Saturday, 14 April 2018 14:28

ጊዜው የትጋት እንጂ የስጋት መሆን የለበትም!

Written by  ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
Rate this item
(3 votes)

 “--የተወደዱ ዶ/ር አብይ አህመድ ያላቸውን አቅም ከምንም እንደሚበልጥ የተረዳነው አይመስለኝም። ያም አቅም ምንጩ የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ ነው። ይህንን የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ ወደ ትልቅ አቅም በመቀየር ፈተናቸውን ለመወጣት የሚችሉት ራሳቸው ዶ/ር አብይ ናቸው፡፡--”
   
   የተወደዱ ዶ/ር አብይ አህመድ እፎይ የሚያሰኝ ቃላቸውን አሰምተውን ሳለ፥ እኛ ግን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስተን ስጋት ውስጥ መግባታችን አልቀረም፡፡ ክቡር ዶ/ር አብይ፤ ሕገ መንግስቱ የሚፈቅድላቸውን ስልጣን በሙላት እንዳይጠቀሙ እንቅፋት ሊኖርባቸው ይችላል እየተባለ ስጋት ውስጥ መገባቱ አግባብ ነው ሊባልም ይችል ይሆናል። ራዕይን የሰነቀ ንግግራቸውን የሚተችም ሆነ ሰብዕናቸውን የሚጠራጠር እምብዛም አይታይም። የሁሉም ጥያቄ ያሰሯቸው ይሆንን? የሚለው ስጋት ነው።
ከዚህ በፊት “ዘብ ቆመናል ክቡር የኢትዮጵያ ልጅ ዶ/ር አብይ አህመድ” በሚለው ፅሁፌ እንደገለፅኩት፥ ዶ/ር አብይ አህመድ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለኢሕአዴግም ጭምር በረከት ናቸው። ክቡር ዶ/ር አብይ ለኢሕአዴግ ከተጋረጠበት አጣብቂኝ መውጫ ቀዳዳ እንዲሁም ኢሕአዴግ ለሚቀጥለው ምርጫ በሕዝብ እውነተኛ ምርጫ ሊያሸንፍ የሚችልበት ዕድልን የፈጠሩለት መሪ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ዶ/ር አብይ አሕመድ ህዝብን ያስደመመውን፣ የሕዝብ የልብ ትርታ ነፀብራቅ የሆነውን ንግግራቸውን በስራ ለመግለፅ ፈተና አለባቸው ከሚል ስጋት ለመላቀቅ የተቻለ አይመስልም።
የተወደዱ ዶ/ር አብይ አህመድ ያላቸውን አቅም ከምንም እንደሚበልጥ የተረዳነው አይመስለኝም። ያም አቅም ምንጩ የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ ነው። ይህንን የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ ወደ ትልቅ አቅም በመቀየር ፈተናቸውን ለመወጣት የሚችሉት ራሳቸው ዶ/ር አብይ ናቸው፡፡ ፈተናቸውን በድል ለመወጣት አቅም እንዲኖራቸውና ለሕዝብ ቃል የገቡትን በስራ ለመተርጎም የሚያስችላቸው ቁልፍ በራሳቸው እጅ ነው ያለው። ስለዚህ መስጋት ካለብን ዶ/ር አብይ የሚታመኑ አይደለም በማለት እንጨነቅ እንጂ አቅም አይኖራቸው ይሆናል ብለን አንፍራ።
ዶ/ር  አብይ አህመድ አዋላጅ ባለስልጣን ናቸው። አዋላጅ መንግስት ከማየታችን በፊት አዋላጅ ባለስልጣናት መገኘት አለባቸው። አዋላጅ መንግስት ራዕዩ ራሱን ከንጉስ መንግስትነት አላቆ ሕዝብን ማንገስ ነው። ያኔ ንጉስ የሚሆነው ሕዝብ፥  አገልጋይ የሚሆንለትን መንግስት መምረጥ እንዲችል መድረኩ ያመቸ ይሆናል። አሁን ያንን አዋላጅ መንግስት ዕውን ለማድረግ አዋላጅ ባለስልጣን የሆኑት ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ባለ አደራ ናቸው። አዋላጅ ባለስልጣን መሆን በክቡር ዶ/ር አብይ ተጀምሮ፥ በክቡር ዶ/ር አብይ የሚደመደም አይደለም። ክቡር አቶ ለማ ሀገርን ከስልጣን አስበልጠው ዶ/ር አብይን ማስቀደማቸው አዋላጅ ባለስልጣን ያደርጋቸዋል። ክቡር አቶ ደመቀ ለራሳቸው ስልጣን ከማቀንቀን ይልቅ ራሳቸውን አግልለው ዶ/ር አብይን ማስቀደማቸው አዋላጅ ባለስልጣን ያደርጋቸዋል። እንደዚሁም ክቡር አቶ ኃይለማርያም ስልጣናቸውን ለቀው ለዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት ምክንያት መሆናቸው አዋላጅ ባለስልጣን ያደርጋቸዋል። እነዚህን ለምሳሌነት ጠራው እንጂ እንደ እነ ክቡር አቶ ገዱ የመሳሰሉና ለመመረጥ ያበቋቸው ከመቶ በላይ የሆኑት የኢሕአዴግ አመራሮች እየተቀባበሉ ዶ/ር አብይን ወደ ስልጣን አምጥተዋል። እንደኔ ክቡር ዶ/ር አብይ ያደረጉት ንግግር ከምንም በላይ ባለስልጣኑ ሕዝብ እንዲሆን የሚፈልጉና ሀገርን ከራሳቸውና ከሁሉ በላይ እንዳስቀደሙ ያሳያል። ስለዚህም ዶ/ር አብይ ከስልጣናቸው ጋር የሚጣበቁ ሰው እንደማይሆኑ ግልፅ ነው። በብዙ አዋላጅ ባለስልጣናት መስዋዕትነት ታጅበውና የሕዝብን ፍቅርና አመኔታ ተገን አድርገው ለስልጣን ከመሳሳት ይልቅ ለሕዝብ ለማደር ምንም እንደማይቸገሩ መገመት ከባድ አይደለም።
ታዲያ ይህን ሁሉ ከቁጥር ስናስገባ፥ ክቡር ዶ/ር አብይ ከምንምና ከማንም በላይ ራዕይን የሰነቀውን ንግግራቸውን በተግባር ለመፈፀም አቅም አላቸው ማለት እንችላለን። ምክንያቱም እውነትን ይዘውና የሕዝብን ምኞት አንግበው፥ በሕዝብ ልብ ውስጥ ገብተው፥ በሕዝብ ከለላ ተጠልለዋልና ነው። ስለዚህም ሲሆን ሲሆን ከቻሉ፥ ይህንን የሚወዳቸውን ሕዝብ ማገልገል፥ ካልሆነ ደግሞ ስልጣናቸውን አሽቀንጥረው ለመጣል ብቃት ያላቸው ይመስለኛል። ምንም እንኳን ሕዝብ ባይመርጣቸውም፥ በመመረጣቸው ሕዝብ መደሰቱና ምርጫቸውን ማፅናቱ በእሳቸው ልብ ውስጥ የሚፈጥረውን የባለ አደራ ቁርጠኝነት መገመት ይቻላል። ከዚህም የተነሳ እሳቸው በስልጣን እያንዳንዷን ቀን ማሳለፍ የሚፈልጉት ይህንን ሕዝብ ለማገልገል እስከቻሉ ድረስ ብቻ ይመስለኛል። ስለዚህ ጊዜው የትጋት እንጂ የስጋት መሆን የለበትም። በእርግጥ እሳቸውን አላሰራ የሚል ቢሮክራሲ ተደቅኖባቸው ሕዝብን ማገልገል ካልቻሉና በዚህም ምክንያት ስልጣናቸውን ከለቀቁ ያኔ መስጋት ያስኬዳል።
ይህንን እንደ ባለ አዕምሮ ሰው ካልኩኝ፥ ደግሞ እንደ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እምነት አንድ ነገር ልጨምር። ባብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈጣሪውን እየተማፀነ፥ የኢትዮጵያም አምላክ ኢትዮጵያን እየጠበቀ እዚህ እንደተደረሰ የአደባባይ ምስጢር ነው። በአንድ ቀን ጀንበር የተወደዱ ክቡር ዶ/ር አብይ፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከተደበቀበት ጓዳ አውጥተው ከፍ አድርገው ሲያሳዩን፥ ሁላችንም በኢትዮጵያዊነታችን ኮርተንና ተደንቀን፥ እጅ ለእጅ በፍቅር ለመያያዝ በቃን። ታዲያ ይህን ሁሉ ከተዐምር ያላነሰ ድርጊት ስናይ፥ የአምላክ እጅ አለበት ብለን ለማመን ለብዙዎቻችን አይቸግረንም። የኢትዮጵያን ትንሳዔ በማብሰር የጀመረው ፈጣሪ፤ አዲሲቷ ኢትዮጵያ እስክትወለድ ድረስ ለጠላቷ ዕድል እንደማይሰጥ በማመን ከስጋት ወደ ትጋት ተሻግረን፥ ሁላችንም የአዋላጅነትን ሚና ለመጫወት ነገ ሳይሆን ዛሬ እንነሳ።
ኢትዮጵያ ትንሳዔን አግኝታለችና ከእንግዲህ ሕዝቧ ሰሚ ያጣ ሕዝብ ተብሎ መጠራቱ ያከትማል። የማታ የማታ ሰሚ ያገኘች ይህች እናት ሀገር፤ ማንም ይሁን ምንም ይህንን የኢትዮጵያ ትንሳዔ ሊቋቋም የሚችል ሃይል ከሰማይ በታች ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም ከሰማይ በላይ ያለው ፈጣሪ፤ በቃ ያላት ወቅት ነውና።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
(ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡)

Read 1117 times