Print this page
Saturday, 14 April 2018 14:40

500 ሶርያውያን የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ቅዳሜ በሶርያዋ ዱማ ከተማ በተፈጸመው ጥቃት የኬሚካል ጦር መሳሪያ ሰለባ በመሆን ለህመም የተዳረጉ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር 500 ያህል መድረሱን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ ህጻናትን ጨምሮ ለህመም የተዳረጉት 500 ያህል ሶርያውያን የመርዛማ ኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የሚጠቁሙ የመተንፈሻ አካላትና የአእምሮ ስርዓት ችግር ምልክቶች እንዳሳዩ በሃኪሞች ተረጋግጧል ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የበሽር አልአሳድ መንግስት 70 ሰዎች ያህል ለህልፈተ ህይወት ተዳርገውበታል የተባለውን የምስራቃዊ ጉታ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቃት አለመፈጸሙን በመግለጽ፤ አለማቀፍ ተቋማት ጉዳዩን እንዲያጣሩ የጠየቀ ሲሆን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሶርያ አምባሳደር ሁሳም ኢዲን አላም በበኩላቸው፤ የአለም የጤና ድርጅት ይፋ ያደረገውን መረጃ፣ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው ሲሉ ማጣጣላቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
በሶርያ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቃት ሰለቦችን የማከምና የመንከባከብ ተልዕኮ የተሰጣቸው 800 የአገሪቱ የጤና ሰራተኞችን ማሰልጠኑን የጠቆመው የአለም የጤና ድርጅት፤ በምስራቃዊ ጉታ ጥቃት ለደረሰባቸው ለእነዚህ ዜጎች አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ለመስጠት እንዲቻል የበሽር አል አሳድ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቁንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ የበሽር አልአሳድ መንግስት የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቃቱን አልፈጸምኩም ቢልም የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማርኮን በበኩላቸው፤ ጥቃቱን መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ መረጃ ማግኘታቸውን ከትናንት በስቲያ ገልጸዋል፡፡
ለጥቃቱ ሶርያንና ሩስያን ተጠያቂ ያደረጉት አሜሪካና እንግሊዝን ጨምሮ የተለያዩ የአውሮፓ አገራት መንግስታት፤ በመርዛማ ጋዝ ጥቃቱ ብዙዎችን ሰለባ አድርገዋል ባሏቸው የሶርያው ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጋራና በተናጠል እየተወያዩ እንደሆነና የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ ወታደራዊ እርምጃው እንዳይወሰድ ማስጠንቃቃቸው ተዘግቧል፡፡

Read 1679 times
Administrator

Latest from Administrator