Saturday, 07 April 2018 00:00

ፋሲካና 21ኛው የዓለም ዋንጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

• 68 ቀናት ቀርተዋል፡፡ በአዘጋጇ ራሽያ ላይ ተቃውሞው ቀጥሏል፡፡ ከፖለቲካዊ ጫና አይዘልም እንጅ፡፡
 • ልዩ የ‹‹ቱሪስት ፖሊሶች›› ይሰማራሉ፤ መላውን ራሽያና ሞስኮ ከተማን የሚያስተዋውቁ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ መመርያ  ህትመቶች ይሰራጫሉ፡፡
 • 68 ቀናት ቀርተዋል፡፡ በአዘጋጇ ራሽያ ላይ ተቃውሞው ቀጥሏል፡፡ ከፖለቲካዊ ጫና አይዘልም እንጅ፡፡
 • ልዩ የ‹‹ቱሪስት ፖሊሶች›› ይሰማራሉ፤ መላውን ራሽያና ሞስኮ ከተማን የሚያስተዋውቁ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ መመርያ ህትመቶች ይሰራጫሉ፡፡
 • በሁለት የሽያጭ ምዕራፎች 1.7 ሚሊዮን ትኬቶች ተሸጠዋል፤ የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ አፍቃሪዎች በግዢ ብዛት ይመራሉ
 • የአዘጋጇ ራሽያ ቡድን ከምድብ ፉክክር ማለፍ አጠያያቂ እንደሆነ ነው፡፡
 • 23ኛውን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ ፍጥጫው በአፍሪካዋ ሞሮኮ እና በሰሜንና መካከለኛው አሜሪካዎቹ አሜሪካ፤ካናዳና ሜክሲኮ• በሁለት የሽያጭ ምዕራፎች 1.7 ሚሊዮን ትኬቶች ተሸጠዋል፤ የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ አፍቃሪዎች በግዢ ብዛት ይመራሉ
 • የአዘጋጇ ራሽያ ቡድን ከምድብ ፉክክር ማለፍ አጠያያቂ እንደሆነ ነው፡፡
 • 23ኛውን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ ፍጥጫው በአፍሪካዋ ሞሮኮ እና በሰሜንና መካከለኛው አሜሪካዎቹ አሜሪካ፤ካናዳና ሜክሲኮ

   ራሽያ የምታስተናግደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ልክ ዛሬ በፋሲካ ዋዜማ ላይ 68 ቀናት ይቀሩታል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር /ፊፋ/ በቀውስ ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ደብዳቤ የላከ ሲሆን ኘሬዚዳንታዊ እና የሥራ አስፈፃሚዎች ምርጫን አስመልክቶ የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫን የሚያስፈጽም አዲስ አስመራጭ ኮሚቴ እንደገና እንዲቋቋም ጠይቋል። በፌደሬሽኑ ዙርያ ያለውን ውዝግብ ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ  ነው ብሎ ባሰበበት በዚህ ውሳኔው ፊፋ አዲሱ የአስመራጭ ኮሚቴ የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በድጋሚ በመመርመርና በመፈተሽ እንዲያፀድቅ እና ከጅምሩ  ወደ ምርጫ ሒደት እንዲገባ አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል ዓለም ዋንጫውን  በዋና ዳኝነት እንዲመሩ ከተመረጡት 36 ዋና ዳኞች ኢትዮጵያዊው ባምላክ ተሰማ የሚገኝበት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ወደ ራሽያ በመጓዝ  ዘገባ እንዲሰሩ የተመረጡት 3 የስፖርት ጋዜጠኞች እኔ ግሩም ሰይፉ ከአዲስ አድማስ፤ ዳዊት ቶሎሳ ከሪፖርተር እንዲሁም አለምሰገድ ሰይፉ ከሊግ ስፖርት ጋዜጦች በራሽያ የዓለም ዋንጫ ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ እና በፊፋ ማመልከቻ ተቀባይነት አግኝቶ ተሳትፏቸው ተረጋግጧል፡፡ ፊፋ ለ21ኛው የዓለም ዋንጫ 36 ዋና ዳኞች እና 63 ረዳት ዳኞችን ከ46 የተለያዩ አገራት የመረጠበትን ዝርዝርን ከሳምንት በፊት ሲያስታውቅ፤ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ከአፍሪካ ከተመረጡት 6 ዳኞች አንዱ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም  10 ረዳት ዳኞችም ከአፍሪካ ተመርጠዋል፡፡
በዓለም ዋንጫው በቪዲዮ የተደገፈ ዳኝነትም (VAR) ተግባር ላይ እንደሚውል ያመለከተው ፊፋ የዓለም ዋንጫው 99 ዋና ዳኞችና ረዳት ዳኞች ከወር በኋላ በጣሊያን በተዘጋጀ ልዩ ሴሚናር እንደሚሳተፉም አስታውቋል፡፡ ለሁለት ሳምታት ያህል በሚቆየው በጣሊያን እግር ኳስ ማህበር በሚዘጋጀው ሴሚናር ላይ ይሳተፋሉ፡፡ ከአፍሪካ  አህጉር ምርጥ 10 ዋና ዳኞች አንዱ የሆነው ባምላክ ተሰማ በ4 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች፤ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕና በፊፋ የሀ20 ዓለም ዋንጫ ወሳኝ ጨዋታዎችን በመምራ ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ሲሆን፤ በመሃል ዳኝነት የመራቸው ዓለም ቀፍ ጨዋታዎች ከ50 በላይ ናቸው፡፡  
በ2010 ዓ.ም የፋሲካ በዓል ዋዜማ ላይ የቀረበው ይህ የስፖርት አድማስ ዘገባ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ራሽያ ላይ በሚያንዣብቡ የውዝግብ አጀንዳዎች እና ወቅታዊ ጫናዎች፤ ለዓለም ዋንጫ እንግዶች ስለታቀዱ መስተንግዶዎች፤ ስለ ትኬቶች ሽያጭ፤ ስለ ራሽያ ብሄራዊ ቡድን ፈተና እንዲሁም በአጠቃላይ በዓለም ዋንጫ አዘጋጅነትና ምርጫ ዙርያ የሚያጠነጥን ነው፡፡
በፑቲንና በራሽያ መንግስት
ላይ ከየአቅጣጫው ጫና ቢበዛም…
ቭላድሚር ፑቲን ለሚቀጥሉት 6 ዓመታት ራሽያን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ከተመረጡ በኋላ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ አገር ላይ ባለፉት 2 ወራት የተለያዩ የውዝግብ አጀንዳዎች ጫና መፍጠራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ራሽያ በዓለም የፖለቲካ ስነ ምህዳር በሶርያ፤ በመካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም በአሜሪካ የውስጥ ፖለቲካ የምታራምደው አቋም ከበርካታ አገራት ጋር እንደሚያነታርካት ይታወቃል፡፡ ከ21ኛው የዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ  በተለይ እየተባባሰ የመጣው የውዝግብ አጀንዳ የፑቲን አስተዳደር በቀድሞ የስለላ ባለሙያ ዜጎቹ ላይ ኢሰብዓዊ ተግባራት ፈፅሟል የሚለው ውንጀላ ነው፡፡ በቅርቡ በእንግሊዝ የሚገኝ እና ለሁለት ወገን የሚሰልል ራሽያዊ ላይ የመርዝ ጥቃት የራሽያ ደህንንት ተቋማት አድርሰዋል መባሉ ተፅእኖ እንደፈጠረ ማስተዋል ይቻላል፡፡ አንዳንድ አገራት በራሽያ መንግስት ማንአለብኝነት መስፈኑን በመጥቀስ ከዓለም ዋንጫው ተሳትፎ ብሄራዊ ቡድኖቻቸውን ለማግለል የሚዝቱበት ምክንያት አግኝተዋል፡፡  
ማጣርያውን ባለማለፏ ዓለም ዋንጫ ያመለጣት አሜሪካም የራሽያን የዓለም ዋንጫ ድግስ በዚሁ አጀንዳ ለመበጥበጥ በየፊናው መሯሯጧን ቀጥላለች።  በአጠቃላይ ግን ዓለም ዋንጫ በሚካሄድበት ዓመት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የውዝግብ አጀንዳዎች በአዘጋጅ አገር ላይ ጫናዎች የሚፈጥሩበት አባዜ ዘንድሮም እየተስተዋለ ነው፡፡ የስፖርት ኢንዱስትሪው ባለሙያዎች እና ሚዲያዎች ከዓለም ዋንጫው ተሳትፎ ራሳቸውን ለማግለል የሚያስቡ አገራት  በራሽያ መንግስት ላይ ተፅእኖ ለማድረግ እንጅ  የሚተገብሩት አይደለም እያሉ ነው፡፡ ይህ አይነቱን ዛቻ ካሰሙት አገራት ደግሞ አውስትራሊያ እና እንግሊዝ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በዓለም ዋንጫው ብሄራዊ ቡድኖቻቸውን አናሰልፍም የሚሉት አሰልጣኞቹና ተጨዋቾቹ ሳይሆኑ በመንግስት አስተዳደራቸው ያሉ ባለስልጣኖች ናቸው።  በተለይ 23 የራሽያ ዲፕሎማቶችን ከአገሯ ያባረረችው እንግሊዝ ከውድድሩ እወጣለሁ በሚል ዛቻ ተፅእኖ ለመፍጠር እየሞከረች ሲሆን፤ ተግባራዊ ከሆነ እጅግ ትርፋማው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ይጎዳል መባሉ ኢንዱስትሪውን አስጨንቆታል፡፡ በፊፋ ህግ ደንብ መሰረት የዓለም ዋንጫን ተሳትፎ መሰረዝ ብዙ ቅጣት የሚያስከትል ነው፡፡ በተለይ ውድድሩ ከመጀመሩ  ከወር ባነሰ ጊዜ ላለመሳተፍ በወሰነ ብሄራዊ ቡድን  የሚወክለው ፌደሬሽኑ እስከ 377ሺ ፓውንድ ወይንም እስከ 500ሺ ዶላር ሊቀጣ ይችላል፡፡ ዓለም ዋንጫን ወደፊት የማስተናገድ እድሉንም ይነፈጋል፡፡
በርካታ የስፖርቱ ባለሙያዎች እና ተንታኞች እንደፃፉት ከዓለም ዋንጫ ተሳትፎ እንቀራለን የሚሉ አገራት ብዙም በዚህ አቋማቸው እንደማይቀጥሉ ነው። በፖለቲካ  ልዩነቶች ተሳትፎን መሰረዝና ከውድድር መገለል ውሳኔዎች በስፖርቱ ታሪክ የተከሰቱ ሲሆን ከእግር ኳስ ይልቅ በኦሎምፒክ መድረክ በተደጋጋሚ አጋጥሟል፡፡ በ1980 እኤአ ላይ ሞስኮ ባዘጋጀችው ኦሎምፒክ 60 አገራት ላለመሳተፍ የወሰኑት በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር አነሳሽነት ሲሆን፤  ራሽያ አፍጋኒስታንን መውረሯን በመቃወም የተፈጠረ  ነበር።  ከ4 ዓመታት በኋላም በ1984 እኤአ ላይ ኦሎምፒኩ በደቡብ ኮርያ ሲኦል ሲካሄድ  የቀድሞዋን ሶቪዬት ህብረት  አቋም በመደገፍ 14 አገራት  ተሳትፏቸውን በመሰረዝ የበቀል ርምጃ መውሰዳቸው ይታወሳል።  በዓለም ዋንጫ ታሪክ ተሳትፎን በመሰረዝ ብቸኛው ታሪክ  ያጋጠመው በምእራብ ጀርመን በተዘጋጀው የ1974 ዓለም ዋንጫ ሲሆን ሶቪዬት ከቺሊ ጋር በጥሎ ማለፍ ላለመጫወት ወስና ከውድድር የወጣችበት ነበር፡፡
ከዓለም ዙርያ ለሚመጡ ስፖርት አፍቃሪዎችና ቱሪስቶች አስተማማኝ ፀጥታና ምቹ መስተንግዶ
የራሽያ መንግስት ዓለም ዋንጫው በሚካሄድባቸው 30 ቀናት ከ3 ሚሊዮን በላይ ስፖርት አፍቃሪዎችን ከመላው ዓለም ማስተናገዱ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ በራሽያ ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴው የዓለም ዋንጫውን ቱሪስቶች በምቹ ሁኔታ ለማስተናገድ ያስችሉኛል በሚላቸው ዝግጅቶች መስራቱን ቀጥሏል፡፡ ከእነዚህ ዝግጅቶች አንዱ በ6 ቋንቋዎች የጉዞ መመርያ ህትመቶች መሰራቱ ሲሆን  በራሽያኛ፤ በእንግሊዝ፤ በቻይንኛ፤ በጀርመኛ፤ በፈረንሳይኛ እና በስፓኒሽ ቋንቋዎች የተሰራው መፅሃፍ በ1.4 ሚሊዮን ቅጂ ታትሞ በነፃ እንደሚታደል ታውቋል። በተጨማሪም 960 ሺ የቱሪስት ካርታዎች እና ከ480ሺ በላይ የሞስኮ ከተማ የሚያስተዋውቁ ህትመቶች ይሰራጫሉ፡፡  
በሌላ በኩል ከዓለም ዙርያ ለሚመጡ ስፖርት አፍቃሪዎችና ቱሪስቶች አስተማማኝፀጥታ ለማስፈን በከፍተኛ ትኩረት እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ነው። በቅርቡ በፀጥታ እና ደህነነት ዙርያ በሞስኮ በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ላይ ይህ ጉዳይ ሰፊ ምክክር ተደርጎበታል፡፡ የራሽያ ብሄራዊ ደህንነት ኤጀንሲ FSB ዲያሬክተር አሌክሳንደር ቦርቲኒኮቭ  አገራቸው የተሳካ ዋንጫ እንድታካሂድ የሌሎችአገራት የደህንነት ተቋማት ሙሉ ድጋፍ ያስፈልጋል በሚል በይፋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተያያዘ  የራሽያ መንግስት በዓለም ዋንጫው በየቋንቋው ልዩ ግልጋሎት የሚሰጡ የቱሪስት ፖሊሶች ለማሰማራት እንደወሰነ ታውቋል፡፡ በ11 ከተሞች የሚሰማሩት እነዚህ ልዩ ሃይሎች ከ32 አገራት የሚመጡ ደጋፊዎችን በእንግሊዘኛ፤ በፈረንሳይኛ፤ በስፓኒሽ ቋንቋዎች እንዲያግዙ ተፈልጓል፡፡
የደቡብ አሜሪካ ህዝቦች የተረባረቡበት ትኬት ሽያጭ
ለ21ኛው የዓለም ዋንጫ የሚካሄደው ስታድዬም የመግቢያ ትኬት ሽያጭ ሁለተኛው ምዕራፍ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ተዘግቷል፡፡ ታላቁ የስፖርት መድረክ ሊጀመር ከ3 ወራት ያነሰ ጊዜ ቢቀሩም  በሁለት የትኬት ሽያጭ ምዕራፎች 1698049 ትኬቶች መሸጣቸውን ፊፋ በድረገፁ አረጋግጧል፡፡ በትኬት ሽያጩ ሁለተኛው ምዕራፍ 394,433 ትኬቶች መሸጣቸውን ያመለከተው ፊፋ 216,134 የአዘጋጇ ራሽያ ህዝቦች መግዛታቸውን ጠቁሞ የደቡብ አሜሪካ ህዝቦች  ከአውሮፓ በተሻለ ብዛት ትኬቶች መግዛታቸውን ጠቁሟል፡፡
በትኬቶች ግዢ ብዛት ከአዘጋጇ ራሽያ ውጭ በወጣው ደረጃ ከአሜሪካ 16,642፤ ከአርጀንቲና 15,006፤ ከኮሎምቢያ 14,755፤ ከሜክሲኮ 14,372፤  ከብራዚል 9,962፤  እና ፔሩ  9,766 ትኬቶች ተገዝተው እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ወስደዋል፡፡  ከጀርመን 5,974፤ ከቻይና 6,598 ፤ ከአውስትራሊያ 5,905 እና ከህንድ 4,509 የትኬት ግዢ ተመዝግቦ በቅደም ተከተል እስከ 10ኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የትኬት ሽያጩ ሶስተኛው ምዕራፍ ከ12 ቀናት በኋላ እንደሚከፈት ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር አስታውቋል፡፡
ራሽያ በአዘጋጅነቷ ከምድብ ማለፍም
ላይሳካላት ይችላል…?
ባለፈው 1 ወር ውስጥ የራሽያ ብሄራዊ ቡድን በወዳጅነት ጨዋታ በብራዚል 3ለ0 ከዚያም ብዙም ባልተጠናከረው የፈረንሳይ ቡድን 3ለ1 መሸነፉን ተከትሎ በአዘጋጅነት ከምድብ ማለፍም ላይሳካላት ይችላል? የሚል ጥያቄ ተፈጥሯል፡፡
ዋና አሰልጣኙ ስታኒስላቭ ቼርቼሶቭ ቡድናቸውን በምድብ ፉክክር ስኬታማ በማድረግ  ለጥሎ ማለፍ ምዕራፍ እንዲያበቁ በራሽያ መንግስትና ስፖርት አፍቃሪዎች እየተጠየቁ ናቸው፡፡  አዘጋጇ አገር  ከምትገኝበት ምድብ 1 ወደ ጥሎ ማለፍ ያልፋሉ ተብለው የተጠበቁት ሳውዲ አረቢያ እና ግብፅ ሳይሆኑ ራሽያ እና ኡራጋይ እንደሚሆኑ ግምት መሰጠቱ ብቻ ተስፋ ፈጥሮላቸዋል፡፡
ባለፉት 18 ወራት ዋና ቡድናቸውን ለመለየት 45 የተለያዩ ተጨዋቾቻቸውን በማፈራረቅ ሲሰሩ የቆዩት አሰልጣኙ ብሄራዊ ቡድኑን ከያዙ በኋላ 18 ጨዋታዎችን አድርገው በስምንቱ የተሸነፉ ሲሆን ይህ ሁኔታም የተሰጣቸውን ግምት የሚያጠናክር ባለመሆኑ ጫና ፈጥሮባቸዋል፡፡ ከዓለም ዋንጫው በፊት የራሽያ ብሄራዊ ቡድን በአራት ዋና ውድድሮች ማለትም በ2014 የዓለም ዋንጫ፤ በ2012 እና በ2016 የአውሮፓ ዋንጫዎች እንዲሁም በ2017 የፊፋ ኮንፌደሬሽን ካፕ ተሳትፎ ከምድብ ማጣርያ ሊያልፍ አልቻለም፡፡ ለቡድኑ በቅርብ ጊዜ ከፍተኛ ውጤት ሆኖ የሚጠቀሰው በ2008 እኤአ ላይ በአንድሬ አርሻቪን አምበልነት በመመራት በአውሮፓ ዋንጫ ለግማሽ ፍፃሜ መደረሱ ነው፡፡
23ኛውን የዓለም ዋንጫ በ2026 እኤአ ላይ የማስተናገድ ፍጥጫ…
በ2026 እኤአ ላይ በሚዘጋጀው 23ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፊፋ 48 ቡድኖች ለማሳተፍ መወሰኑ ይታወቃል። 23ኛውን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ በይፋ እቅዳቸውን በማቅረብ ፉክክር የገቡት የሰሜን አፍሪካዋ አገር ሞሮኮ እና ከሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ ደግሞ 3 አገራት በጥምረት አሜሪካ፤ ካናዳና ሜክሲኮ ናቸው። ሞሮኮ በ2026 እኤአ ላይ 23ኛውን የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት በይፋ እቅዷን ስታስታውቅ የስፖርት መሰረተልማቶቿን በአዲስ መልክ ገንብታ እና ሰርታ ለውድድሩ ለማድረስ ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ እንደሚኖርባት አመልክታለች፡፡ሞሮኮ በእቅዷ መሰረት በአፍሪካ ምድር ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫውን በብቃት ለማካሄድ 14 ስታድዬሞች ለመገንባት ያሰበች ሲሆን 3 ቢሊዮን ዶላር ለ9 አዳዲስ ስታዲዬሞች ግንባታ፤ ለአምስት ስታዲዬሞች እድሳት እና ለ130 የልምምድ ማዕከሎች መስርያ በጀት በማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም በ20 ከተሞች ለዓለም ዋንጫ ብቁ የሆኑ የስፖርት እና ሌሎች መሰረተልማቶች ግንባታ ለማከናወን ከ12.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማውጣት ማቀዷን አስታውቃ፤ በግል ኢንቨስተሮች ደግሞ እስከ 30ሺ መኝታ ያላቸው ሆቴሎች በ3.2 ቢሊዮን ዶላር  መገንባታቸውን ትጠብቃለች፡፡   
ሞሮኮ በ1994፤በ1998፤ በ2006 እና በ2010 እአኤ ዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ አመልክታ ያልተሳካላት ሲሆን የአሁኑ እቅድ አምስተኛዋ ሙከራ ነው፡፡ በሞሮኮ ጥያቄ 57 የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ ከ47 የኤስያ አገራት ድጋፍ ሊገኝ እንደሚችል ተጠብቋል፡፡ በሌላ በኩል ሰሜንና መካከለኛው አሜሪካን በመወከል መስተንግዶውን ለማግኘት ከሞሮኮ ጋር የሚፎካከሩት አሜሪካ፤ ካናዳ እና ሜክሲኮ  በተሟላ የመሰረተ ልማት አቅማቸው ግምት ያገኙ ሲሆን በሶስቱ አገራት የሚገኙት 23 ከተሞች 48 ቡድኖችን በተሟላ አቅም ለማስተናገድ እንደማይቸገሩ እየተገለፀ ነው፡፡ ፊፋ የ23ኛውን ዓለም ዋንጫ አዘጋጅ የሚወሰነው ከ3 ወራት በኋላ በሚያካሄደው ኮንግረስ 211 አባል አገራት በነፍስወከፍ የሚሰጡትን   ድምፅ መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ራሽያ የምታስተናግደውን 21ኛው የዓለም ዋንጫን ጨምሮ 17 አገራት ታላቁን የስፖርት መድረክ በማዘጋጀት የተሳካላቸው ሲሆን እያንዳንዳቸው  እኩል ሁለቴ ዓለም ዋንጫን ማዘጋጀት የቻሉ አገራት ሜክሲኮ፤ ጣሊያን፤ ጀርመን፤ ፈረንሳይና ብራዚል ናቸው፡፡
በ2022 እ.ኤ.አ ላይ የመካከለኛው ምስራቅ አገር ኳታር 22ኛውን የዓለም ዋንጫ እንድታስተናግድ የተመረጠች ሲሆን በ2026 እ.ኤ.አ ደግሞ የአፍሪካዋ ሞሮኮ ከሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ ሦስት አገራት ለ23ኛ የአለም ዋንጫ አዘጋጅነት ፉክክር መግባታቸው ከላይ እንደተጠቀሰው ነው፡፡
በ2030 እ.ኤ.አ የዓለም ዋንጫ 100ኛ ዓመት የሚከበር ሲሆን በዚሁ ጊዜ በልዩ ሁኔታ የሚካሄደውን 24ኛው የዓለም ዋንጫ በጣምራ ለማስተናገድ የመጀመሪያውን ጥሪ የደቡብ አሜሪካዎቹ ኡራጋይና አርጀንቲና ሲያስታውቁ ተፎካካሪያቸው የአውሮፓዋ እንግሊዝ ናት፡፡ በ2034  እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ 25ኛውን የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት የኤሺያ አገራት እድል ሲኖራቸው ኢንዶኔዥያና ታይላንድ በጋራ እንዲሁም ቻይና ብቻዋን መስተንግዶውን የመጠየቅ ፍላጎት አላቸው፡፡

Read 2589 times