Saturday, 14 April 2018 14:30

የንጉሱ የመጨረሻ ሰዓት!

Written by  ሰአቸ
Rate this item
(1 Vote)

ሁለት  አየርላንዳውያን ወታደሮች፤ በመቅደላ አፋፉ ላይ፣ ከአንድ የከብት ድርቆሽ ክምር አጠገብ፣ አንድ ሰውዬ ሽጉጡን እንደያዘ ቆሞ ያያሉ። ቶሎ ብለው ሊመቱት  አነጣጠሩ። ሰውዬው የዋዛ አይደለም፤ እመር ብሎ በድርቆሹ ጀርባ ተደበቃቸው። የወደሩበትን ትንፋሽ መልሰው ሳይጨርሱ፣ ተኩስ ከወደዚያው አቅጣጫ ሰሙ።
መሣርያቸውን መልሰው አየደገኑ ተያዩና፣ አንዳቸው በስተግራ፣ አንዳቸው በስተቀኝ ወደ ክምሩ ጀርባ ሊሔዱ፣ በጥድፍያ ክምሩን ተጠጉ። ጀርባ ለጀርባ እያስተያዩ፣ መሣርያቸውን እንደደገኑ፣ ቀስ እያሉ፣ ወደ ክምሩ ጀርባው ቢዞ ሩ፣ ያ ቅድም ያዩት ሰውዬ፤ ሪቮልቨር ሽጉጡን በቀኝ እጁ እንደያዘ ተዘርግቷል። ጣቱ ከቃታዋ ላይ እንዳለች ናት። ራሱን በገዛ ጥይቱ መትቷል።
ተጠግተው አዩት። ገና ትንፋሹ አልቆመም።
አንደኛው ወታደር ከሰውየው እጅ ሽጉጡን ወሰደ። ወዲያው ለሁለተኛው ወታደር የሽጉጡን አንድ ጎን አሳየው። ሁለቱም ዓይናቸውን አጉርጠው፣  አንዴ የወደቀውን ሰውዬ፣ አንዴ  መሣርያውን  እያዩ፣ በጥያቄ ተያዩ። በሽጉጡ ላይ የተለጠፈች፣ በራሳቸው ቋንቋ የተጻፈች አጭር ጽሑፍ አለች፤ እንዲህ የምትል:—
***
PRESENTED  BY VICTORIA QUEEN OF
GREAT BRITAIN Z & IRELAND TO THE ODIRUS EMPEROR OF ABYSINIYA AS   A  TOKEN OF  HER  FOR  HER  GRATITUDE FOR HIS       
KINDNESS SERVANT PLOWDEN 1954
***
ለአገልጋይዋ ለቆንሲል ካሜሩን፣ ለሰረገው ችሮታ፣ የብሪታንያና አየርላንድ ንግሥት ቪክቶርያ፣ ለኢትዮጵያው ንጉሥ ለ ‘ቴዎዱሩስ‘  ከ14 ዓመት በፊት ያበረከተችው ንፀስ ማስታወሻ። ወታደሮቹ ሰውዬውን እንደ አዲስ ይመለከቱት ገቡ።
በባዶ እግሩ ነው። በከፊል በረኃብ የተጎዳ ያገሬውን ሰው ዓይነት ነው።  ራሱን ለማትረፍ ሲታገል የቆየው መኾኑ ፊቱ  ያሳብቃል።
ድብን ያለ ቡኒ ፊት ነው። በሚገባ ክርክም ብለው የሚታዩ ስስ ከንፈሮችና ሲበዛ ነጫጭ የሆኑ ሁለት መደዳ ድርድር ጥርሶች። ከግንባሩ ጀምሮ በሦስት ተከፍሎ፣ በወፍራሙ የተሾረበ ጠጉሩ፣ ወደ ኋላው፣ አንገቱ ድረስ ወርዷል።
የቁመቱ ልክ (በኋላ ላይ ተለክቶ፣ በእንግሊዞቹ 5 ጫማ  ከ8 ኢንች) ወደ 1ሜትር ከ73 ገደማ ነበረ።
ድኅረ ሞት ምርመራ ተደርጎለታል።
ቀኝ እግሩ ላይ ሥጋ ለሥጋ የሔደች ጥይት አቁስላዋለች። ላንቃው  ነግሏል፤ እንዳለ የለም። የአፉ ላይኛው ክፍል እንዳለ አርሯል። ከጀርባ ጭንቅላቱ ተበስቷል። ከዚህ መደምደም የቻሉት፣ ዳግማዊ ቴዎድሮስ የሞተው ጥይቱን ጠጥቶ ነበር።
አየርላንዳውያን ወታደሮቹ፣ ነፍሱ ገና ያልወጣችውን የቴዎድሮስ ሁለት እግሮች ይዘው፣ መሬት ለመሬት እየጎተቱ፣ በዛፍ ላይ ታስሮ በሚገኝ የሸራ  አልጋ ላይ ጣሉት። ከዚያ አንድ ሁለቴ ህቅ-- ህቅ ሲል ቆይቶ፣ የመመጨረሻይቱን ህቅታ አሰማ።
ሌሎች ወታደሮችም ተሰብስበው ያዩት ነበር። ከሞቱ ጋር ትንቅንቅ ይዞ  ሳለ፣  ወታደሮቹ ያፌዙበት ነበር። መሬት ለመሬት ሲጎተት ቀሚሱ ተሸብሽቦ  ሆዱ ተገልጦ ነበር። ከመካከላቸው አንዱ ጠጋ ብሎ ሸፈነለት። የተንዘላዘሉትን እጆቹንም በደረቱ ላይ አጋደመለት።
ቀስ በቀስ የሰዉ ቁጥር በዛ።
ቢያንስ አንዴ እንኳ ለማየት ተገፋፋ፤ ተተረማመሰ። የዘመቻው መሪ ሌተና ጄኔራል ሰር ሮበርት ናፒየርም በፈረስ መጣ። ለአንዳፍታ አስከሬኑን ዓይቶ ተመለሰ። ምንም አላለም። የኃዘን መግለጫ ቃል አልወጣውም።
ቆይቶ አስከሬኑ እንዲመረመር የሸራ ቃሬዛ ላይ ተቀመጠ። ጠባቂ አልተመደበለትም። የከበቡት ወታደሮቹ፣ ከቴዎድሮስ ልብስ ቅዳጅ ጨርቅ ለመውሰድ ይናጠቁ፣ ይጨቃጨቁ ጀመሩ።  በደም ከተበከለው የንጉሡ ልብስ እራፊ ጨርቅ ለመውሰድ  ተናነቁ።  አስከሬኑን  ገፈፉት። ጨካኝ አእምሮ ያላቸው ሌሎች ደግሞ፣ በድኑን እየጎነተሉ፣ ያፌዙበትና ይሣለቁበት ገቡ።
ያላንዳች ከፈን  በድኑ ተገላልጦ የመተዉን ወሬ፣  ናፒየር  በሰማ ጊዜ ትዕዛዝ አስተላለፈ።
አስከሬኑ ገና ምርመራ ይደረግበታል፤  እስከዚያ  ድረስ ከነልብሱ መቆየት አለበት።
እቴጌ ጥሩወርቅ፤ ለናፒየር፣ የባላቸውን አስከሬን በሥርዓቱ እንዲቀብሩት ይሰጧቸው ዘንድ ጠየቁ። ተፈቀደላቸው። በተገኙ ቄሶች በጥድፊያ ያለቀች ፍትሐት ሌሊቱን ተደረገ።
በቀጣዩ ቀን፣ መይሳው ካሣ፣ ዳግማዊ
ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ በመቅደላ መድኃኔ ዓለም ተቀበረ።
ጦርነቱን ለመዘገብ መጥቶ ከነበረው የዓይን እማኝ፣ በአሜሪካዊ ጋዜጠኛ ስታንሊ 1874 ኤዲ፣ ከአሳተመው “ኮማሲ ኤንድ ማግደላ” የተሰኘ መጽሐፍ፣ የተዘገበውን  መሠረት በማድረግ የተተረከ ነው።

Read 735 times