Saturday, 07 April 2018 00:00

የዶ/ር አብይ ንግግር ለምን ተወደደ?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ታሪካዊ እንደሆነ የተነገረለት የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ንግግር ባልተለመደ መልኩ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል አስደስቷል፡፡ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ፡፡ ምስጢሩ ምንድን ነው? ከንግግራቸውም በመነሳት ብዙዎች ለጠ/ሚኒስትሩ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ኢትዮጵያውያን በጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ላይ ያላቸውን አስተያየት አሰባስቦ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡


               “ስለ ኢትዮጵያና ስለ ወላጅ እናታቸው ሲናገሩ አንብቻለሁ”
                  አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ (የኦሮሞ አባገዳዎች ም/ቤት ሰብሳቢ)

    በእውነት ዶ/ር አብይ ከአንድ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቀውን ንግግር ነው ያደረጉት፤ አንጀት የሚበላ ነው፡፡ የተራራቀውን ህዝባችንን የሚያቀራርብ ነው፡፡ ከአንድ መሪ የሚያስፈልገውም ይሄ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም የተጠማው ይህን አይነቱን ውስጥን የሚያለመልም፣ ተስፋ የሚሰጥ፣ ትህትና የተሞላበትን ንግግር ነበር፡፡ እኛም እንደ አባ ገዳና ሃገር ሽማግሌ ስንመኝ የነበረው፣ እንዲህ ሃገሩን ከፍ አድርጎ የሚጠራ መሪን ነው፡፡ ቋንቋችን ዥንጉርጉር ይሁን እንጂ ደማችን አንድ ነው ብዬ ደጋግሜ ተናግሬያለሁ፡፡
ከዚህ በኋላ የሚፈለገው የተናገሩትን ወደ ተግባር እንዲለውጡልን ነው፡፡ መናገሩ ብቻ ሳይሆን ዋናው ተግባሩ ነው፡፡ ወደ ተግባር እንደሚለውጡት ደግሞ እተማመናለሁ፡፡ ከአንዲት ኢትዮጵያዊት የተወለደ፣ ከአንድ ኢትዮጵያዊ የተወለደ፣ ኢትዮጵያዊነቱን ያልዘነጋ፣ የተጣላን የሚያስታርቅ፣ ከሃገር የወጣውን የሚያስመልስ፣ ጫካ የገባውን ወደ ሃገሩ በፍቅር የሚመልስ መሪ እንዲሆኑ ነው ፈጣሪን የምንለምነው፡፡ እኔ በበአለ ሲመቱ ላይ ነበርኩ፤ እውነቴን ነው የምልህ በጣም ነው ያለቀስኩት፡፡ ንግግሩ ነው ያስለቀሰኝ፡፡ ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር ነው የተገናኘነው፡፡ ሰው በጎሳ ተከፋፍሎ ሲተራመስ የነበረበትን ጊዜ እያስታወስኩ ነበር ያለቀስኩት። ለወደፊትም ይህቺን ሃገር ለማዳንና ለትውልዱ ለማስረከብ የሚያስፈልገው እንዲህ ያለው መሪ ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ መሪ የሚጠበቅበት ይህ ነው፡፡ እኔ ደስ ብሎኛል፡፡
ስለ ወላጅ እናታቸው ሲያነሱ አንብቻለሁ፡፡ እናታቸውን ሲያነሱ የሁሉንም እናት እንዳነሱ ነው የተረዳሁት፡፡ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነታችን ደጋግመው ሲናገሩ፣ ብዙ ነገር ነው የተሰማኝ። በሌላ በኩል ደግሞ በሃገር ውስጥም በውጪም ካሉት ጋር እንሰራለን ሲሉ፣ በሆዴ ውስጥ ትኩስ ወተት ነው ሲፈስ የተሰማኝ፡፡
እኛ መደማመጥና መተባበር ስንችል ነው ቃላቸው ወደ ተግባር የሚለወጠው፡፡ ስለዚህ መደማመጥ መቻል አለብን፡፡ ጊዜ መስጠት አለብን። መተባበርና መደጋገፍ፣ የተሳሳቱትን እየነገሩ በማረም መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡

-----------
             “ዶ/ር አብይ የህዝብ አመፅ የወለዳቸው መሪ ናቸው”
                 ዶ/ር ንጋት አስፋው (ፖለቲከኛና የዩኒቨርሲቲ መምህር)

    ከኢህአዴግ የቆየ ባህሪ አንፃር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የተለየና ተስፋ ሰጪ ነው። አንደኛ ብሔራዊ እርቅ እንደሚፈፀም፣ ሁለተኛ ሀገርን የማረጋጋት ሥራ እንደሚሰራ መናገራቸው መልካም ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማጠናከር ላይ ያደረጉትም ንግግር፣ ከዚህ ቀደም ከምናውቀው የድርጅቱ  ባህሪ የተለየ ነው፡፡ ይህቺ ሃገር ከትውልድ ወደ ትውልድ በአንድነት ፀንታ መሸጋገር እንዳለባት ያቀረቡበት መንገድ፣ ለሁሉም ገዢ ሀሣብ ነው። በግል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የልብን ፍላጎትን የሚሞላ ቢሆንም ከኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ባህሪና መርህ አንፃር፣ ቃላቸው ወደ ተግባር ይለወጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ዶ/ር አብይ የህዝብ አመፅ የወለዳቸው፣ የማዕበሉ ውጤት ናቸው፡፡ ህዝባዊ አመፁ የፈጠራቸው መሪ እንጂ ከኢህአዴግ የፖለቲካ ባህል የተገኙ አይደሉም፡፡ ማዕበሉ ያመጣው፣ ያልታሰቡ መሪ ናቸው - ዶ/ር አብይ፡፡
በንግግራቸው ላይ የእስረኞች ጉዳይ አልተነሳም። ለኔ ይሄ ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ስለ ፖለቲካና ዲሞክራሲ ያወሩበት ድምፀት ግን ጥሩ ነው፡፡ ለእርቀ ሰላም ጥሪ ማቅረባቸውም መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በምን መንገድ? እንዴት የሚሉት አልተዳሰሱም። በንግግራቸው ልብን ከማሞቅ የዘለለ ህዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች በሚገባ አልተነሱም። በኤርትራ ጉዳይ የያዙት አቋም ስንናፍቀው የነበረው ነው፡፡ ነገር ግን አሁን እውን ይሆናል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ እኒህ አዲስ መሪ መጡ ማለት የሀገሪቱ ችግር ተፈታ ማለት አይደለም። ችግር መፈታት የሚጀምረው ፖለቲከኞች በነፃነት ሲወያዩ፣ አዳዲስ ሃሳቦች ሲፈልቁ ነው፡፡
እኔን ያስገረመኝ በ15 ዓመቱ ህውኃትን የተቀላቀለና በህውኃት የዲሞክራሲ ፀበል ተጠምቆ ያደገ ወጣት ሆኖ ሳለ፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት ብዙዎችን ያስደመመ፣ ማራኪ ንግግር ማቅረቡ ነው፡፡ እኔ ጅማ ስሰራ፣ በግሌ ቤተሰቦቹንም እሱንም አውቀዋለሁ፡፡ ገጠራማ ከሆነ አካባቢ የወጣ ሰው ነው፡፡ ከንግግሩ ንቃተ ህሊናው የዳበረ መሆኑን ነው የተረዳሁት። ንግግሩም የራሱ እንደሆነ አያሻማም፡፡ ነገር ግን የሀገሪቱ ችግር የሚፈታው፣ ምርጫ ተደርጎ፣ በህዝብ የተመረጠ መሪ ሲመጣ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በሌላ በኩል፤ ዶ/ር አብይ የወጣቱን ቀልብ የመያዝ አቅም አለው፡፡ ጊዜውንና ዕድሉን ከተጠቀመበት ጥሩ ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ዋናው ጊዜውን በአግባቡ መጠቀሙ ላይ ነው፡፡ የቂም በቀል ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሀገር ውስጥ ተነቅሎ መጥፋት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡  ይሄ ደግሞ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ይመለከታል፡፡   

--------

              “መሪዎች እንደ ፀሐይ በፈጣሪ የሚታዘዙ መሆን አለባቸው”
                  መጋቢ ሃዲስ እሸቱ አለማየሁ


    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር ደስ ብሎኛል፡፡ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ተስፋ ሰንቄያለሁ። አስተማማኝ ደህንነት እፈልጋለሁ፤ ወጥቼ መግባት፣ ሃገሬ ውስጥ እንዳሻኝ መንቀሳቀስ እፈልጋለሁ፡፡ እሳቸው ያደረጓቸው ንግግሮች ለዚህ ማረጋገጫ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ በንግግራቸውም ደስተኛ ነኝ፡፡ እንዲህ ሃሳብና ንግግር እርሾ ናቸው፤ ተግባር ደግሞ ዱቄት ነው፡፡ እርሾና ዱቄት ተዋህዶ ደግሞ ዳቦ ይፈጠራል፡፡ በሃሳብና በንግግር እርሾነት፣ በተግባር ዱቄትነት መልካም ኑሮ የሚባለው ዳቦ ይጋገራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ከጠ/ሚኒስትሩ ንግግር እኩል እኔን ያስደሰተኝ፣ በንግግራቸው የተደሰተው ህዝብ የነበረው ስሜት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ መሪው ምን አይነት ቋንቋ ይናገራል? የቱን እምነት ይከተላል? ከየት አካባቢ ነው የመጣው? የሚል ስሌት ውስጥ አይገባም፡፡ ህዝቡ የሚፈልገው በትክክል የሚመራውን ብቻ ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ በምሳፈረው ታክሲ ውስጥ ያለው ሹፌር ፕሮቴስታንት ይሁን፣ ትግሬ ይሁን፣ አማራ ይሁን፣ ኦርቶዶክስ ይሁን፣ ሙስሊም ይሁን---- የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ የኔ ፍላጎት መኪናውን በትክክል አሽከርክሮ ካሰብኩት ቦታ እንዲያደርሰኝ ብቻ ነው፡፡ ህዝባችን በትክክል የሚመራው፣ ትክክለኛ ሹፌር ካገኘ ጨዋ ተሳፋሪ ነው፡፡ ይሄን ልናይለት ይገባል፡፡
በሌላ በኩል በሃይማኖት አስተምህሮ፤ መሪዎች በፀሐይ ይመሰላሉ፡፡ ፀሐዩ ንጉሥ ይባሉ ነበር፤ ነገስታቱ፡፡ መሪዎች የፀሐይነት ባህሪ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በዓለም ላይ ፀሐይ ትልቁ የብርሃን ምንጭ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ነው አምፖል፣ ጧፍ፣ ሻማ፣ ኩራዝ የሚመጣው፡፡ እነዚህ ደግሞ ሰው እየለኮ ሰው ራሱ ያጠፋቸዋል፡፡ ፀሐይ ግን በሰው ትዕዛዝ የምትወጣ የምትገባ አይደለችም፡፡ ስለዚህ መሪዎች እንደ አምፖል በቆጣሪ ሳይሆን እንደ ፀሐይ በፈጣሪ የሚታዘዙ መሆን አለባቸው፡፡ ሁለተኛ፤ ፀሐይ ከሰማይ በመለስ ለሁሉም ነው የሚያበራው፤ አምፖል ደግሞ ከጣራ በታች ለቤተሰብ ነው የሚያበራው፡፡ መሪዎች ፀሐይ ናቸው፡፡ ፀሐይን ለመሞቅ ኦሮሚኛም ሆነ ትግርኛ፣ እስልምናም ሆነ ክርስትና መመዘኛዎች አይደሉም፡፡ ሰው ሁሉ ይሞቃቸዋል፡፡ መሪዎችን ልክ እንደ ፀሐይዋ ሁላችንም እኩል የምንሞቃቸው፣ ሲያቃጥሉን ደግሞ እኩል አቃጥለውን እኩል የምንናገራቸው፣ ሲያጠፉ እኩል የምንወቅሳቸው፣ ሲያለሙ ደግሞ እኩል የምናመሰግናቸው እንዲሆኑ እንጠብቃለን፡፡
ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ሰዎችና የሃይማኖት ሰባኪዎችን የሚያመሳስሉን ሶስት ፀባዮች አሉ። አንደኛ እኛ የገባን ሁሉ ህዝቡ ገብቶታል ብሎ መደምደም፣ እኛ ያልገባን ሁሉ ህዝብ አልገባውም ብሎ መወሰን፣ በሌላ በኩል እኔ የወደድኩትን ሁሉ ህዝብ ይወደዋል፣ እኔ የጠላሁትን ሁሉ ህዝብ ይጠላዋል ብሎ ሚሊዮኖችን በአንድ ጫማ ውስጥ አስገብቶ ማቆም ወይም ደግሞ ጠቅልሎ በአንድ መስፋት ይታያል፡፡ ይሄ ችግር ነው፡፡ ከዚህ ችግር መውጣት ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰባኪ መፆም ካቃተው ምዕመኑን ማሳነፍ የለበትም። ፖለቲከኞችም እነሱ የወደዱትን ሁሉ ህዝቡ ይወደዋል ማለት አይደለም። እኛ የወደድነውን ህዝቡ የመውደድ ግዴታ የለበትም፤ ህዝቡ የወደደውን ግን የመውደድ ግዴታ አለብን፡፡
አዲሱ መሪያችን እነዚህን ሁሉ ዙሪያ መለስ አስተሳሰቦች አዋደው ይመሩናል የሚል ተስፋ አለኝ። በቀን ሦስት ጊዜ እንበላለን ብለን ስንጠብቅ፣ በቀን ሦስት ጊዜ ወደ መባላቱ ልናሽቆለቁል ነበር፤ ከዚህ የማምለጫ መንገዱን የጨበጥን ይመስላል፡፡
ከንግግሮቻቸው የማረከኝ አንድነትን የመነዘሩበት መንገድ ነው፡፡ እዚህ ሀገር ላይ ስለ አንድነት የተንሸዋረሩ አመለካከቶች አሉ። አንድነቱን የተወሰነ ሃይማኖት ወይም ብሄር አድርጎ የመረዳት ችግር አለ፡፡ እሳቸው መደመር ጥንካሬ፤ ብርታት ነው ብለዋል፡፡ በንግግራቸው የጠቀሷቸው የጦርነት ቦታዎች አሉ፤ እነዚያ ቦታዎች ላይ ደማችን ነው የፈሰሰው እንጂ ቋንቋችን አይደለም። የኢትዮጵያውያን ደም ነው የፈሰሰው፡፡ ስለዚህ አንድነትን የገለፁበት መንገድ ለኔ ጠንካራ ነው። ልዩነት መረገም አይደለም ብለዋል፡፡ ይሄ ሁሉም ሊቀበለው የሚገባ ሃሳብ ነው፡፡ የቋንቋና የህዝብ ብዛትን እንደ መርገም ሳይሆን እንደ በረከት መውሰድ ይገባናል፡፡ በሌላ በኩል እናታቸውን ያመሰገኑበት መንገድ አርአያነት ያለው ነው፡፡ ብዙ ባለስልጣኖች በአደባባይ ስለ ሃይማኖታቸው፣ ቤተሰባቸው፣ ሚስታቸው ሲናገሩ አንሰማም። እርግጥ ነው ስለ ሃይማኖታቸው እንዲናገሩ አንፈልግም፤ ምክንያቱም እኛ መሪ እንጂ ሼህ ወይም ፓትርያርክ አይደለም የሾምነው፡፡ እምነታቸውን ሳይሆን ሰውነታቸውን፣ በጎ ህሊናቸውን ነው የምንፈልገው፡፡

-----------
           “የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር የብዙዎችን ስሜት የሚገዛ ነው”
                አቶ ግርማ ሰይፉ (የቀድሞ የፓርላማ አባል)

    የብዙዎችን ስሜት የሚገዛ በተሻለ ሁኔታ የተዘጋጀ ንግግር ነው ማለት ይቻላል - የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፡፡ ዘወትር የምንሰማው አሰልቺ የሆነ፣ የካድሬ ቋንቋ የለበትም፡፡ ስለዚህ የካድሬ ንትርክ ላሰለቸን ሰዎች፣ እንዲህ አይነት ንግግርን ማድነቃችን ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ውጪ ይዘቱን በተመለከተ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ችግሮችን በሙሉ በዚያ ንግግር ውስጥ ዘርዝሮ ለመግለፅ ቢሞከር፣ የፊደል ካስትሮ ንግግር ነው የሚሆነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ማሳጠራቸው ተገቢ ነበር፡፡ ንግግራቸውን ለማሳጠር ሲሞክሩ፣ አንዳንድ ነገሮችን እኛ በፈለግነው ጥልቀት ላናገኛቸው እንችላለን፡፡ ይህም ሆኖ ጥሩ ጥሩ ነገሮች በንግግሩ ተነስተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ይቅርታ የጠየቁበት መንገድ አንዱ ነው፡፡ በእርግጥ አቶ ኃይለማርያም “ይቅርታ” ማለትን አስለምደውን ነበር፡፡ ነገር ግን ይቅርታዎቹ ከልብ አይመስሉም ነበር፡፡ የዶ/ር አብይ ይቅርታ ከልባቸው መሆኑ ያስታውቃል። እያንዳንዱን ስማቸውን ጠርተው፣ ባለብን የዲሞክራሲ አያያዝ ችግር ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ፣ በተለይ ቦርቀው ያልጨረሱ ህፃናት--- በማለት ይቅርታ መጠየቃቸው፣ ልባቸው ለተሰበረ ቤተሰቦች ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ የእሳቸውንም ትልቅነት ያሳያል። ከዚያ በተጨማሪ የቀድሞውን ዘግተን አዲስ ምዕራፍ እንጀምር ተብሏል፡፡ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ይህን ማድረግ የሚያስችል ብዙ አጋጣሚዎች አግኝታ አልተጠቀመችበትም፡፡ አሁን በዚያ ቁጭት ተነስተን፣ ይህን እንደ አንድ አጋጣሚ ተጠቅመን፣ ወደ ተሻለ ደረጃ ብንወስደው ጥሩ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ንግግሮቹን ወደ ተግባር ለመለወጥ፣ አንዳንዶቹ የፍቃደኝነት ጉዳይን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲ ያስፈልገናል ይገባናልም ነው ያሉት፡፡ ነፃነት ደግሞ ከመንግሥት የሚሰጥ ችሮታ አይደለም፤ ሰው በመሆናችን ብቻ ያገኘነው ነገር ነው ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ እስካሁን እንዲህ እውቅና መስጠት ነበር ችግር ሆኖ የቆየው። ሌላው የሃሳብ ልዩነትን ማክበር ነበር ትልቁ ችግር። አሁን ግን የሃሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ የሃሳብ ልዩነት እርግማን ካልሆነና እንዲያውም በረከት ከሆነ፣ ዲሞክራሲንና ነፃነትን ማፈን አያስፈልግም፤ ምክንያቱም አፈና የሚኖረው ሌላውን ለመስማት ፍላጎት ሳይኖር ሲቀር  ነው፡፡
ለእናታቸው ያቀረቡትን ምስጋና ስሰማ እንባዬ መጥቷል፡፡ ለማርች 8 ለእናቴ የፃፍኩት አንድ ግጥም ነበረ፡፡ እሱን ነው ያስታወሰኝ፤ ንግግራቸውን ብቻዬን ስሰማው ነበርና እንባዬ ነው የመጣው። እናቱን የሚወድ፣ ለቤተሰቦቹ ዋጋ ያለው ሰው፣ ልጅ የሞተባትን እናት ቁስልና የህሊና ጠባሳ ይረዳል። ይሄን በማለታቸው በእውነት ጥሩ ነገር ነው ያደረጉት፡፡
እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው፣ መብራት አጥፍቶ ግፍ አይሰራም፡፡ ምክንያቱም ሰው ባያየኝ፣ የሚያየኝ ፈጣሪ አለ ይላል፡፡ አቶ ኃይለማሪያም አማኝ በመሆናቸው፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ነበራቸው፡፡
 ሌላው ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፤ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ ሲሉ በጣም ነው ደስ ያለኝ። እኔ በፓርላማው እሳቸው ያሉትን ቃል በቃል በተናገርኩ ጊዜ፣ ፓርላማው በሙሉ ነበር  የሳቀው፡፡ ዛሬ ግን አጨብጭበዋል፡፡ የፓርላማው አባላት ለዶ/ር አብይ ሲያጨበጭቡ፣ ያኔ ያደረግሁት ነገር የበለጠ ትክክል እንደነበረ ተጨማሪ ማረጋገጫ አግኝቻለሁ፡፡

----------
                   “ህዝቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል”
                     አያልነህ ሙላት (ገጣሚና ጸሃፌ ተውኔት)

    በከፍተኛ ስሜት ነው ንግግሩን የተከታተልኩት። ይህ የሆነበት ምክንያትም ለብዙ ዘመናት ከኢትዮጵያ ምድር ደብዛቸው ጠፍቶ የነበረ ኢትዮጵያዊነትና አንድነት የሚሉት ጉዳዮች ጎልተው በመውጣታቸው  ነው፡፡ ይህ ለኔ ከፍተኛ ስሜትን ነው የፈጠረብኝ፡፡ በአብዛኛው የተጠማነው ይሄን ነገር ነበር፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ይሄን ጥማት አርክቶልናል፡፡ ግን በንግግር ብቻ መርካት አስቸጋሪ ነው፡፡ ንግግሩ እንዴት በተግባር ይተረጎማል? የሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ ለወደፊት በተስፋ የሚጠብቀው ይመስለኛል፡፡ ንግግሩ ወደ ተጨባጭ ነገር ተቀይሮ ለውጥ መምጣት አለበት፡፡ አለበለዚያ በቃላት መካካብ ብቻ ሆኖ ይቀራል የሚል ስጋት ስላለኝ፣ በቶሎ ወደ ተግባር መለወጥ ይገባዋል፡፡
ይህን ለማድረግ በዋናነት ሦስት ነገሮች የሚያስፈልጉ ይመስለኛል፡፡ አንደኛው፤ ኢህአዴግ ንግግሮችን የህዝብን ቁጣ ለማብረድ ብቻ የተጠቀመበት ሳይሆን ከልቡ አምኖ የፈፀማቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ሁለተኛው፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሄን ሳያረጋግጡ ወደዚህ ስልጣን ይሸጋገራሉ ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም ከጀርባቸው ያኮረፈ ትውልድ አለ፣ በጥቅም የተሳሰረና የበለፀገ ካድሬ አለ፡፡ ይሄን እንዴት ወደ ለውጡ ማምጣት እንደሚቻል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ይሄ ተሃድሶ /ለውጥ/ ስለሆነና በማሳመንም ብቻ የሚከወን ስላልሆነ ጠ/ሚኒስትሩ በቀላሉ ይወጡታል ብዬ አልገምትም፡፡ ህዝቡም ይሄን ነገር አሁኑኑ ውለዳት ከማለት ይልቅ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ትዕግስት ከሌለ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ራሳቸውን ወደ ተስፋ መቁረጥ ስለሚመራቸው ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ ህዝቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደ ጋን የሚቆጥራቸው ከሆነ ጠጠር ሆኖ ሊደግፋቸው ይገባል፡፡ ምሁሩም ከትዝብት ወደ ተሳትፎ መሻገር አለበት፡፡
እኚህ ጠቅላይ ሚኒስትር በንግግራቸው ይቅርታ መጠየቃቸው ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ እርግጥ ነው አሁን የፓርቲ ለውጥ አልተደረገም፡፡ ነገ የምንጠብቀው ደግሞ ያለ ጥይት ድምፅ፣ አንድ ፓርቲ በአንድ ፓርቲ ሲለወጥ ማየት ነው፡፡ በቀጣይ በጉጉት የምንጠብቀው ይሄንን ነው፡፡
ተፅፎ የተሰጠውን የማያነብ መሪ ነው ያገኘነው። ለዚህም ወላጅ እናታቸውን ማመስገናቸው፣ ከዚህ በፊት የሰለቹ ቃላትን አለመጠቀማቸውና ስለ ሀገራቸው ያላቸውን ምኞት መግለፃቸው ንግግሩ የራሳቸው መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ዶ/ር አብይ እናታቸውን ሲያመሰግኑ፣ ሃገራቸውን እንዳመሰገኑ ነው የገባኝ፡፡ ሚስታቸውን ሲያመሰግኑ የስኬታቸውን ምንጭ ነው ያመሰገኑት፡፡ ይሄ አስደሳች ነው፡፡ እኔ በንግግራቸው በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡

Read 3632 times