Saturday, 07 April 2018 00:00

እንግሊዝ ከኢትዮጵያ የተዘረፉ ቅርሶችን በረዥም ጊዜ ውሰት ልትሰጠን ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ቅርሶቹን ሙሉ ለሙሉ ለኢትዮጵያ መመለስ የማይታሰብ ነው ብላለች

    እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ተዘርፈው ከተወሰዱ ጥንታዊ ቅርሶች መካከል አንድ የወርቅ አክሊልና የጋብቻ ቀሚስ በረጅም ጊዜ ውሰት ለኢትዮጵያ ልትሰጥ ነው ተብሏል፡፡
ከ150 ዓመት በፊት በተካሄደው የመቅደላ ጦርነት ወቅት በ15 ዝሆኖችና 200 በቅሎዎች ተጭነው ወደ እንግሊዝ የተወሰዱ ቅርሶችን ሙሉ ለሙሉ መልሶ ለኢትዮጵያ መስጠት የማይታሰብ መሆኑን የገለፀችው እንግሊዝ፤ የተወሰኑትን በረጅም ጊዜ ውሰት ለጉብኝት ፕሮግራም እሰጣለሁ ማለቷን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
 በውሰት ይመለሳሉ ከተባሉት መካከል አንድ የንጉስ የወርቅ የራስ አክሊልና በጥሩ ጥልቅ የተዋበ የሴቶች የጋብቻ ቀሚስ እንደሚገኝበት የቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም ዳይሬክተር አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትና የቅርስ ተቆርቋሪዎች እ.ኤ.አ በ2007 በመቅደላ ጦርነት የተዘረፉ ቅርሶች እንዲመለሱላቸው መጠየቃቸውን ያስታወሱት የሙዚየሙ ዳይሬክተር፤ ሙሉ ለሙሉ መመለስ የማይሞከር ነው፤ ነገር ግን ቅርሶቹን ለጎብኚዎች ለማሳየት ከፈለገች እናውሳታለን ብለዋል፡፡
ሰሞኑን በዚያው በሃገረ እንግሊዝ በሚካሄደው “የመቅደላ ማስታወሻ” የቅርስ ማሳያ ሥነ ስርዓት ላይም በውሰት የተሰጡት ከ20 በላይ ቅርሶች ለህዝብ ይፋ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የመቅደላ ቅርሶች አስመላሽ ቅስቀሳ ቡድን መስራች ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ፤እንግሊዝ በረጅም ጊዜ ውሰት ቅርሶቹን ለመስጠት መፍቀዷ እንዳስደሰታቸው መገልፃቸውን ዘ ጋርድያን ዘግቧል፡፡

Read 2065 times