Saturday, 14 April 2018 14:51

‹‹የሩጫዎች ሙሽሪት›› አትሌት መሰለች መልካሙ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)


    ሰሞኑን ለየት ያለ መልዕክት ደረሰኝ፡፡ በፅሁፍ የተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ወይንም በመግለጫ ላይ እንድገኝ የሚጋብዝ ጥሪ አልነበረም፡፡ የሙያ ባልደረባዬ በመጀመርያ መልዕክቱን ያደረሰኝ በስልክ ነው፡፡ አትሌት መሰለች መልካሙ ሰርግ ጠርታሃለች በማለት ጥሪው እንዳስደሰተኝ በመግለፅ እዚያው እንገናኝ ብለን ተለያየን፡፡
አዎ የሠርግ ካርዱ ደርሶኛል፡፡ “ይድረስ ለወዳጃችን ይላል… እንደምን ሰንብተዋል፡፡ እኛም ባለንበት በእግዚአብሄር ቸርነት በጣም ደህና ነን፡፡ ይኸው እንደ ወግ ልማዳችን ልጃችን አትሌት መሰለች መልካሙ እና አቶ አብርሃም በቀለ የፍቅር አጋር ሊሆኑ ተጫጭተዋል፡፡ እኛም ይሁን ብለን የሰርጉን ቀን ቆርጠናል፡፡…. ሚያዚያ 7 በምናደርገው የእራት ግብዣ ላይ ብቅ ብለው ያዘጋጀነውን ድግስ አብረን ተቋድሰን እንመርቃቸው፡፡ ወዲያውም ስንጫወት እናመሻለን፡፡ ታዲያ እንዳይቀሩ የቀሩ እንደሆነ ግን ማርያምን እንቀየምዎታለን……
አክባሪዎ ወይዘሮ የአለምወርቅ አዘነ
እና አቶ ይታያል መልካሙ
በዚህ አጋጣሚ አትሌት መሰለች መልካሙንና ቤተሰቧን በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በስፖርት ጋዜጠኝነት እኔም የናንተ ቤተሰብ አክባሪ ነኝ፡፡ በዚህ የስፖርት አድማስ አምድ የታሪክ ማስተወሻ ላይ ስለ አትሌት መሰለች መልካሙ የሩጫ ዘመን ለመፃፍ አጋጣሚውን ስፈልግ ነበር፡፡ በነገው እለት ከአቶ አብርሃም በቀለ ጋር በሠርግ መሞሸሯን ምክንያት በማድረግ የሩጫ ገድሏ እንዲህ አቅርቤላችኋለሁ፡፡
 ሙሉ ስሟ መሰለች መልካሙ ኃይለእየሱስ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ 360 ኪሎሜትሮች ርቃ በምትገኘው ደብረማርቆስ ተወልዳለች። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ከ18 ዓመታት በላይ በመስራት ከፍተኛ እውቅና እና ክብር አግኝታለች፡፡ ምንም እንኳን የሩጫ ዘመኗን በአገር አቋራጭ ውድድር ብትጀምርም በትራክ ላይ በ5ሺ ሜትር እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች ላይ በመሮጥም ከ8 የውድድር ዘመናት በላይ ልምድ አላት፡፡ በቤት ውስጥ አትሌቲክስ፤ በጎዳና ላይ ሩጫ፤ በተራራ ላይ ሩጫዎች በግማሽ ማራቶንና ማራቶኖችም ተወዳዳሪ በመሆን ተሳክቶላታል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ስታድዬም በተካሄደው 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከታዩ አስደናቂ ውድድሮች የማይረሳው የሴቶች አምስት ሺ ሜትር ውድድር ነበር። በ5ሺ ሜትር የምንግዜም ምርጥ ሯጭ የሆነችውን መሰረት ደፋር በማሸነፍ የአፍሪካ ሻምፒዮን ሆና የወርቅ ሜዳልያውን አትሌት መሰለች ስትጎናፀፍ ሙሉ ስታድዬም ቆሞ ነበር ያጨበጨበላት። በሴቶች 10ሺ ሜትር ደግሞ በ2009 እኤአ ላይ  ያስመዘገበችው 29:53.80 የሆነ ጊዜ ከቻይናዋ የዓለም ሪከርድ ባለቤት ዋንግ ዡንክስያ ቀጥሎ ለ7 ተከታታይ የውድድር ዘመናት በ2ኛ ደረጃ ለመቀመጥ የበቃ የምንግዜም ፈጣን ሰዓት ነበር፡፡ በሪዮ ኦሎምፒክ ይህን ደረጃዋን በኦሎምፒክ ሻምፒዮናዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት አልማዝ አያና 29:53.80 በሆነ ጊዜ የተረከበችውና የኢትዮጰያ ሪከርድ ሆኖ የሚገኝ ነው፡፡ በሴቶች የ10ሺ ሜትር ሩጫ ታሪክ ከ30 ደቂቃ በታች ከገቡ 10 አትሌቶች አንዷ ስትሆን ይህን የሰዓት ገደብ ካስመዘገቡ አምስት የኢትዮጵያ ሴት ሯጮችም አንዷ ናት፡፡
ሩጫን ከ18 ዓመታት በፊት የጀመረችው የአባቷን ተቃውሞ በመቋቋም ሲሆን በደብረማርቆስ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ልምምድ በመስራት ነበር፡፡ በደብረማርቆስ ከተማ በተካሄዱ የተለያዩ ውድድሮች በተለይ በአገር አቋራጭ ሩጫዎች ስኬታማ ከሆነች በኋላ ክልሏን በመወከል በኢትዮጵያ የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና የምትሳተፍበት እድል ተፈጠረላት፡፡ በወጣቶች ውድድር ጃንሜዳ ላይ ተሳትፎ አድርጋ በ11ኛ ደረጃ ነበር የጨረሰችው፡፡ ከዚህ ውድድር በኋላ ክልሏን በመወከል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ በቃች በትራክ የ1500 ሜትር ውድድር ተሳታፎ በመሆን ባሳየችው ልዩ ብቃት በመብራት ሃይል የአትሌቲክስ ክለብ የምትቀጠርበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ በዚህ መሰረት ከምትኖርበት የደብረማርቆስ ከተማ የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን በማቋረጥ ወደ አዲስ አበባ መጥታ በመብራት ኃይል ክለብ አትሌትነት ሙሉ ለሙሉ ወደሩጫ ስፖርት ገብታለች፡፡ አባቷም ሩጫን ሙያዋ አድርጋ እንደምትዘልቅ በመረዳታቸው ድጋፋቸውን በዚህ ወቅት መስጠት ጀምረዋል፡፡ በማንኛውም ውድድር ለሁሉም ተፎካካሪ ግምት ሰጥታ ለማሸነፍ እንድትወዳደር ነበር የአባቷ ምክር፡፡  በመጀመርያው ዓመት በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመካተት ህልም የነበራት ቢሆንም አልተሳካላትም፡፡ ከ2003 እኤአ ጀምሮ ወደ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ በወጣቶች ደረጃ መሳተፍ ጀምራለች የመጀመርያ ውድድሯ የነበረው በሉዛን የተደረገው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሲሆን፤ ጥሩነሽ ዲባባ ባሸነፈችበት የወጣቶችውድድር 4ኛ ደረጃ አግኝታ ነበር፡፡ ከዚያም በ2004 እኤአ ላይ በኢትዮጵያ የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና በወጣቶችውድድር አሸንፋ በአዋቂዎች የ4ኪሜትር ውድድር ደግሞ 4ኛ ደረጃ በማስመዝገብ ለዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመመረጥ እድሏን አሰፋች፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ መጥቃ የወጣችበት የውድድር ዘመን በ2004 እኤአ ሲሆን በወጣቶች ምድብ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናንና የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች በድርብ ድል የተቀዳጀችበት ነበር፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን በዋናው የአዋቂ ሴቶች አጭር ርቀት 4 ኪሎሜትር ውድድር አራተኛ እንዲሁም በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ በ5ሺ ሜትር 4ኛ ደረጃ ነበራት፡፡ይህ ልምዷን በማጠናከር በ2004 እና በ2005 እኤአ የውድድር ዘመናት በአገር አቋራጭ ውድድሮች ብቻ ሳይሆን፤ በትራክ እና የጎዳና ላይ ሩጫዎች ከ1500 ሜትር እስከ 10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ከ16 በላይ ውድድሮች አድርጋለች፡፡
ከወጣቶች ምድብ ወደ አዋቂ ደረጃ ከተሸጋገረች በኋላ ከፍተኛ የሜዳልያ ውጤት ለማስመዝገብ የበቃችው በ2006 እኤአ ላይ ነው፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአጭር ርቀት 4 ኪሜትር እና በረጅም ርቀት 8 ኪሜትር ውድድሮች ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎች እና በቡድን ደግሞ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን በመውሰድ ነበር። ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በግሬት አየርላንድ ራን የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ላይ በስፍራው ሪከርድ 31:41  በማሸነፍ ተሳክቶላታል፡፡
ከጎዳና ላይ ሩጫው በኋላ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በመመለስ በ2007 እኤአ ላይ በድጋሚ የነሐስ ሜዳልያ ከመውሰዷም በላይ በቡድን ተጨማሪ የወርቅ ሜዳልያ አስገኝታለች፡፡ በተመሳሳይ የውድድር ዘመን ላይ ደግሞ ወደ ትራክ በመግባት በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ አትሌት መሰረት ደፋርን ተከትላ በመግባት በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ አግኝታለች። በዚያው የውድድር ዘመን ማብቂያ ላይ  በ5ሺ ሜትር በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 6ኛ ደረጃ ነበራት፡፡
በ2007 እኤአ ላይ በአንድ የውድድር ዘመን ከጎዳና ላይ ሩጫ ተነስታ በአገር አቋራጭ ከዚያም በትራክ በመወዳደር የተለየ አቅም ነበር ያሳየችው፡፡ በ2008 እኤአ ደግሞ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ3ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ አገኘች። የወርቅ ሜዳልያው የአትሌት መሰረት ደፋር ነበር፡፡ በዚያው የውድድር ዘመን ከፍተኛ ልምድ ባካበተችበት የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በዘጠነኛ ደረጃ ብትጨርስም ይህን የሚያካክስ ውጤት ደግሞ አሳክታለች፡፡ በ2008 እኤአ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተስተናገደው 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አትሌት መሰረት ደፋርን ቀድማ በመግባት የወርቅ ሜዳልያ በ5ሺ ሜትር የተጎናፀፈችበት ነበር፡፡ ይህ ውጤቷም በቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ ለተካሄደው 29ኛው ኦሎምፒያድ ተሳትፎ አብቅቷታል፡፡ በ5ሺ ሜትር በሆነ ጊዜ በስምንተኛ ደረጃ ነበር የጨረሰችው፡፡ ከዓመታት በኋላ በዚሁ ኦሎምፒክ በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ የወሰደችው የቱርኳ ኤልቫን አብይ ለገሰ በዶፒንግ ውጤቷ በመሻሩ፤ አትሌት መሰለች መልካሙ በተሳተፈችበት የመጀመርያ ኦሎምፒኳ በ5ሺ ሜትር የ7ኛ ደረጃ እንዲመዘገብላት ሆኗል፡፡
በ2009 እኤአ ላይ ወደ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ስትመለስ የሜዳልያ ውጤት ነበራት፡፡ በረጅም ርቀት የ8 ኪሎሜትር ውድድር የነሐስ ሜዳልያ ወሰደች፡፡  በጥቂት ወራት ውስጥ ደግሞ በሆላንዷ ኡትርቼት በተካሄደ የ10ሺ ሜትር ሩጫ አዲስ የአፍሪካና የኢትዮጵያ ሪከርድ 29:53.80 በሆነ ጊዜ አስመዘገበች፡፡ አስቀድሞ በጥሩነሽ ዲባባ የተያዘውን የአፍሪካና የኢትዮጵያ ሪከርድ 29:54.66 የሆነ ጊዜ በማሻሻል ነበር፡፡ ያን የውድድር ዘመን የመጀመርያውን የዓለም ሻምፒዮና ከፍተኛ ውጤት በ10ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ በመጎናፀፍ አጠናቀቀች፡፡
በ2010 እኤአ ላይ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በመሳተፍ  የለመደችውን የነሓስ ሜዳልያ በረጅም ርቀት ለመውሰድ የበቃች ሲሆን፡፡ በዚያው የውድድር ዘመን በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ በ10ሺ ሜትር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳልያ ተጎናፅፋለች፡፡ የውድድር ዘመኑን ያገባደደችው በናይጄርያ ኦቡዱ ግዛት በተካሄደ የአፍሪካ ረየተራራ ላይ ሩጫ ጫምፒዮንሺፕ Obudu Ranch International Mountain Race አስደናቂ ድል በማስመዝገብ ነበር፡፡ በ2011 እኤአ ላይ ትልቁ ውጤታ በጃንሜዳ አገር አቋራጭ ለ4ኛ ጊዜ ማሸነፏ ነበር፡፡
ከ2012 እኤአ ወዲህ ያለፉትን አምስት የውድድር ዘመናት ደግሞ ዋና ትኩረቷ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ግማሽ ማራቶንና ማራቶኖች ሆነዋል፡፡ በ2012 እኤአ በጀርመን ፍራንክፈርት ማራቶኑን ስታሸንፍ 2:21:01 በሆነ ጊዜ የግሏን ፈጣን ሰዓት እና የስፍራውን ሪከርድ አስመዝግባለች፡፡ ይህ የመሰለች መልካሙ የማራቶን ሰዓት ከኢትዮጵያ ሴት ማራቶኒስቶች ፈጣን ሰዓቶች አንዱ ነው፡፡ በ2013 እኤአ ላይ በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ የራስ አልካሂማህ ግማሽ ማራቶን ስትወዳደር በ7ኛ ደረጃ ብትጨርስም በርቀቱ የግሏን ፈጣን ሰዓት 1:08:05  አስመዝግባለች፡፡
ባለፉት 4 የውድድር ዘመናት  በተሳተፈችባቸው የማራቶን ውድድሮች የተሳካላት ናት፡፡ በ2013 እ.ኤ.አ ላይ ሞስኮ ባስተናገደችው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን ብትሳተፍም ውድድሩን ለመጨረስ አልቻለችም፡፡ የመጀመሪያ ማራቶን የሮጠችው በ2012 እኤአ በፍራንክፈርት ማራቶን ሲሆን፣ ውድድሩን ስታሸንፍ 2:21:01 በሆነ ጊዜ ሲሆን  ብርቀቱ የተመዘገበላት ምርጥ ሰዓቷ ነው፡፡ በዱባይ ማራቶን  ሁለት ጊዜ ስትሳተፍ በ2016 እኤአ ላይ በ2፡22፡29 በሆነ ጊዜ ሦስተኛ ደረጃ ማግኘቷ ይታወሳል፡፡  በ2017 እኤአ ደግሞ አልተሳካለትም ከዱባይ ማራቶን ባሻገር በጀርመንና በሆላንድ ከተሞች ሁለት ትልልቅ ማራቶኖችን አሸንፋለች፡፡ በተለይ  በጀርመን ሀምቡርግ ካስመዘገበችው ድል ቀጥሎ ሁለተኛውን የትልቅ ከተማ ማራቶን አሸናፊነት ክብር በአምስተርዳም ለመቀዳጀት መብቃቷ ይጠቀሳል፡፡
በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ማህበረሰብ፤ በዓመለሸጋነቷ፤ በልምምድ ትጋቷ እና በውድድር ላይ ለቡድን ውጤት በምታበረክተው አስተዋፅኦ የምትከበረው አትሌት መሰለች መልካሙ በአገር አቀፍ እንቅስቃሴዎችም ንቁ ተሳታፊ ናት፡፡ ከ4 ዓመታት በፊት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያ የሚውል 20 ኤል.ሲ.ዲ ቴሌቪዥን በስጦታ ያበረከተች ሲሆን ባለ 32 ኢንች ኤል.ሲ.ዲ ሳምሰንግ ቴሌቪዥኖች  ከ153 ሺህ ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸዋል፡፡ በ2017 ላይ ግን አንድ አሳዛኝ ገጠመኝ ነበር፡፡ አትሌት መሰለች መልካሙን ጨምሮ አምስት አትሌቶች ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ደረቅ ቼክ በመጻፍ ማናጀር አታሏቸው መነጋገርያ ሆነው ነበር፡፡ በማታለል ወንጀል የተከሰሰው የአትሌቶች ማናጀር ወላይ አማረ የሚባል ሲሆን በወቅቱ የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንዳመለከተው ተከሳሽ ወንጀሉን በአትሌቶቹ ላይ የፈፀመው ከ2008 እስከ 2009 ዓ.ም ባለው ጊዜ ነው።
ማናጀሩ  ከአምስቱ አትሌቶች በተለያዩ ጊዜና ሀገራት ባደረጉት ውድድር የተሳትፎ የኮንትራት ውል ክፍያን ገንዘብ ሳይኖረው በአዋሽና በሌሎች ባንኮች ሂሳቡ ውስጥ ገንዘብ እንደሌለው እያወቀ ደረቅ ቼክ በመጻፍ ማታለሉ በክሱ ተጠቅሷል። በዚህም መልኩ ለአትሌት አፀደ ፀጋዬ ከ1 ሚሊየን 15 ሸህ ብር በላይ፣ ለአትሌት መሰለች መልካሙ ከ2 ሚሊየን 368 ሺህ ብር በላይ እንዲሁም ለአትሌት በላቸው አለማየሁ 230 ሺህ ብር እና ለሌሎችም አትሌቶች ተመሳሳይ የገንዘብ መጠን ደረቅ ቼክ በመጻፍ የማታለል ተግባር መፈጸሙ በክሱ ተዘርዝሯል፡፡
 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሽ ወላይ አማረ በ10 ዓመት ከ11 ወራት ፅኑ እስራትና በ2 ሺህ 500 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
በአሁኑ ወቅት አትሌት መሰለች መልካሙ ለኢትዮጵያ አትሌቶች ዋና ተምሳሌት ሆና የምትጠቀስ ናት፡፡  የሩጫ መደቦቿ 1500ሜ፤ 3000ሜ፤ 5000ሜ ፤ 10,000ሜ፤ የቤት ውስጥ አትሌቲክስ፤ አገር አቋራጭ፤ የጎዳና ላይ ሩጫዎች፤ ግማሽ ማራቶንና ማራቶን ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ለረጅም ጊዜ ያገለገለችበት ክለብ  መብራት ኃይል ሲሆን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከአሰልጣኝ ዶክተር መስቀል ኮስትሬ እንዲሁም ከዶክተር ይልማ በርታ ጋ ሰርታለች። ለረጅም ጊዜ ማናጀሯ ሆነው ያገለገሏት የግሎባል አትሌቲክስ ኮሚኒኬሽኑ ሆላንዳዊው  ጆስ ሄርማንስ ናቸው፡፡
በዓለም የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታስቲክስ ድረገፅ ኤአርአርኤስ (Arrs) የመረጃ መዝገብ መሰረት አትሌት መሰለች መልካሙ በሩጫ ዘመኗ 41 ውድድሮችን ያሸነፈች ሲሆን በይፋ የሚታወቅ የገንዘብ ሽልማቷ ከ701ሺ 150 ዶላር በላይ ነው፡፡
ፈጣን ሰዓቶቿ
- በ1500 ሜትር – 4:07.52 (2007)
- በማይል ሩጫ– 4:33.94 (2003)
- 2000 ሜትር ቤት ውስጥ - 5:39.2 (2007) 12ኛው የምንግዜም ፈጣን ሰዓት
• በ3000 ሜትር ትራክ- 8:34.73 (2005)
• 3000 ሜትር ቤት ውስጥ - 8:23.74 (2007) 4ኛው የምንግዜም ፈጣን ሰዓት
• 5000 ሜትር ትራክ– 14:31.91 (2010)
• 10,000 ሜትር ትራክ – 29:53.80 (2009) 6ኛው የምንግዜም ፈጣን ሰዓት
• 10 ኪ ሜትር ጎዳና – 31:17 (2013)
• 15 ኪ ሜትር ጎዳና  - 47:54 (2013)
• 20 ኪ ሜትር ጎዳና  - 1:04:32 (2013)
• ግማሽ ማራቶን - 1:08:05 (2013)
• 30 ኪ ሜትር ጎዳና - 1:39.21 (2014)
• ማራቶን – 2:21:01 (2012)
ዋና ዋና ውጤቶቿ
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና፤ በወጣቶች, በ2003 4ኛ እንዲሁም በ2004 1ኛ፤
በ2004   በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና, 5000ሜ የወርቅ ሜዳልያ
ከ2005 እኤአ ጀምሮ  በ6 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች በመሳተፍ፤  በአጭር 4ኪ.ሜ 6ኛ እንዲሁም በረጅም ርቀት 3 የነሃስ ሜዳልያዎች፤ ሁለት 4ኛ ደረጃዎች እና 9ኛ ደረጃ አስመዝግባለች፡፡
ከ2006 እስከ 2010 እኤአ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5000ሜ 1 የወርቅ ሜዳልያ እና 6ኛ ደረጃ እንዲሁም በ10ሺ 1 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች አግኝታለች፡፡
በ2007 መላው አፍሪካ ጨዋታዎች በ5000m የብር ሜዳልያ እንዲሁም በ2008 በዓለም አትሌቲክስ ፍፃሜ 5000m የነሐስ እና በየዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና 3000ሜ የብር ሜዳልያ
ከ2005  ጀምሮ እስከ 2011   በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 5000ሜ 4ኛ፤6ኛ እና 5ኛ ደረጃ በ10ሺ ሜትር ደግሞ የብር ሜዳልያ እና 5ኛ ደረጃ

Read 3964 times