Saturday, 14 April 2018 14:03

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 10 ቀናት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

በጅግጅጋ--አምቦ---መቀሌ --- ከህዝብ ጋር ተገናኝተዋል በአዲስ አበባ ከወጣቶችና ከባለሃብቶች ጋር ይወያያሉ

    አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ ወደ ሥልጣን የመጡት በ“ሰላም” ዘመን አይደለም። አገር በቀውስ ማዕበል በምትናጥበት፣ ሚሊዮኖች ከቀዬአቸው በተፈናቀሉበት፣ ዘረኝነት በእጅጉ  በናኘበት፣ አንድነት በመነመነበት፣ ሙስና በናጠጠበት፣ የጥላቻ ፖለቲካ በነገሰበት …ፈታኝ ወቅት ላይ ነው አገር የመምራት ዕጣ ፈንታ የወደቀባቸው። ጊዜና ትንፋሽ የማይሰጥ ከባድ ሃላፊነት ነው የጠበቃቸው፡፡ ለዚህ ነው በብርሃን ፍጥነት ወደ ሥራ የገቡት፡፡
ዶ/ር አብይ ሥልጣን በያዙ በአምስተኛው ቀን ላይ ቅዳሜ መጋቢት 29 ቀን 2010 ዓ.ም ነው ወደ ጅግጅጋ ያቀኑት-- የሶማሌ ክልላዊ መንግስት መናገሻ በሆነችው ጅግጅጋ በተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ፤ 1 ሚሊዮን ገደማ ለሚሆኑ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው የኦሮሚያ ሶማሌ ክልሎች የድንበር ግጭት በእርቅ ተፈትቶ፣ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ውይይት ላይ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ አህመድ፣ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ሌሎች ባለሥልጣናት እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የስብሰባው ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡  
ጠ/ሚኒስትሩ በጅግጅጋ ባደረጉት ንግግር፤ “ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው ግጭት አሳፋሪ የሽንፈት ታሪካችን ነው” ብለዋል፡፡ ለአስተዳደር አመቺነት የሚሰመር ወሰንም ቢሆን እንኳ ለሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች የመለያያ ግንብ መሆን እንደሌለበትም በአፅንኦት አሳስበዋል - ዶ/ር አብይ፡፡ ችግሩ በማያዳግም መልኩ ከስር መሰረቱ እንዲፈታም ለሁለቱ ክልሎች ፕሬዚዳንቶች ጠንከር ያለ መልዕክትና አደራ አስተላልፈዋል፡፡ “ግጭቱን የምናስታውሰው እንዳይደገም ብቻ ነው፤ አሁን አጀንዳችን ሰላም … ሰላም … ብቻ” ብለዋል  - ዶ/ር አብይ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፤ “የተፈጠረው ችግር ሁላችንንም ያሳዘነ ውርደታችን ነው” ብለዋል፡፡ ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ የሶማሌ ተወላጆችን በራሳቸው ተነሳሽነት ኃላፊነት ወስደው፣ ወደ ነበሩበት ለመመለስ ቃል የገቡ ሲሆን የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሃመድም ተመሳሳይ ንግግር አድርገዋል፡፡ የኦሮሞና የሶማሌ ህዝብ አንድነትን ሁለቱ መሪዎች ከተቀመጡበት በመነሳት በእጃቸው እንዲያሳዩ የጠየቁት ዶ/ር አብይ፤ “የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፤ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሃመድ” … በማለት ሆነ ብለው መሪዎችን አለዋውጠው ሲጠሩም ያልተጠበቀ የሳቅና ዘና የማድረግ ስሜትን ፈጥሯል፡፡ ትልቅ መልዕክትም የሚያስተላልፍ ነው - ለመሪዎች፡፡   
ጠ/ሚኒስትሩ ሥልጣን በጨበጡ በዘጠነኛው ቀን፣ ረቡዕ ሚያዚያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ ወደ  አምቦ አቅንተዋል፡፡ አምቦ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ገደማ በመላው ኦሮሚያ ለዘለቀው ተቃውሞና ግጭት ዋና መነሻ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ወደ ከተማዋ እንደሚመጡ ቀደም ብሎ የተነገረው መረጃ አብዛኞቹን ነዋሪዎች በተስፋና በደስታ የመሙላት አቅሙ ታላቅ ነበር ተብሏል፡፡
ጠ/ሚኒስትር አብይ፤ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ለማ መገርሳ አምቦ ሲገቡ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች፣ ከ200 በላይ ፈረሰኞችና ከ1 ሺህ በላይ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች በመሆን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር አብይ በአምቦ ስቴዲየም ለታደመውና ቁጥሩ ወደ 300 ሺ የሚደርስ ህዝብ ባደረጉት ንግግር፤ “መጪው ጊዜ በአንድነታችንና በአብሮነታችን በዓለም ህዝብ ዘንድ በምሳሌነት የምንጠራበት ሊሆን ይገባል … በትግላችን ድልን መቀዳጀት ችለናል፤ የድላችን ውጤትም ያለፈ ታሪካችንን የምንቆጥርበት ሳይሆን ወደፊት አርቀን በማየት ለአጠቃላይ ለውጥ የምንሰራበት ነው” ብለዋል፡፡
“የማይነቃነቅና የማይፈራርስ የመሸጋገሪያ ድልድይ በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት የህዝቡ ንቅናቄ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” ያሉት ዶ/ር አብይ, “ህዝቡ የሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ ምሰሶ ነው” ሲሉም ተናግረዋል። በህዝብና በመንግሥት መካከል መደማመጥ መኖር እንዳለበት ያሳሰቡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “በአንድ ሃገር ጠቃሚ ሃሳብ ሊመነጭ የሚችለው ዜጎች በነፃነት የሃሳብ ፍጭት ሲያደርጉ በመሆኑ፣ ይህን ስናደርግ ብቻ ነው የጀመርነውን ሩጫ በድል ልንጨርስ የምንችለው” ብለዋል፡፡ “ብቸኛ የመፍትሄ ሃሳብ ያለኝ እኔ ብቻ ነኝ” የሚል አመለካከት መቅረት እንዳለበትም ዶ/ር ዐቢይ አሳስበዋል፡፡
“ቄሮ የኦሮሞ ህዝብ ጋሻ ነው፣ የህዝብ ሁሉ ጋሻ ነው፣ ከቄሮዎች ተሳትፎ ውጪ አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው ሰላም እንዲሁም ልማትና ዲሞክራሲን መሬት ማስያዝ የማይታሰብ መሆኑን እናውቃለን” ያሉት ዶ/ር አብይ፤ “በየጊዜው በተደረጉ ትግሎች ለተሰዉ ሁሉ ክብር ይሁን” ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ በበኩላቸው፤ “ዛሬ ወደ አምቦ የመጣነው እንደሌላው ጊዜ እሳት ለማጥፋት ሳይሆን የምስራች ልንናገር ነው፤ ለኦሮሞ ህዝብ ሩቅ የነበረው ሃገሪቱን የመምራት ዕድል በሁሉም ህዝብ ትግል እውን ሆኗል፤ ኃላፊነታችንን በአግባቡ መወጣት አለብን” ብለዋል፡፡
ድርጅታቸው ኦህዴድ በየጊዜው በህዝቡ ትግል ለውጦችና መሻሻሎችን በማድረግና ጥንካሬን በመላበስ ሀገሪቱን የመምራት ኃላፊነት መረከቡን ጠቁመው፤ ”ኢትዮጵያ ለሁሉም ብሔረሰቦች የተመቸች አገር እንድትሆን እንሰራለን” ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለምክትላቸው እንዲሁም ለኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ከአካባቢው ሽማግሌዎች የፈረስ፣ የጦርና ጋሻ፣ እንዲሁም የኦሮሞ የጦር ጀግና አልባሳት ከሕዝቡ በስጦታ እንደተበረከተላቸውም ታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአስረኛ ቀናቸው፣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ምሽት ለተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ ለአርቲስቶች፣ ለታዋቂ ግለሰቦችና ለሲቪክ ተቋማት መሪዎች በቤተ መንግስት የእራት ግብዣ ያደረጉ ሲሆን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለማጠናከርና የዲሞክራሲ ሥርዓትን ውጤታማ ለማድረግ በጋራ ሊሰራ ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በአስራ አንደኛ ቀናቸው ትላንት አርብ  ያቀኑት ወደ መቀሌ ሲሆን እዚያም በትግርኛ ያደረጉት ንግግር የትግራይ ህዝብን አድናቆትና ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል፡፡
ዶ/ር አብይ አህመድ ትናንት በመቀሌ የሰማዕታት ሐውልት በሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር “ኢትዮጵያ ያለ ትግራይ ህዝብ፣ የትግራይ ህዝብ ያለ ኢትዮጵያ የሚሆን አይደለም” ብለዋል፡፡ አያይዘውም የትግራይ ህዝብ ሃገሩን የሚወድና ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ለመገንባት ልጆቹን መስዋዕት ማድረጉን አውስተዋል፡፡
የትግራይ ክልል የስልጣኔ፣ የዜማ እና የቅኔ መነሻ መሆኗን ያወሱት ጠ/ሚኒስትሩ ትግራዋዮችም ለኢትዮጵያ አንድነትና መጠናከር ሲታገሉ ኖረዋል ብለዋል፡፡
በትግራይ ክልል ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው የአረና ሊቀ መንበር አቶ አብርሃ ደስታ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቀሌ ቆይታቸው ከክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ተመርጠው ከተሰበሰቡ ካድሬዎች ጋር እንጂ በቀጥታ ከህዝቡ ጋር የመገናኘት እድል አላጋጠማቸውም ሲሉ የጉብኝቱ አላማ ግቡን እንዳልመታ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን በተረከቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ በየክልሉ እየዞሩ የሚያደርጉትን ጉብኝትና ህዝባዊ ውይይት አስመልክቶ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው አንጋፋ ፖለቲከኞች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱን ማድረጋቸው ጠቃሚ ቢሆንም ያን ያህል አስፈላጊ ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡ ዋናው ጉዳይ በአፋጣኝ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ድርድር ተቀምጦ፣ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ ማሻሻል ነው ብለዋል - ፖለቲከኞቹ፡፡  
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝብን በየቦታው እየተንቀሳቀሱ ማግኘታቸው ያለው ፖለቲካዊ ፋይዳ አጠያያቂ አይደለም ያሉት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ዋናው ግን በተጨባጭ ፖለቲካዊ ማሻሻያ የሚወስድ እርምጃ ነው ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ በተለይ ወደ ብሔራዊ መግባባት የሚወስድ ድርድር ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር መጀመር ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ይህ እስካልሆነ ድረስ ግን አሁን ጠ/ሚኒስትሩ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጊዜያዊ ስሜትን ከማርገብ በዘለለ ብቻውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ሊለውጥ አይችልም  ብለዋል፡፡
አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል የተከሰተው ግጭት የፈጠረውን ስሜት ለማሻር ወደ ጅግጅጋ ማቅናታቸው ተገቢ መሆኑን አስምረውበት ከዚያ ውጭ በየቦታው የሚደረገው ስብሰባ ግን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለው እንደማያምኑ ነው የተናገሩት፡፡ ከህዝብ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የመወያየት አስፈላጊነት አጠያያቂ ባይሆንም በቅድሚያ ግን ቃል ወደገቧቸው ነጥቦች ፊታቸውን አዙረው፣ ከፖለቲካ ኃይሎችና የሃገሬ ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉ አካላት ጋር ለድርድር መቀመጥ አለባቸው ባይ ናቸው አቶ ልደቱ፡፡   
“ህዝቡ ተጨማሪ ንግግር ሳይሆን ተጨባጭ እርምጃ ነው የሚጠብቀው” ያሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ፤ “አለበለዚያ የጫጉላ ሽርሽር ጊዜው ያልቅና በድጋሚ
ወደ ነበርንበት ችግር እንዳንመለስ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል - ጠ/ሚኒስትሩ ተጨባጭ የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጦች የሚመጡበት ሁኔታ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው በማሳሰብ፡፡ 

Read 8705 times