Saturday, 14 April 2018 14:35

የዘፈቀደ ስልጣንን፣ አጥፊ የቢሮክራሲ ሁከትን፣ አላስፈላጊ ቁጥጥርን ያስቁሙልን

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(4 votes)

 • ሚኒ ባስ ታክሲዎችን የማጥፋት ዘመቻ? በይፋ የሚፎከርለት፣ በግላጭ የሚካሄድ ዘመቻ! ይሄ መቆም አለበት!
  • “አረንጓዴ ልማት”፣ “የካርቦን ልቀት” በሚሉ የተሳከሩ ሃሳቦች ሳቢያ ፋብሪካ መዝጋትና ታክሲዎችን ማጥፋት ይቁም።
  • ይሄ በዜጎች ኑሮ ላይ መቀለድ ነው። ይህንን ክፋት በማስወገድ ትልቅ ቁምነገር ይስሩ - አዲሱ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ። -     እንደ አሜረካው ፕ/ር ዶናልድ ትራምፕ
  • በዋጋ ቁጥጥር፣ በስምሪት ቁጥጥር፣ በኮታ ቁጥጥር መፍትሄ አልተገኘም። ችግር ከማባባስ በቀር!
  • በዳቦ ቤቶች ቁጥጥር ሳቢያ፣ ዳቦ እየጠፋ ነው። እስከ መቼ ነው በዳቦና በስንዴ ዋጋ ቁጥጥር!
          
    ስራ የጠፋ ይመስል፣ ሚኒባስ ታክሲዎችን የማጥፋት ዘመቻ ምን የሚሉት ስራ ነው? ከዚህስ፣ “በስራ ፈትነት” ደሞዝ ቢከፈላቸው ይሻል ነበር። አሁንኮ፣ “ስራን በማጥፋት ዜጎችን ማንገላታት” እንደ ስራ የተቆጠረ መስሏል።
ሲሆን ሲሆን፣ ቁምነገር መስራት እንጂ… ለምሳሌ፣…
በስንትና በስንት ወጪ የተሰሩ አስፋልት መንገዶች፣ የመኪና ማቆሚያ እየሆኑ መንገዶች እየተጣበቡ ትራፊክ መጨናነቅ ነበረበት? ይህንን በዝምታ የሚያዩ ወይም መፍትሄ ለማበጀት የማይሞክሩ የትራንስፖርት ቢሮ ባለስልጣናት፣… በተቃራኒው፣ ሚኒባስ ታክሲዎችን ለማጥፋት እንቅልፍ አጥተው የሚታትሩ ይመስላሉ።
ሚኒባስ ታክሲዎችን ለማጥፋት፣ ለአመታት ያለማቋረጥ በተካሄደው የትራንስፖርት ቢሮ ዘመቻ ሳቢያ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ከጥዋት እስከማታ በትራንስፖርት እጥረት እየተንገላቱ ነው።
እንዲህ አይነት አይን ያወጣ፣ በጠራራ ፀሐይ የሚፈፀም፣ በይፋ የታወጀና እንደ ጀግንነት በየእለቱ እየተፎከረለት ለአመታት የዘለቀውን ዘመቻ ማስቆም የማይችል ፓርቲና መንግስት፣… ስራው ምንድነው?
ሚኒባስ ታክሲዎችን ማጥፋትና ዜጎችን በትራስፖርት እጥረት ማንገላታት አስፈላጊ የሆነበት አንዳት ተዓምረኛ ምክንያት ይኖር ይሆን እንዴ? ሰበብና ማመካኛማ አይጠፋም። መቼም ቢሆን፣ ያለ ሰበብና ያለማመካኛ የሚፈፀም ጥፋትና ክፋት የለም። ሁሌም!
የነዚህ ሰበብስ ምንድነው? ያው፣… የተለመደው “የአረንጓዴ ልማት” ዲስኩር ነው ሰበባቸው። “የካርቦን ልቀት ወደ ዜሮ መውረድ አለበት”… ምናምን ብለው የሚያወሩት ነገር ነው - ማመካኛቸው።

አረንጓዴ ልማት ማለት አረንጓዴም አይደለም፤ ልማትም አይደለም።
“የካርቦን ልቀትን ማስወገድ” የሚሉ ዲስኩሮችን በየእለቱ የሚሰማ ሰው፣ ትርጉም የለሽ ቀልድ ሊመስለው ይችላል - በሕይወትና በኑሮ ላይ፣ ውጤትም ሆነ መዘዝ የሌለው፣ “የስራፈት ቢሮክራቶች ኦና መነባንብ” ወይም “የተሳከረባቸው ምሁራን የሚያዘወትሩት አስመሳይ የቃላት ሰርከስ” ሆኖ ሊታየው ይችላል። ቢመስለው አይገርምም። ግን ተሳስቷል። የጥፋትና የክፋት መዘዝ አለውና።
አዎ፣ “የካርቦን ልቀትን ማስወገድ፣… የአለም ሙቀትን መቀነስ” የሚለው የአገራችን ባለስልጣናትና የቢሮክራቶች ዲስኩር፣.. ከእውነተኛ መረጃ የራቀ፣ ኦና መነባንብ ነው።
አዎ፣ “ወደ ታዳሽ ሃይል መሸጋገር፣… ወደ አረንጓዴ ልማት መራመድ ያዋጣል… ምናምን”… የሚለው የአላዋቂዎች የተለመደ ወሬ፣ ከእውቀት የራቀ ባዶ የቃላት ሰርከስ ነው። ለዚህም ነው፣ መዘዝ ሲያስከትል የሚታየው። ከእውነትና ከእውቀት የራቀ መነባንብና የቃላት ሰርከስ በነገሰበት ቦታ ሁሉ፣… የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣ ከኑሮ ጋር የሚያጣላ፣ ከድህነት ጋር የሚያቆራኝ፣ የመሻሻል ተስፋን የሚበጥስ መዘዝ የሚያመጣ ክፉ ጥፋት የተደገሰበት ቦታ ይሆናል። በዓለም፣ እጅግ ድሃ፣ ለአቅመ ኢንዱስትሪ ያልተራመዱና የካርቦን ልቀት የሌላቸው አስር ኋላቀር አገራት ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን እያወቁ፣ ስለካርቦን ልቀት ማነብነብ ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም - ከጥፋትና ከክፋት በስተቀር።
በሌላ አነጋገር፣ ኑሮን የማይነካ ኦና መነባንብ የመሰለን የቢሮክራቶች ዲስኩር፣ በተግባር ኑሮን የሚነካ፣ የታክሲ እጥረትን የሚፈጥርና ዜጎችን የሚይንገላታ የጥፋት መነባንብ ነው።
ባዶ የቃላት አክሮባት የመሰለን የወገኞች ስብከት፣… “የካርቦን ልቀት አይፈቀድም” እያሉ ፋብሪካዎችን በመዝጋት እርካታ ለማግኘት ለሚሞክሩ የክፋት ሱሰኞች የሚዳርግ መጥፎ የቃላት ሰርከስ ነው። ባለፋብሪካዎች ቁጭ ብድግ እንዲሉለት በማዋከብና አዛዥ ናዛዥ በመሆን እርካታን ለመግኘት የሚደናበሩ ክፉዎች፣… ካሰኛቸው የበርካታ ሰራተኞችን ኑሮ የመዝጋትና የመክፈት ስልጣን ያስጎመጃቸዋል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ ከቀዳሚ ስራቸው መካከል አንዱ፣… ይህንን “የካርቦን ልቀት”፣ “የአለም ሙቀት”፣ “የአካባቢ ጥበቃ”፣ “አረንጓዴ ልማት”… በሚሉ የተሳከሩ ዲስኩሮች አማካኝነት እየተስፋፋ የመጡ የተሳከሩ የጥፋትና የክፋት ዘመቻዎችን ማስቆም ሊሆን ይገባል።
ለምን? ከእውነትና ከእውቀት የራቁ ዲስኩሮች ናቸውና። የሰውን ኑሮ የሚያጎሳቁሉ ተግባራትንና ጥፋቶችን የሚያስከትሉ ዲስኩሮች ናቸው። በተቃራኒው፣ እነዚህ ማስወገድ ትልቅ ቁም ነገር ነው። ለምን? ከእውነትና ከእውቀት የሚበልጥ መተማመኛ፣ ከዜጎች ኑሮ የሚበልጥ አላማ፣ ለዚህም በብቃት ከመስራት የበለጠ ክብር የለም።
አረንጓዴ ልማት ማለት አረንጓዴም አይደለም፤ ልማትም አይደለም። የአካባቢ ጥበቃ ማለት፣ ችግኝ መትከል፣ አካባቢን ለሰው ኑሮ ተስማሚና አመቺ ማድረግ አይደለም (ይሄማ “አካባቢን ይለውጣል” ተብሎ የሚወገዝ ነው)። “አካባቢን ከሰው ንክኪ ነፃ ማድረግ ማለት ነው” የአካባቢ ጥበቃ። እንደወገኞቹ አባባል፣ “ወንዝ መነካት የለበት - ለመስኖ ለኤሌክትሪክ”። እንደ አጥፊዎቹ አባባል፣ “መሬት መነካት የለበትም - የሚታረስ መሬት መቀነስ አለበት። የሰው መኖሪያ አካባቢም መቀነስ አለበት - ከከተማው መሬት ውስጥ አንድ ሶስተኛው ለፓርክና ለእፀዋት መለቀቅ አለበት”።
“ማዕድን መነካት የለበትም - ነዳጅ መጠቀም፣ መኪና መንዳት… እንዲቀንስ ማድረግ ግዴታ ነው” እንደ ክፉዎቹ አባባል።
አዎ፣ እነዚህ ከአላዋቂዎች፣ ከአጥፊዎችና ከክፉዎች የምንሰማቸው አባባሎች፣ “ኦና መነባንብ፣ ባዶ የቃላት ሰርከስ” ይመስላሉ። ግን፣… ኦና ወይም ባዶ አይደሉም። ህይወትን የሚነኩ፣ ኑሮን የሚያጎሳቁሉ የጥፋትና የክፋት ድግሶች ናቸው።
Ethiopia’s Climate-Resilient Green Economy strategy ገፅ 169 ላይ የቀረበውን መረጃ መመልከት ትችላላችሁ። አዎ እቅዱ የወጣው ከ8 ዓመት በፊት ነው። አዎ፣ በተግባር ኑሮን ለመንካት የማይበቃ ወገኛ ወሬ ይመስላል። ግን፣ ይሄውና እየነካን ነው።
ለአውቶቡስ ብቻ የሚያገለግሉ መንገዶችን በማዘጋጀት፣ የአነስተኛ መኪኖችንና የሚኒባስ ታክሲዎችን እንቅስቃሴ መግታት እንደ አንድ ትልቅ እቅድ ተፅፏል። በብዙ ሚሊዮን ብር ሃብት የሚገነቡ መንገዶችን፣ አውቶቡስን ብቻ እንዲያገለግሉ ማድረግ፣… ከንቱ የሃብት ብክነት እንደሆነ፣ የትራንስፖርት እጥረትን በማባባስ ዜጎችን ለእንግልት እንደሚዳርግ ግልፅ ነው - ላልተሳከረበት ጤናማ ሰው። ለዚህም ነው፣ እንዲህ አይነት የተሳከ ሃሳብና እቅድ ሲያጋጥመን፣ በቸልታ የምናልፈው - በተግባር አይፈፀምም በሚል ከንቱ ተስፋ። ግን፣ ይሄውና ሲፈፀም እያየነው ነው።
በአዲስ አበባ፣ “ለአውቶቡስ ብቻ” በሚል መንገዶችን መዝጋትና ሚኒባስ ታክሲዎች እንዳይሰሩ መከልከል ተጀምሯል። እኮ ለምን? ሃብትን ለክንቱ ብክነት፣ ዜጎችን ለተጨማሪ እንግልት የሚዳርግ እቅድ ተዘጋቶለት እንዴት በተግባር ይፈፀማል? ለምን? የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ!
ምን ያህል ነው የሚቀንሰው? እንግዲህ በአለም ከሚፈጠረው የካርቦንዳይኦክሳይድ ጋዝ… ማለትም 1,000,000 እጅ ውስጥ፣ 1 ብቻ ለመቀነስ እንደሚያስችል የስትራቴጂው ሰነድ ይጠቁማል። (ማለትም ከ40ሺ ሜቶ ውስጥ፣ 0.04 ሜቶ መቀነስ!... እና ከዚህ ምን ጥቅም እናገኝበታለን? ምንም፣… ከከንቱ ወሬ በቀር ጠብ የሚል ጥቅም የለውም)። እንግዲህ ለዚህ ባዶ ከንቱ ወሬ ነው፣ የድሃ አገር ሃብት የሚባክነው። ዜጎች በታክሲ እጦት የሚሰቃዩት።
የትራንስፖር ቢሮ ግን፣ ጭራሽ ሰሞኑን ፎክሯል። ሚኒባስ ታክሲዎች ከከተማዋ መንገዶች ሳያስወጣ እንደማያርፍ ገልጿል።
ነፃነትን ማስከበር ማለት እንዲህ የዜጎችን የኑሮ መተዳደሪያ ለማጥፋት፣ ትራንስፖርት ፈላጊ ዜጎችን ለማንገላታት በአደባባይ የሚካሄዱ ዘመቻዎችን በአፋጣኝ፣ ሳይውል ሳያድር እንዲወገድ ማድረግ ነው።

Read 3398 times