Saturday, 14 April 2018 14:19

“ብቆጣም እመታሻለሁ፤ ብትቆጪም እመታሻለሁ!”

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ጥንት በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን አንድ ምስኪን አሜሪካዊ፤ በአሜሪካኑ ሁዋይት ሐውስ ፊት ለፊት፣ ሣር ሲግጥ ይታያል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሰገነታቸው ላይ ቆመው ይህ ዜጋ ሳር ሲግጥ በማየታቸው እጅግ ተደንቀው ያስጠሩታል፡፡
ፕሬዚዳንት፤
“ምን ሆነህ ነው ሳር የምትግጠው?”
ምስኪኑ ዜጋም፤
“ርቦኝ፡፡ ጠኔ ሊገለኝ ሲሆን ሳርም ቢሆን ልቅመስ ብዬ ነው!”
ፕሬዚዳንት፤
“በል በቃህ፡፡ ለአምስት ዓመት በቀን ሶስት ጊዜ ማክዶናልድ (ሀምበርገር) በእኔ ሂሳብ ትበላለህ”፤ ግን ሥራ ፈልግ” ብለው አሰናበቱት፡፡ ተደስቶ ጮቤ እየረገጠ ሄደ፡፡
አምስት ዓመት በላ፡፡ አምስት ዓመት ጠገበ፡፡ ሥራ ግን አሁንም አላገኘም!
ስለዚህ ወደ ሩሲያ ሄደ፡፡ ሩሲያ ጥቂት እንደቆየ መራብ ጀመረ፡፡ ረሀቡን ለማስታገስ ወደ ዋናው የመንግሥት መናኸሪያ ወደ ክሬምሊን ሄደ፡፡ ከዚያም ፊት ለፊት ያገኘውን ሣር መጋጥ ጀመረ፡፡ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ብሬዤኔቭ አዩት፡፡ ነገሩ ገርሟቸው አስጠሩት፡፡ በአጃቢ ገብቶ ፊታቸው ቀረበ፡፡ ብሬዥኔቭም፤
“ምን ሆነህ ነው እንዲህ እየተስገበገብክ ሳር የምትግጠው?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
ምስኪኑ አሜሪካዊም፤
“ርሃብ! ጠኔ ሊገለኝ ነው ክቡር ፕሬዚዳንት!”
ፕሬዚዳንቱ ትንሽ አቅማሙና፤
“ታዲያ ለነገዬ አትችልም? ፕላንድ ኢኮኖሚ አታውቅም? በአንድ ቀን ግጠህ ልትጨርሰው ነው?” ብለው ኢኮኖሚያዊ ግሳፄ ሰጡት!!
*   *   *
አሜሪካኖች ሥራ ከመስጠት ይልቅ፤ ብር መስጠት ወደዱ፡፡ ሩሲያውያን በባዶ ሆድህ ቁጠባን ዕወቅ አሉ፡፡ ዓለም እንደዚያ ነበረች፡፡ ከዚያ ይሰውረን!
ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፤ ዛሬም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሆነ አለ! የዓለም ባንክና የዓም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዘገባዎች፤ (የአየለ አይኤምኤፍን ነብስ ይማር!) በኢትዮጵያ ኑሮና ካዝና አንፃር፡-
“ላም አለኝ በሰማይ
ወተቷንም አላይ” ናቸው፡፡ እንጂ እንደ  ካፒታሊስቶቹ ምኞትማ፡-
“ላም አለኝ በሰማይ
ወተቷ እሚከራይ!” በሆነ ነበር!
ከሁሉም ያውጣን!
“ገንዘቤን የወሰደ ሰው፣ ወሰደ እንበል ከንቱ ነገር የእኔም የሱም የዚያም ነበር
ግና ስሜን የሰረቀኝ የማያከብረውን ወስዶ፣ እኔን በግልፅ አደኸየኝ” (ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን)
ከማለት ሌላ ምን አቅም አለን፡፡
ካርል ማርክስ እንደሚለንም፤
“ፖለቲካ የኢኮኖሚ ጥርቅም መልክ ነው” (Politics is the concentrated form of economics)
ይህ እንግዲህ በሀገራችን ተሾመም፣ ተመረጠም፣ መሪ የሆነ ሰው፤ የፖለቲካም የኢኮኖሚም የአደራ ዕዳ እንዳለበት ነው፡፡ የህዝቡ ኑሮ እጅግ ጠያቂ ነው፡፡ ማንንም አይምርም! ይፈታተናል፡፡ ብልህ መሪ፤ አስተዋይ፣ ሆደ - ሰፊ፣ ትዕግሥቱን በብዛት የሰጣቸውን ባለ ራዕይ ጠቢባን የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን በዙሪያው ሰብስቦ፡-
“ነገርን ከሥሩ
ውሃን ከጥሩ”
ማጤን ይጠበቅበታል!
“ጣሊያን ሊማሊሞን በመድፍ ሲደበድበው አደረ” ቢሉት፤
“ተወው ይበለው! እሱም መገተሩን አብዝቶት ነበር” አለ አሉ የጎንደር ሰው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግን በመድፍም ቢመታ ውልፊት አይልም! እንኳንስ በአንድ ጀምበር በአያሌ ጀምበሮችም የማይነቀነቅ ስለሆነ፣ “እንኳን ተለያይተን አንድ ሆነንም አስቸጋሪ ነው” ማለት ትክክለኛ አቅጣጫ ነው!
ተባብረን የኢኮኖሚያችንን ነገር ምን እናድርገው? እንባባል!
የቀድሞ፣ ቀድሞ መሪያችንን ራዕይ ብቻ የሙጥኝ በማለት አንወጣውም! ከአዳጊው ሁኔታ ጋር ምን ምን የኢኮኖሚ መንገድ እንቀይስ ካልተባባልን፣ የተሾመን የሚሽር፣ የመጣን የሚያወርድ አደጋ ፊታችን ላይ ተደቅኗል! እንደ ወትሮው፣
“ብቆጣም እመታሻለሁ፤ ብትቆጪም እመታሻለሁ” ዓይነት ዲሞክራሲ ዛሬ ወንዝ አያሻግርም! ደጋግመን “ፖለቲካው የኢኮኖሚው ጥርቅም መልክ ነው!” የሚለውን ጥልቅ አስተሳሰብ፤ በጥልቅ ግምገማም ቢሆን እንመርምረው!
ለክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች
መልካም የዳግማይ ትንሣዔ በዓል!

Read 6320 times