Sunday, 01 April 2018 00:00

አዲሱ ጠ/ሚኒስትር፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሣትና እስረኞችን በመፍታት ሥራቸውን እንዲጀምሩ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  ”ዶ/ር አቢይ፤ ሃገሪቱን ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲ ለማሸጋገር ድፍረት ይኖራቸዋል ብዬ አምናለሁ”- አና ጎሜዝ
           *ዳግም ታስረው የነበሩት እነ እስክንድር ነጋ ሃሙስ ተፈተዋል

    አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ሰላምና መግባባትን መፍጠር በሚያስችል መልኩ የፖለቲካ እስረኞችን በመልቀቅና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳት፣የመንግሥት ስራቸውን  እንዲጀምሩ የካናዳና የአሜሪካ መንግሥታት ጠየቁ።
 በሌላ በኩል፤ በባህርዳር በኮማንድ ፖስቱ ታስረው የነበሩ 19 የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ፖለቲከኞች ከእስር የተፈቱ ሲሆን እስክንድር ነጋን ጨምሮ 12 የሚደርሱ ዳግም ለእስር የተዳረጉ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ባለፈው ሃሙስ አመሻሽ ላይ ከእስር እንደተለቀቁ ታውቋል፡፡  
በአዲስ አበባ የሚገኘው የካናዳ ኤምባሲ፤ የዶ/ር አብይን በጠ/ሚኒስትርነት መመረጥ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤በቀጣይ የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ወሳኝ ነው ብሏል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳም ኤምባሲው ጠይቋል፡፡
የሀገሪቱን የፖለቲካና ማህበራዊ ምህዳር ለማስፋት እንዲሁም ሁሉንም ዜጎች ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት መጀመር እንዳለበት የጠቆመው የኤምባሲው መግለጫ፤የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትም ሊከበር ይገባል ብሏል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት በበኩሉ፤ሠላማዊና ህገ መንግስታዊ የስልጣን ሽግግር በመካሄዱ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ፤ፈጣን ዲሞክራሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት በቅድሚያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት ያስፈልጋል ብሏል፡፡ በሀገሪቱ ሁሉን አሳታፊ የፖለቲካ ንግግርና ውይይት እንዲካሄድ፣ የህዝቡ የፖለቲካ ተሳትፎም እንዲጎለብት መንግሥታቱ በመግለጫቸው  ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር የሚታወቁት የአውሮፓ ፓርላማ አባል አና ጎሜዝ በበኩላቸው፤ዶ/ር አብይ ያቀረቡት ንግግር ጠንካራ እንደነበር ጠቁመው፤ቃላት ብቻ ግን በቂ እንዳልሆነና  ተግባራቸው እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ፤ ሃገሪቱን ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲ ለማሸጋገር ድፍረት ይኖራቸዋል ብለው እንደሚገምቱም አና ጎሜዝ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የሱዳንና የግብፅ ፕሬዚዳንቶች ከዶ/ር አብይ ጋር በስልክ ውይይት ማድረጋቸውንና በቀጠናው ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት መነጋገራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ለሁለት ሳምንታት በኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ስር ውለው በፖሊስ ጣቢያ ታስረው የነበሩት እስክንድር ነጋን ጨምሮ 12 የሚደርሱ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ባለፈው ሃሙስ አመሻሽ ላይ እንደተፈቱ ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ በባህርዳር የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም ሲንቀሳቀሱ ተይዘው ታስረው የነበሩ 19 የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ፖለቲከኞችም ባሳለፍነው ሳምንት ከእስር ተለቀዋል፡፡
መጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መኖሪያ ቤት በተዘጋጀ የግብዣ ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ በነበሩበት ወቅት “አርማ የሌለው ባንዲራ ይዛችኋል፣ ያልተፈቀደ ስብሰባ አድርጋችኋል” በሚል ታሰረው የነበሩት እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ይድነቃቸው አዲስ፣ ማህሌት ፋንታሁንና ወይንሸት ሞላን ጨምሮ 12 ግለሰቦች ናቸው ከእስር የተፈቱት፡፡  

Read 2972 times