዋስ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ”የውሳኔ ሃሳቡ እምብዛም ለውጥ የማያመጣና ወቅቱን ያልጠበቀ ነው” ብሎታል፡፡  

Read 2996 times