Saturday, 14 April 2018 14:44

ለአንድ ምሽት 792 ሺ ዶ. የሚያስከፍል የጠፈር ሆቴል ሊከፈት ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 የአሜሪካው ኩባንያ እጅግ ዘመናዊ እንደሆነ የተነገረለትን የጠፈር ላይ የቅንጦት ሆቴል በመክፈት፣ ለአንድ ምሽት 792 ሺህ ዶላር የመክፈል አቅም ላላቸው የናጠጡ ባለጸጎች አገልግሎት ሊሰጥ በዝግጅት ላይ  እንደሚገኝ ማስታወቁ ተዘግቧል፡፡
ተቀማጭነቱን በሂውስተን ያደረገው ኦሪዮን ስፓን የተባለ ኩባንያ ከሶስት አመታት በኋላ በሚጀምረው በዚህ የቅንጦት የጠፈር ሆቴል ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ደንበኞችን ለማስተናገድ ማሰቡን የዘገበው ብሉምበርግ፤ ደንበኞቹ በህዋው ሆቴል ለሚኖራቸው የ12 ቀናት ቆይታ እያንዳንዳቸው 9.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍሉ አመልክቷል፡፡
ኩባንያው በሁለት የበረራ ባለሙያዎች በምትመራዋና 35 ጫማ በ14 ጫማ ስፋት ባላት መንኮራኩር ላይ በሚከፍተው በዚህ የጠፈር ላይ ዘመናዊ ሆቴል፤ የመክፈል አቅም ላላቸው ደንበኞች ከምድር በ200 ማይል ርቀት ላይ ከመሬት ስበት ውጭ ሆነው ለቀናት ሙሉ መስተንግዶ የሚያገኙበትን ዕድል ለመፍጠር ዝግጅቱን እያጧጧፈ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በአለማችን የጠፈር ቱሪዝም ታሪክ በግላቸው ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጠፈር የተጓዙት አሜሪካዊው ባለሃብት ዴኒስ ቲቶ እንደነበሩ ያስታወሰው ዘገባው፤ ግለሰቡ በ2001 ወደ አለማቀፉ የጠፈር ማዕከል ላደረጉት ጉዞ 20 ሚሊዮን ዶላር ያህል መክፈላቸውንም ጠቁሟል፡፡

Read 3546 times