Saturday, 14 April 2018 14:27

የ”ሃውስ ሪዞሉሽን 128” ይዘትና አንደምታዎቹ

Written by  ታምራት መርጊያ
Rate this item
(1 Vote)


   ሚያዚያ 2 ቀን 2010 ዓ.ም የአሜሪካ ምክር ቤት (congress) ሃውስ ሪዞሉሽን 128  (#HRes128) በመባል የሚታወቀውን ሰነድ ለምክር ቤቱ አቅርቦ፣ ማሳለፉ፣ የብዙዎችን ትኩረት የሳበና መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተ ጉዳይ ነው። ሰነዱ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብዓዊ መብቶች፥ ለህግ የበላይነትና  ለዴሞክራሲ መረጋገጥ ተገዢ እንዲሆን በጥብቅ የሚያሳስብ ሰነድ እንደሆነ ከመፅደቁ በፊት ጀምሮ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በስፋት ሲዘግቡት እንደነበርም የሚታወስ ነው።. ይህ ሰነድ፤ ከ2007  ጀምሮ በሐገሪቱ ውስጥ የነበረውን የሰብዓዊ መብት አጠባበቅና አያያዝ፣ በመንግስታቱ ድርጅት የሚቋቋም የሰብዓዊ መብቶች  አጥኚ ቡድን እንዲመረምረው በፅኑ የሚጠይቅ ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ከዓመት በፊት ሰነዱን ለመጀመሪያ ጊዜ አርቅቀው ለአሜሪካው የህግ መወሰኛ ምክር ቤት  ያቀረቡት፥ ኮንግረስ ማን ክርስቶፈር ሄነሪ  ስሚዝ  ወይም በአጭሩ ክሪስ ስሚዝ የሚባሉ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባልና የኒው ጀርሲ አውራጃ የህዝብ እንደራሴ ናቸው።
  በተለያዩ ሂደቶችና የምክር ቤቱ እርከኖች ሲንከባለል ቆይቶ፤ በመጨረሻም ማክሰኞ ሚያዚያ 2 ቀን 2010 ዓ.ም የፀደቀው ኤች.አር 128 የተባለው ሰነድ ይዘት እንደሚያመለክተው፥በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ በመንግሥት ላይ ተቃውሞ በማሰማታቸው የተገደሉ ዜጎች፣ ሕገመንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሐሳባቸውን በነፃ የገለፁ እንዲሁም የመሰብሰብና የመደራጀት ሕገመንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀማቸው ምክንያት ለእስርና እንግልት የተዳረጉ ፖለቲከኞች፥ ጋዜጠኞች፣ ተማሪዎችና የመብት አራማጅ ዜጎች፤ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት የፀረ ሽብር አዋጁን  ሰበብ በማድረግና ያለአግባብ በመጠቀም በሐገር ውስጥ የሲቪልና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የጋዜጠኞችን መብት ለማፈን አውሎታል ብሎ በማመን፤ ድርጊቱን በፅኑ እንደሚያወግዝ ይገልፃል።
በሌላ በኩል ደግሞ ይኸው ሰነድ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ላይ ተቃውሞአቸውን በማሰማት ላይ ያሉ ዜጎች፥ ኃይል ከተቀላቀለበት ሁከትና ብጥብጥ እንዲታቀቡ በማሳሰብ፤  የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኙ ሐይሎችም የትጥቅ ትግላቸውን አቁመው፣ ከመንግስት ጋር ሰላማዊ ድርድር እንዲያካሂዱ አበክሮ ያሳስባል።
ሰነዱ ላይ እንደተመለከተው የኢትዮጵያ መንግሥት፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሳ፤ በፀጥታ አካላት የሚወሰድ ተመጣጣኝ ያልሆነ የሐይል እርምጃ እንዲቆም፤ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ውስጥ በተካሄዱ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ምክንያት በፀጥታ ሐይሎች በተወሰደ እርምጃ ህይወታቸውን ባጡ ዜጎች ላይ የተወሰደው እርምጃ እንዲጣራ፤ ሕገመንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀማቸው የታሰሩ የመብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፤ መንግሥት የመሰብሰብ መብትን እንዲያከብርና የሚዲያ ነጻነትን እንዲያረጋግጥ፤ በልማት እቅድ ላይ በግልጽ ከዜጎች ጋር እንዲወያይ፤ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት አያያዝ አጣሪዎች በሐገሪቱ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ተንቀሳቅሰው እንዲያጣሩ፤ ህጋዊ ፍቃድ ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን ቅሬታ መንግሥት በአግባቡ እንዲፈታ፥ ንፁሐን ዜጎችን የገደሉ፣ ያሰሩና ያሰቃዩ አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ፤ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ወቅት የነበረው ሁኔታ፣ በእሬቻ በዓል አከባበር ላይ የተሳተፉ ዜጎች ላይ የተፈፀመ ግድያና   በሶማሌ ክልል በፖሊስ የተገደሉት ዜጎች ጉዳይ ተጣርቶ ሪፖርት እንዲደረግ..... የሚሉ ነጥቦች ተዘርዝረው ለኢትዮጵያ መንግስት ጥሪ ቀርቧል።
በተጨማሪም መንግሥት በሐገር ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ መብት አጣሪ ቡድኖች፣ በሰላማዊ መንገድ የተለየ የፖለቲካ  አቋም በማራመድ ለፖለቲካ ነፃነት የሚታገሉ አካላት፤ ለትርፍ ለማይሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የስራ እንቅስቃሴ አላማ ወዘተ.... የሚደረግ የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ጫና የሚፈጥርና ከልካይ የሆነ አዋጅ እንዲሻር ይጠይቃል። በሌላ በኩል፥ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፥ የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገውን ፀጥታን የተመለከተ  ድጋፍ በድጋሚ እንዲያጤነውና በድጋፉ ላይ ያለውን ቸልተኝነት እንዲያሻሽል..፤ የአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄድ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥረቶች ላይ አጋዥ ሚና እንዲኖራቸው....፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፥ ከገንዘብ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር (Department of the Treasury) ያለ ፍርድ በዜጎች ላይ፥ ግድያ፣ የማሰቃየት ተግባር ወይም በአለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመፈፀም ተጠያቂ የሚሆኑ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ እቀባ እንዲያደርግ... ይጠይቃል።
እንግዲህ ከሞላ ጎደል በይዘት ይህን የመሰለ መልክ ያለው ኤች.አር 128፤ የተለያዩ አንደምታዎች ሊኖሩት እንደሚችል ይገመታል። ከነዚህ አንደምታዎች ውስጥ ሰነዱ፤ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብር ሊያስገድድ ይችላል ብለው የሚያምኑ ወገኖች አሉ። በአንድ ወቅት የዚህ ሰነድ አርቃቂ የሆኑት ኮንግረስ ማን ክሪስ ስሚዝ የሰነዱን ጠቀሜታ አስመልክተው ለጋዜጠኞች ሲገልጹ፤ “ይህ ሰነድ የኢትዮጵያ መንግሥት እራሱን ሊመለከትበት የሚያስችለው መስታወት ነው” ብለዋል፡፡ ከዚህ እንደምንረዳውም፤ ለኢትዮጵያ መንግሥት ጠንካራ አጋር የሆነችዉ አሜሪካ፤ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያን መንግሥት የምትመለከትበትን አሮጌ መነፅር አውልቃ፤ በአዲስ መቀየሯ ይሆናል። አዲሱ መነፅር ደግሞ የሚያሳየው፥ የሰብዓዊ መብቶችን የሚያከብርና ለዴሞክራሲ ማበብ የሚተጋ የፖለቲካ ስርአትን ሳይሆን፤ የዚህ  ቀጥተኛ ተቃራኒ የሆነ  መንግሥትን ነው ማለት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የምዕራቡ አለም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋፊና ወዳጅ ሐገራት መንግሥታት፥ ልዕለ ሐያሏ አሚሪካ በክፉ የተመለከተችውን ሐገር በደቦ አብረው የመመልከት አባዜና ባህሪ ስላላቸው፥ የኤች.አር 128 መፅደቅ እነርሱንም በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ፖሊሲ እንዲቀይሩ ሊያደርጋቸው እንደሚችል አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ግምታቸውን እየሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ ይህም በምላሹ የኢትዮጵያን መንግሥት አለማቀፋዊ ገፅታ በማጠየም፥ በተለያየ መልኩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ መዘዞችን ሊያስከትል እንደሚችል ተንታኞቹ ይገልፃሉ። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ የሰነዱን መፅደቅ እንደሚቃወም የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ  ገልጸዋል። ዶ/ር ነገሪ ከሰነዱ መፅደቅ በኋላ ለአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ በሰጡት ቃለመጠይቅ፤ የሰነዱ መፅደቅ ወቅቱን ያልጠበቀና መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሐቅ ያላገናዘበ እንደሆነ አፅዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ችግሮቹን አምኖ እራሱን ለማሻሻልና ለችግሮቹ መፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውን የተለያዩ አዎንታዊ የማስተካከያ እርምጃዎች ደረጃ በደረጃ እየወሰደው በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፥ የሰነዱ መፅደቅ አግባብነት እንደሌለውም አክለው ገልፀዋል። በተጨማሪም መንግሥት ማሻሻያዎችን የሚወስደው ለውጭ አካላት ብሎ ሳይሆን ለዜጎቹ ሲል መሆኑንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፥ ከኢትዮጵያ መንግሥት አንፃር በተቃውሞ ጎራ የቆሙ ኃይሎች፥ የዚህ ሰነድ መፅደቅ ላለፋት ዓመታት የአለማቀፉ ማህበረሰብና የኢትዮጵያ መንግሥት አጋርና ደጋፊ የሆኑ አገራት፣ የመንግስትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ የዜጎቹን ህገ መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለማክበር እንቅስቃሴ ለአለማቀፍ ማህበረሰብ ለማሳወቅ፣ ሰርክ በመትጋትና በመወትወት ረገድ ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ እውቅና ማግኘቱንና ፍሬ ማፍራቱን የሚያረጋግጥ ሰነድ እንደሆነ በማሰብ፤ የሰነዱን መፅደቅ በከፍተኛ ደስታ ነው የተቀበሉት፡፡  በዚሁ ረገድ ሰነዱ ለምክርቤቱ ቀርቦ በፀደቀበት ዕለት፣ በምክር ቤቱ አዳራሽና ከአዳራሹ ውጭ በመሰብሰብ፣ ደስታቸውን በእልልታና በከፍተኛ ጭብጨባ የገለጹበትን ሁኔታ ልብ ይሏል።  
በእርግጥ ቢያንስ በመርህ ደረጃ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ አጠቃላይ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶችም ሆኑ፥ ሌሎች የህዝቡን እርካታና ጥቅም የሚያረጋግጡ ለውጦች መምጣት ያለባቸው  ዶክተር ነገሪ እንዳሉት፤ ለህዝብ ተብሎ እንጂ፤ በውጭ ኃይሎች ግፊት ወይም የውጭ አካላትን ለማስደሰትና የነርሱን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል መሆን የለበትም። ይህም ለንግግርና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን በተግባርም የመንግሥት ገዢ ሐሳብ መሆን ይገባዋል። ለማጠቃለል፤ የዚህ ሰነድ መጽደቅ፥ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለሚመራው አዲሱ መንግሥት፥ በቀጣይ  የአገሪቱን አለማቀፋዊ ገፅታ መልሶ ከመገንባት አንስቶ፣ በዜጎች የሚነሱ በርካታ የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ እንዲሁም የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዎች የመመለስ ብርቱ ፈተና፤ ከፊቱ እንደተጋረጠበት አመላካች ጉዳይ ነው። ስለሆነም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርና መንግስታቸው  በዚህ ረገድ እስከሰሩ ድረስ፥ በውጭም ሆነ በሐገሪቱ ውስጥ የሚገኝ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ ከጎናቸው ቆሞ ሊረዳቸው ይገባል ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ሀላፊነትም አለበት።

Read 536 times