Saturday, 14 April 2018 14:53

የመስፍን ኃብተማሪያም “ትንሳዔ” የስዕል ትርኢት ተከፈተ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

የአንጋፋው ሠዓሊ መስፍን ኃብተማሪያም የሥዕል ስራዎች ስብስብን ያካተተ “ትንሳዔ” የተሰኘ የሥዕል ትርዒት በትላንትናው ዕለት ከራስ መኮንን ድልድይ ወደ አፍንጮ በር መሄጃ ላይ በሚገኘው በጉራምዓይኔ የሥነ-ጥበብ ማዕከል ተከፈተ፡፡ ትርዒቱ ሰላሳ ስምንት የሠዓሊውን ስራዎች ለህዝብ የሚያቀርብ ሲሆን እነዚህ የሥዕል ስራዎች ቤተሰቦቹ በተለይም ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ተናኘወርቅ ካሳሁን፣ከሠዓሊው ህልፈት በኋላ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል ጠብቀው ያቆዩዋቸው እንደሆኑ ታውቋል፡፡ መስፍን ኃብተማሪያም በ1980ዎቹና 90ዎቹ መጀመሪያ፣ በኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ሊጠቀሱ ከሚችሉ ባለ ታሪኮች መሃከል አንዱ የነበረ ሲሆን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ቴአትርና ባሕል አዳራሽ በመድረክ ዲዛይነርነት፣ በሜጋ የኪነ-ጥበብ ማዕከልና በተዋናይ ስቱዲዮ በዲዛይነርነት፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በኢሉስትሬተርነት ማገልገሉን የህይወት ታሪኩ ይመሰክራል፡፡   
በትርዒቱ የቀረቡት ስራዎች ሠዓሊው የኖረበት ዘመንና ማኅበረሰብ፣ እየተጓዘበት በነበረው የባሕል፣ የአኗኗርና የአስተሳሰብ ሂደቶች ያስተናግድ የነበረውን እሳቤዎችና መቀያየጥ ያመላከተበት ብቻ ሳይሆን ለውጦቹ የተነሱበትንና የሚሄዱበትንም አካሄድ መለስ ብለን እንድንቃኝ እድል የሚሰጡ ናቸው፡፡
የመስፍን ስራዎች ከምናባዊ ምጥቀታቸው ባሻገር ጊዜና ማኅበረሰብ የቆመበትን፣ ወደ ኋላና ወደ ፊት የሚመለከትበትን መስታወቶች የሚቸሩ ናቸው።  ሠዓሊ መስፍን ኃብተማሪያም ጥልቅ ሃሳቦችን በውብ ቋንቋ የሚያስቀምጥ ገጣሚም ነበር፡፡ በቅርቡ ግጥሞቹንና ሌሎች ጽሁፎቹን ያካተተ መጽሐፍ ለንባብ ለማብቃት በዝግጅት ላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ለአንድ ወር በሚቆየው በዚህ “ትንሳዔ” የተሰኘ የስዕል ትርዒት ላይ ሠዓሊው በተለያዩ ሥነ-ጥበባዊ ዝግጅቶች ይዘከራል ተብሏል፡፡ በ1957 ዓ.ም የተወለደው መስፍን ኃብተማሪያም፤ገና በ36 ዓመት ለጋ ዕድሜው ነበር ህይወቱ ያለፈው - በ1993 ዓ.ም፡፡

Read 2288 times