Saturday, 14 April 2018 15:01

‹‹…ለእናቶች…በሁሉ ነገር…ትኩረት…››

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ‹‹…እኔ ትዳር በያዝኩ በሶስተኛው አመት የመጀመሪያ ልጄን አረገዝኩ፡፡ ከዚያም በአቅራቢያዬ ወደሚገኝ ሆስፒታል ሄድኩና ምርመራ መጀመር እንደምፈልግ ነገርኩዋቸው። እነርሱም ተቀብለውኝ ምርመራውን ስጀምር ባለቤቴን እንድጠራ ተነገረኝ፡፡ ለምንድነው? ብዬ ብጠይቅ መጀመሪያ ሁለታችሁም ደም ብትሰጡና ብትታዩ ጥሩ ነው፡፡ ተባልኩኝ፡፡ ከዚያም ወደቤት ተመልሼ የተባልኩትን ነገርኩና የተሰጠንን የጥሪ ወረቀት ስሰጠው…በድንገት ብድግ ብሎ በጥፊ መታኝ፡፡ ምንሆነህ ነው? ብዬ ስጠይቀው በወደቅሁበት በእርግጫ ደገመኝ፡፡ እንደምንም ተጥመልምዬ ከወደቅሁበት ተነሳሁኝ፡፡ እዛው ሄደሽ ጣጣሽን ጨርሺ፡፡ እኔ የምጠራበት ምን ምክንያት አለ? የሆንሽውን እዛው አያክሙሽም? እኔ ለምን እፈለጋለሁ? ብሎ ጮኸብኝ፡፡ ስንጯጯህ የሰሙ ሰዎች ገብተው ገላገሉንና በቀጣዩ ቀን ወደሆስፒታል አብረን ሄድን፡፡ ምርመራውንም የግድ አደረገ፡፡ ነገር ግን ሁለታችንም ቫይረሱ በደማችን ውስጥ የለብንም፡፡ እኔ ግን በዚያ ዱላ ምክንያት ታምሜ ጽንሱ ተቋረጠ፡፡ ጽንሱም ብቻ ሳይሆን ኑሮአችንም ፈረሰ፡፡ ምክንያቱም ቫይረሱ በደማችን ውስጥ ቢገኝ ኖሮ እንደሚገለኝ ከዚያው ከሆስፒታል ነግሮኝ ስለነበር ነው፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎች አርቆ ማሰብ የተሳናቸውና በዘመኑ የሌሉ ሁዋላቀሮች ስለሆኑ ቢመከሩ ጥሩ ነው፡፡…››
ከላይ ያነበባችሁት ታሪክ በአምቦ ከተማ ቡና እያፈላች የምትተዳደር ወጣት ምስክርነት ነው፡፡ በአምቦ አጠቃላይ ሆስፒታል የማዋለጃ ክፍሉን የስራ እንቅስቃሴ ለመመልከት በስፍራው በተገኘንበት ጊዜ ጠበብ ባለ ቦታ ታካሚና አሳካሚ የሆኑ ሰዎች ሲጨናነቁ ተመልክተናል፡፡  ሁኔታውን ለመመልከት ዘልቀን መግባት ነበረብን፡፡ የነበረውን ሁኔታ እንዲያብራሩልን የህክምና ባለሙያዎችን አነጋግረናል፡፡ በቅድሚያ ያገኘናቸው በሱፈቃድ ባልቻ በአምቦ አጠቃላይ ሆስፒታል አዋላጅ ነርስ ናቸው፡፡
ጥ/    በሆስፒታሉ ለመታከም የሚመጡ ተገልጋዮች ከየት ከየት ናቸው?
መ/    በአምቦ ሆስፒታል የሚታከሙት የጽንስና ማህጸን ታካሚዎች የሚመጡት በአጠቃላይ በምእራብ ሸዋ ካሉት ወረዳዎች ካሉ ጤና ጣቢያዎችም ሆነ ሌሎች የህክምና ተቋማት ሲሆን ስፍራዎቹም ጉደር፤ ሸነን፤ ከሚባሉት እና በአብዛኛውም በግላቸው የሚመጡ ናቸው። በአብዛ ኛው የሚመጡት እናቶች ሕመምም በድንገት ጽንስ መቋረጥና እንዲሁም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ፈቅደው ጽንስ ለማቋረጥ የሚመጡም አሉ። ሆስፒታሉ በሪፈር ሕመምተኞችን የሚቀበልባቸው ተብሎ የተመደቡለት ጤና ጣቢያዎች ቢኖሩም በድንገተኛ የሚመጡት ግን ከየትኛውም አካበቢ  ወይንም በግላቸውም ቢሆን አይመለ ሱም፡፡ ምናልባት ሕክምናው የሚሰጥበት ስፍራ ቢጠብና ቢጨናነቅ እንኩዋን ሕይወትን ሳናተ ርፍ ወደሌላ ቦታ እንዲሄዱ አናደርግም፡፡ በእርግጥ ከአሁን ቀደም ሁሉ ነገር በዚሁ ሆስፒታል ብቻ ተጨናንቆ የሚሰጥ ሲሆን አሁን ግን ሌላ የሪፈራል ሆስፒታል ስለተከፈተ ከአቅም በላይ የሆኑትን ወደዚያ እንልካለን፡፡      
በመቀጠል ያነጋገርነው ማትያስ ለሜሳ አዋላጅ ነርስ የማዋለጃ ክፍሉ ኃላፊ ናቸው፡፡
ጥ/    የማዋለጃ ክፍሉ አቅም ምን ይመስላል?
መ/    ማዋለጃ ክፍሉ በጣም የሚጨናነቅ ጠባብ እና ውስን አልጋዎች ያሉት ነው፡፡ በእርግጥ የአምቦ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል ከመጀመሩ በፊት እጅግ በጣም የሚጨናነቅ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከጌዴዎ እና ከጉደር፤ ከጀልዱ አካባቢ ሪፈር የሚባሉት ወደ አምቦ ሪፈራል ሆስፒታል እንጂ እንደድሮው ወደ አምቦ አጠቃላይ ሆስፒታል ባለመሆኑ መጨናነቁን ቀንሶታል፡፡ ነገር ግን አሁን ትንሽ ይሻላል ቢባልም ያው ችግሩ እንዳለ ነው፡፡ በአምቦ አጠቃላይ ሆስፒታል በአሀኑ ወቅት በወር የሚወልዱት እናቶች ወደ 178/አንድ መቶ ሰባ ስምንት የሚደርስ ሲሆን የአለው የአልጋ ቁጥር ግን 4/አራት እንዲሁም ኮች 4/አራት ብቻ ነው፡፡ በሆስፒታሉ ላይ ጫና የሚፈጥሩት በግላቸው ፈልገው የሚመጡት ታካሚዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ወላዶች በአብዛኛው ምንም የጤና ችግር የሌለባቸው እና በአቅራቢያቸው ባሉ የጤና ጣቢያዎች ሊወልዱ የሚችሉ ሆነው ሳለ ወደአምቦ አጠቃላይ ሆስፒታል በመምጣት የአልጋም ሆነ የባለሙያውን ኃይል እንዲጣበብ ያደርጉታል። ሆስፒታሉ ይበልጥ ከወሊድ ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ የጤና እክሎች በተቸገሩት ላይ ብቻ ቢያተኩርና ቢሰራ ጫናው ይቀንሳል የሚል እምነት አለ፡፡ ስለዚህም ጤነኛዎቹ ወላዶች እናት በምንም ሁኔታ ወደሆስፒታሉ ስትመጣ አንቺ ጤነኛ ወላድ ነሽና ተመለሽ እንደማይባል ስለሚያውቁ ብቻ  በሆስፒታሉ አሰራር ላይ ችግር ከማስከተል ቢቆጠቡ መልካም ነው፡፡
ጥ/    ወደሆስፒታሉ የሚመጡት እናቶች ይበልጡኑ የሚታዩባቸው ሕመሞች ምንድናቸው?
መ/    በሪፈርም ይሁን በግላቸው ወደሆስፒታሉ ለእርዳታ የሚመጡት እናቶች በአብዛኛው የሚታይባቸው ችግር በጤና ጣቢያም ይሁን በቤታቸው በረጅም ጊዜ ምጥ የተነሳ የማህጸን መፈንዳት እንዲሁም ከደም ግፊት ጋር በተያያዘ ኢክላምፕሲያ የመሳሰሉት በተጨማሪም ከወሊድ በሁዋላ የደም መፍሰስ ችግሮች ይገጥሙዋቸዋል፡፡ የማህጸን መፈንዳት ደርሶባቸው የሚመጡት በጽንሱ ላይ ጉዳት ደርሶ እናትየውንም ከሚያሰጋበት ደረጃ ላይ ሆነው ከሆስፒታል ሲደርሱ በከፍተኛ ርብርብ እናትየውን ለማዳን ሙከራ ይደረጋል፡፡
በመቀጠል ሀሳብዋን ያብራራችልን ነርስ ሲስተር ስንታየሁ አሰፋ ትባላለች፡፡ ሲስተር ስንታየሁ በእናቶችና በሕጻናት ጤና ላይ የምትሰራ ባለሙያ ነች፡፡
ጥ/  ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ለእናቶች የሚሰጠው አገልግሎት ምን ይመስላል?
መ/    እናቶች በእርግዝናቸው ወቅት ለክትትል ሲመጡ አስቀድሞ የምክር አገልግሎት በመስጠት ምርመራ እንዲያደርጉ ደረጋል፡፡ ከአሁን ቀደም በሌላ ሆስፒታልም ይሁን በአምቦ አጠቃላይ ሆስፒታል ተመርምረው እራሳቸውን የሚያውቁ ቢሆንም እንኩዋን ከእርግዝናው ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ምክር እና አገልግሎቱን እንዲያገኙ የተቻለው ሁሉ ይደረጋል፡፡ ስለዚህም ቫይረሱ በደምዋ ውስጥ ያለባት አዲስ ተመርማሪ ስትገኝ ወዲያውኑ መድሀኒት እንድትጀምር ትደረጋለች፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው እናቶች በሚወል ዱበት ጊዜ ወዲያውኑ Nevirapine የተሰኘውን መድሀኒት እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡  ከዚያም ሕጻናቱ በምንም መንገድ ቫይረሱ ከእና ታቸው እንዳይተላለፍባቸው ለማድረግ በሳይንሱ ረገድ የተቀመጠውን መስፈርት በሙሉ ለማሟላት ጥረት ይደረጋል፡፡
ጥ/    የትዳር ጉዋደኞች ስለሁኔታው ያላቸው ምላሽ ምንይመስላል?
መ/    ቀደም ሲል ቫይረሱ በደማቸው መኖሩን ያወቁ እናቶች ባሎቻቸውም ሁኔታውን የተረዱ በመሆኑ ምንም ችግር አይገጥምም፡፡ነገር ግን አዲስ ተመርማሪ ከሆነችና ቫይረሱ በደምዋ ውስጥ መኖሩን ገና ያወቀች ሴት ከሆነች ባለቤትዋን እንድትጠራ ወረቀት ይሰጣታል፡፡ ብዙዎቹ ባሎች ግን ወደሆስፒታል ለመቅረብ ፈቃደኛ አይሆኑም። አን ዳንዶቹም ቢመጡ እንኩዋን ተጣ ልተው አንዳንድ ጊዜ በሚስቶቻቸው ላይ ዱላ የሚ ሰነዝሩም አይጠፉ። ቢመጡም በትክክል ምር መራውን ለማድረግ ፈቃደኛ የማይ ሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ውጤቱም አንዳንዴ ቫይረሱ በደማ ቸው የሚገኝ ሲሆን አንዳንዴ ደግሞ ወንዶቹ ቫይረሱ በደማቸው አይገኝም፡፡ በሆስፒታሉ በኩል ግን ሁለቱም ማለትም ባልና ሚስቱ ያሉበትን የጤና ሁኔታ አውቀው በወደፊት ሕይወታ ቸው ማድረግ ያለባቸውን ነገር ይመከራሉ፡፡  
አዋላጅ ነርስ በሱፈቃድ እንደሚገልጹት ወላድ እናቶችን በሚመለከት ያሉት መዘግየቶች አሁንም እንደሚንጸባረቁ ነው፡፡ አንዳንዶች ከመንገድ እርቀው ስለሚኖሩ ብዙ ጊዜ ምጥ ሲይዛቸው በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም ለመሄድ ይቸገራሉ። ስለዚህም ከቤታቸው ወልደው ችግር ገጥሞአቸው ለሕክምናው ይመጣሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአምቡላንስ አጠ ቃቀሙ ላይ ምናልባት ዘግይተው አምቡላንስ እንዲመጣ መጠየቅ ወይንም አምቡላንሶ ተጠርቶ በተለያዩ ምክንያቶች በፍጥነት አለመድረስ የመሳሰሉት ችግሮች እናቶቹን ወደሆስ ፒታል ከመምጣት ሊያዘገዩአቸው ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በደረሱበት ጤና ጣቢያም አገልግሎት አሰጣጡ ላይ አንዳንድ ችግሮች …ለምሳሌም እንግዴ ልጁን ማዋለድ አለመቻል የመሳሰሉት ችግሮች ገጥሞአቸው እናቶች ሪፈር ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ከእናቶች ጋር በተያያዘ አንድም ቸል ሊባል የሚገባው ነገር የለም፡፡ ለእናቶች የሚሰጠውን አገልግሎት በሚ መለከት ሁሉም ነገር ትኩረትን ይሻል፡፡

Read 1472 times