Sunday, 01 April 2018 00:00

ተቃዋሚዎች፤ የዲሞክራሲና የፖለቲካ ማሻሻያ እንደሚደረግ ተስፋ አላቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ጠ/ሚኒስትሩ፤”ተቃዋሚዎችን” የገለጹበት መንገድ በብዙዎቹ ፖለቲከኞች ተወዶላቸዋል


     ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግርና ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በሃገሪቱ የዲሞክራሲና የፖለቲካ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡  
ባለፉት ዓመታት በኢህአዴግ ተስፋ ቆርጠው መቆየታቸውን የሚናገሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤አዲሱ የጠ/ሚኒስትር አስተዳደር የፖለቲካ ማሻሻያዎችን ያደርጋል ብለው እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ተቃዋሚዎችን አስመልክቶ፤ ”ከኢህአዴግ ውጭ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነጽር፣ እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣አማራጭ ሃሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ፣አገሩን እንደሚወድ የዜጎች ስብስብ ነው” በሚል የገለጹበት መንገድ፣የብዙዎቹን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ልብ የገዛ ይመስላል፡፡ ለጠ/ሚኒስትሩ ድጋፋቸውን ገልጸዋል - የተቃዋሚ መሪዎች፡፡       
ሰማያዊ ፓርቲና ኢራፓ ባወጡት መግለጫ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  እንዲነሣ፣ የፍትህና የምርጫ ቦርድ ተቋማት የለውጥ ማሻሻያ እንዲደረግ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር ለአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን መኢአድና ኦፌኮ በበኩላቸው፤ የጠ/ሚኒስትሩን ንግግሮች ወደ ተግባር ተለውጠው ማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ ፓርቲዎች አመራሮች ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በአዎንታ ቢቀበሉትም የቃላቸው ተፈፃሚነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡  
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ተከትሎ የአቋም መግለጫውን ያወጣው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ በበኩሉ፤ዶ/ር አብይ በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን የጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣንና ሃላፊነት ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት፣ በሙሉ አቅማቸው እንዲጠቀሙበት ጠይቋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በኢህአዴግ ውስጥ ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸውን አመራር ግለሰቦች በከፍተኛ ጥንቃቄ ከጎናቸው በማሰለፍ፣ በእጃቸው የገባውን ወርቃማ አጋጣሚ እንዲጠቀሙበት የመከረው ኢራፓ፤ የሃገሪቱን የህልውና ስጋት ለመቅረፍ አግላይ ያልሆነ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁሞ፣ከድርጅታዊ ህልውና ይልቅ ለሃገርና ለህዝብ ቅድሚያ እንዲሰጡም አሳስቧል - ጠ/ሚኒስትሩን፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሚዛን የሚደፋና ውሃ የሚቋጥር ነው ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ነገር ግን ቃል የተገቡ ጉዳዮች ወደ መሬት ወርደው ይተገበራሉ በሚለው ላይ ጥርጣሬ እንዳለው አልሸሸገም፡፡ በሌላ በኩል፤አዲሱ ጠ/ሚኒስትር በተለይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ በሃገር ውስጥም በውጪም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራትን በጠረጴዛ ዙሪያ በማቀራረብ በሚደረግ ድርደር፣የህዝብ መንግስት መቋቋም እንዲችል መጣር አለባቸው ብሏል - ፓርቲው፡፡
“የሃሳብ ልዩነት መርገም አይደለም” ሲሉ መናገራቸውን የጠቀሰው ፓርቲው፤ይህን ቃላቸውን ይተገብሩ ዘንድ በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በሙሉ እንዲፈቱ ጠይቋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ፣ በግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች መልሰው እንዲቋቋሙ፣ወንጀሉን የፈጸሙ የመንግስት ባለስልጣናትም ለህግ እንዲቀርቡ ሰማያዊ ፓርቲ አበክሮ ጠይቋል፡፡ የፍትህ ተቋማትና ምርጫ ቦርድ ለዲሞክራሲና ለፍትህ እድገት ወሣኝ በመሆናቸው እንደገና በአዲስ መልክ መዋቀር እንዳለባቸውም አሳስቧል - ፓርቲው፡፡
ከጫና የፀዳ ነጻ የመገናኛ ብዙኃንን መፍጠር የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ያለው ሰማያዊ፤ነፃና ገለልተኛ የሚዲያ ተቋማት በሌሉበት ህዝብን ማገልገል ከቶውንም አይቻልም ብሏል፡፡
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር በተግባር የመተርጎሙ ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ፓርቲያቸው በሃገሪቱ የስልጣን ሽግግር ተደርጓል ብሎ እንደማያምን የጠቆሙት አቶ ሙላቱ፤ “እኛ ሽግግር የምንለው ፓርቲ በፓርቲ ሲተካካ እንጂ በአንድ ፓርቲ ውስጥ የሚደረግ የአመራር ለውጥን አይደለም” ብለዋል። “እኛ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የምንጠብቀው በቀጣይ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር የሚከናወንበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ነው” ሲሉም ከጠ/ሚኒስትሩ የሚጠብቁትን ጠቁመዋል፡፡
“ዶ/ር አብይ ሃገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ ባለችበት ሰዓት ነው ወደ ስልጣን የመጡት” ያሉት የፓርቲው ም/ሊቀመንበር፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሣትና ዜጎችን ያፈናቀሉ አካላትን ለህግ በማቅረብ ረገድ ፈተና ይገጥማቸዋል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል። የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን እንዴት ማረቅ እንደሚቻል ለወደፊቱ የሚታይ ነው ያሉት አቶ ሙላቱ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ በሃገሪቱ 31 ያህል ሰዎች መገደላቸውንና በሺዎች የሚቆጠሩ መታሰራቸውን ፓርቲያቸው መረጃ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያን አንድነት የትግሉ ማዕከል አድርጎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ያወሳው መኢአድ በበኩሉ፤ አሁን ጠ/ሚኒስትሩ በዚህ አስተሳሰብ ዙሪያ ንግግር ማድረጋቸው ተስፋ ሰጪ ነው ብሏል፡፡ የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መግለጫ፤ ፓርቲያቸው ለአመታት በዘርና በቋንቋ ላይ ተመስርቶ፣ ልዩነትን በመስበክ ላይ ያተኮረው የፖለቲካ አካሄድ ለሃገሪቱ እንደማያዋጣ ሲያሳስብ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
“አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ያቀረቡት ንግግር ስንመኘው የነበረውን ነው” ብለዋል - ዶ/ር በዛብህ፡፡ የተቃዋሚም ሆነ የህዝቡ ድምፅ መሰማት እንዳለበት ያቀረቡት ሃሳብ የሚደገፍ ነው ያሉት የመኢአድ ፕሬዚዳንት፤ በቀጣይ ከጠ/ሚኒስትሩ ተግባራዊ ውጤት እንጠብቃለን ብለዋል። “ንግግራቸው ጊዜያዊ እፎይታ ሊሰጥ ይችላል እንጂ ዘላቂ ውጤት አያመጣም፤ በተለይ የወጣቱ የስራ አጥነት ጉዳይ፣ ዲሞክራሲን የማስፋፋትና ፍትህን የማስፈን ተግባራት ሊተኮርባቸው ይገባል” በማለት ተናግረዋል-የፓርቲው መሪ፡፡ 

Read 1221 times