Sunday, 01 April 2018 00:00

የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር፤ ጊዜያዊ መኖሪያቸውን ጦር ሃይሎች አድርገዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

 ዶ/ር አብይ ለማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ጥሪ አስተላለፉ

   በተተኪያቸው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት  ከቤተ መንግስት የክብር  አሸኛኘት የተደረገላቸው የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ፤ ጊዜያዊ መኖርያቸውን በአዲስ አበባ ጦር ሃይሎች፣ ኦሜድላ ክለብ አካባቢ ማድረጋቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ኃይለማርያም ምክትል ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ወደሚኖሩበት ቤት መመለሳቸውን የተናገሩት ምንጮች፤በ25 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነቡ እንደሆነ የተነገረላቸው የመንግስት ባለስልጣናት መኖሪያ ቤቶች ሲጠናቀቁ ወደዚያ እንደሚዛወሩ ጠቁመዋል፡፡ ለጊዜው ግን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤የመኖሪያ ሰፈራቸውን ከአራት ኪሎ ወደ ጦር ኃሎች ቀይረዋል፡፡
በርግጥ ጦር ሃይሎችም ቢሆን ብቻቸውን አይደሉም፡፡ የቀድሞ የሥራ ባልደረባቸው ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ጎረቤታቸው እንደሆኑ  ታውቋል፡፡
አቶ ኃይለማርያምና ቤተሰባቸው ለስድስት ዓመት ገደማ ከኖሩበት ታላቁ ቤተ መንግስት ሙሉ ለሙሉ ለቀው የወጡት ባለፈው ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ነው - ምንጮች እንደጠቆሙት፡፡
ከስልጣን የሚሰናበቱ የመንግስት ባለስልጣናትን ጥቅማ ጥቅሞች ለማስከበር በ2001 ዓ.ም የወጣው አዋጅ ቁጥር 653/2001፣ በጥር 2009 ዓ.ም በድጋሚ የተሻሻለ ሲሆን በተሻሻለው አዋጅ መሰረትም፤ከስልጣናቸው የሚለቁ የመንግስትና የሃገር መሪዎች በመቋቋሚያ አበልነት የ24 ወራት የአበል ክፍያ ተሰልቶ የሚሰጣቸው ሲሆን መኖሪያ ቤት፣ ሁለት ተሽከርካሪ ከእነ ሹሬሩና ጥበቃዎች ይመደብላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለተሽከርካሪዎች ነዳጅና የጥገና ወጪ በመንግስት እንደሚሸፈንም ይጠቁማል፡፡ በሌላ በኩል፤አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን በስልጣን ላይ በሚቆይበት ወቅትም፣500 ካሬ ሜትር የከተማ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንደሚሰጠውም በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ ኃይለማርም ደሣለኝ ጠ/ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ሲጠቀሙበት የነበረውን “Prime minister Hilemariam desalegn” የሚለውን የፌስቡክ ገፃቸውን ከሰኞ ከሰአት በኋላ ጀምሮ “Former Prime minister Hilemariam Desalegn” ወደ ሚል መቀየራቸው ታውቋል፡፡ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር በበኩላቸው፤በበአለ ሲመታቸው እለት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት አማካኝነት አዲስ የፌስ ቡክ ገፅ መክፈታቸው ታውቋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት “Office of the prime minister-Ethiopia” በሚለው የፌስ ቡክ ገፁ ላይ የአዲሱን ጠ/ሚኒስትር የፌስ ቡክ ገፅ ያስተዋወቀ ሲሆን ዶ/ር አብይ ከዚህ ቀደም ትዊተርም ሆነ ፌስ ቡክ እንደማይጠቀሙ አመልክቷል፡፡
አዲሱ የጠ/ሚኒስትሩ የፌስ ቡክ ገፅም፤”Prime minister Abiy-Ahmed PHD” የሚል መሆኑን አስታውቋል - ፅ/ቤቱ፡፡ የፌስ ቡክ ገጹ እስከ ትላንት በስቲያ ድረስ (መጋቢት 27 ቀን 2010 ዓ.ም) ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች “ላይክ” እንዳደረጉትም ለማወቅ ተችሏል፡፡  
በስማቸው የተለያዩ የፌስ ቡክና ቲውተር አካውንቶች እየተከፈቱ መሆናቸውን አስመልክቶ በገጻቸው መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በበኩላቸው፤በስማቸው የሳቸውን ሃሳብ የማይወክል ጽሁፍ የሚያስተላልፉ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል፡፡ “ውድ የማህራዊ ሚዲያ ተከታዮች፤በእኔ ስም በርካታ የፌስ ቡክና ቲውተር አካውንቶች መከፈታቸውንና እየተከፈቱ መሆናቸውን ለማወቅ ችያለሁ፡፡ አካውንቶቹን የከፈቱትም ሆነ እየከፈቱ ያሉት ለእኔ ያላቸውን ፍቅር ለመግለፅ በማሰብ ሊሆን ይችላል፤ነገር ግን የማይወክለኝን ሃሳብ በእኔ ስም ማስተላለፍ አግባብ አለመሆኑን በመገንዘብ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እጠይቃለሁ፡፡” ብለዋል፡፡ ለማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ባስተላለፉት ጥሪም፤” “ገንቢ ሃሳቦችን በማንሸራሸር ለሃገራችን ልማትና ዲሞክራሲ ባህል ማጎልበቻ ተደማሪ ሚና እንድትጫወቱ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ” ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡

Read 4289 times