Saturday, 14 April 2018 14:02

ዶ/ር አብይ ከሃገር ውጭ ለሚታገሉ ተቃዋሚዎች የድርድር ጥሪ አቀረቡ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(12 votes)

 · አርቲስቶች የዶ/ር አብይ አመራር ላይ ተስፋ ጥለዋል  
    · “ደም ሳንቀባባ በሃሳብ ተስማምተን፣ የመሸናነፍ ባህል ልናዳብር ይገባል” - ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ
    · “የጠ/ሚ ትልቁ ፈተና፤ አገሪቱን መምራት ሳይሆን ኢህአዴግን መምራት ነው- ዶ/ር መረራ ጉዲና
           
   አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ በውጭ አገር በትግል ላይ ለሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የድርድር ጥሪ አቀረቡ፡፡ ሰላማዊ መንገድን ተከትለው መደራደር ለሚፈልጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መድረኩ ክፍት ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ መንግስታቸው ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከትናንት በስቲያ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ለተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ ለታዋቂ ሰዎችና ለሲቪክ ማህበራት አመራሮች የእራት ግብዣ አድርገዋል፡፡ በዚሁ የእራት ግብዣ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ለአገሪቱ ሰላም፤ ዲሞክራሲና ልማት ለማምጣት በሚደረገው ትግል ውስጥ የዳር ተመልካች ከመሆን ይልቅ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ተደራጅተውና ፓርቲ መስርተው ያላሰለሰ ትግል በማድረግ ላይ የሚገኙትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አመስግነዋል፡፡
“ሰው በጊዜ፣  በቦታና በሁኔታዎች የሚወሰን በመሆኑ ሁሉን ነገር እኔ ብቻ አውቃለሁ ማለት አይችልም” ያሉት ዶ/ር አብይ፤ በአገራችን ጉዳይ እኛንም ያገባናል በማለት የእኔነት ስሜት ኖሮአቸው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ ጥረት የሚያደርጉትን ተፎካካሪ ፓርቲዎች አድንቀው፤ መንግስታቸው የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣ ከሁሉም ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል - ተከታታይ የሆኑ እርምጃዎች እንደሚወስዱም በመግለፅ፡፡
“አገር ከልዩነትም በላይ ነች” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ልዩነታችንን አጥብበን፣ በጉልበት ሳይሆን በሃሳብ ተዋግተን፣ ደም ሳንቃባ አሸናፊ ለመሆን፤ ከተሸነፍንም አዳዲስ ሃሳቦችን ፈጥረን፣ ለሌላ ጊዜ የምንዘጋጅበት ባህል ማዳበር ይገባናል” ብለዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ከፖለቲካ የውይይት መድረክ የወጡ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ መድረኩ እንዲመለሱና ያሉትን ችግሮች በጋራ በመፍታት፣ ለለውጥ በቁርጠኝነት እንዲታገሉም አሳስበዋል፡፡
በትግል ላይ ለሚገኙና ሰላማዊ መንገድን ተከትለው መደራደር ለሚፈልጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በሩ ክፍት ነው ያሉት ዶ/ር አብይ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በግልና በጋራ በመሆን ከኢህአዴግ ጋር የጀመሩትን ሁሉን አቀፍ ውይይትና ድርድር አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸውም ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለጠ/ሚኒስትሩ ጥሪ የሰጡት ምላሽ ጥርጣሬ የተሞላበት ይመስላል። የኦፌኮ ሊቀ መንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በሰጡት አስተያየት፤ እንዲህ አይነት ጥሪ ከኢህአዴግ ሲቀርብ አዲስ ነገር አለመሆኑን ጠቁመው፤ ዋናው ችግር ኢህአዴግ የሚናገረውና የሚያደርገው ለየቅል መሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ ራሱን ለለውጥ ካዘጋጀ ግን ሁሉም ነገር ቀላል እንደሚሆን ዶ/ር መረራ ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ጠንካራ መሪዎችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የምትፈልግበት ደረጃ ላይ መድረሷን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ አገር መምራትና ማስተዳደር፣ ውስብስብና ከባድ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ግን የተለየ ሃሳብ አላቸው፡፡ “የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ትልቁ የታሪክ ፈተና የኢትዮጵያን ህዝብና አገሪቱን መምራት ሳይሆን ኢህአዴግን መምራት ነው” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢህአዴግን መምራት ከቻሉ አገሪቷንና ህዝቡን መምራት ቀላል እንደሆነ ተናግረዋል።
“አፄ ኃይለሥላሴ፤ ጣሊያንን አሸንፈው ሲገቡ “አዲስ ዘመን ሆነ” እንደተባለ ሁሉ፤ ለመቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ፣ አዲስ ዘመን ለመፍጠርና አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆኑ ኢህአዴግም ዝግጁ ሊሆን ይገባዋል ብለዋል” ዶ/ር መረራ፡፡
የኦፌኮ ተ/ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው፤ በኢህአዴግ በኩል የዚህ አይነት ጥሪዎች በተደጋጋሚ መቅረባቸውን አስታውሰው፤ ጥሪው በተግባር ሊደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ “አገራችንን በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ገንብተን፣ ህገ መንግስቱን አክብረን፣ ሰላማዊና የተረጋጋች አገር እንፈጥራለን የሚለውን ጉዳይ እኛ ቀደም ሲል ስንተገብረው የኖርነው ነው” ያሉት አቶ በቀለ፤ በአገሪቱ ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ ተጠያቂው ኢህአዴግ ወይንም አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው መንግሥት ነው፤ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተተኮሰ ጥይት የለም አሊያም ለሁከት መነሳት ምክንያት የሆነ ተቃዋሚ አልታየም፤ ይህን ሲያደርግ የኖረው መንግስት ነው፡፡” ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ጥሪ ይበልጡኑ ለፓርቲያቸው አባላትና ደጋፊዎች ቢያደርጉት የተሻለ እንደሚሆንም አቶ በቀለ ገልፀዋል፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አጀማመራቸው ጥሩ ይመስላል ከኢህአዴግ የተለየ አመለካከትና ባህል ይዘው ብቅ ያሉ ይመስላሉ” ብለዋል፡፡ “ኢህአዴግ ከዚህ ቀደም ሁሉንም ነገር የማውቀው እኔ ነኝ፣ ከኔ በላይ የሚችል - ከእኔ ውጪ ለአገር የሚያስብና የሚቆረቆር የለም የሚል እምነት ነበረው፤ አሁን ግን ሁላችሁም ያገባችኋል፣ አገር ለማስተዳደር አቅምም ፍላጎትም አላችሁ መባላችን በራሱ አንድ የተለየ ስሜትን የሚፈጥር ጉዳይ” ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሐሙስ ምሽት በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተካሄደው የራት ግብዣ ላይ የተገኙት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ታዋቂ ሰዎች በበኩላቸው፤ አገሪቱ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተጓዘች መሆኗ እንደሚያስደስታቸው ጠቁመው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል አክብረው አገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሳታል የሚል ትልቅ እምነትና ተስፋ አለን ብለዋል፡፡

Read 8630 times