Print this page
Saturday, 07 April 2018 00:00

የጠቅላይ ሚኒስትራችን እናት!

Written by  መኮንን ተሾመ ቶሌራ (ዘገዳም ሰፈር)
Rate this item
(0 votes)

 አንዳንድ ጊዜ አስገራሚ ጥያቄዎች ወደ አእምሮአችን በራሳቸው ጊዜ ይመጣሉ፡፡ ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር አቢይ አህመድ፣ ባዕለ ሲመታቸውን ሲያደርጉ አንድ ነገር አስደሰተኝ፡፡ የተደሰትኩበት ነገር በሹመቱ አይደለም፣ በደማቅ ሥነ-ሥርዓቱም አልነበረም፡፡ በአንድ ባልተለመደ ክስተት እንጂ፡፡
ክስተቱ የእናት፣ የሚስት፣ የልጆችና ባጠቃላይ የቤተሰብና የሰው ጉዳይ በመሆኑ ልዩ ስሜት ፈጠረብኝ፡፡ ሁኔታውም አንድ አስገራሚ ጥያቄም ጫረብኝ፡፡ የእስከዛሬ መሪዎቻችን እናት አልነበራቸውም?  የሚል ጥያቄ፡፡ ለነገሩ የጥያቄው መልስ ግልፅ  (Rhetorical) ነው፡፡ ነበራቸው። ይሁንና ጥያቄው የመነጨው ከነበረን ልምድና ታሪክ መሆኑ ግን እሙን ነው፡፡ የቀድሞ መሪዎቻችን ንግግር ሲያደርጉ፤ ስለ ሰው ሳይሆን ስለ ግዑዝ ነገር፣ ስለ ቀላል ነገር ሳይሆን ስለ ውስብስብ ሃሳብ፣ ስለ መረዳት ሳይሆን ስለ ማስረዳት እንደነበረ እናውቃለን፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ቀደምት መሪዎች ሰዋዊ በሆነና ማንነታቸውን በሚያሳይ መልኩ እራሳቸውን ሳያቀርቡ፣ እኛም ሳንረዳቸው እንደተራራቅን፣ ጊዜያቶች አልፈዋል፡፡
ለምሳሌ ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ፤ በረዥም የሥልጣን ዘመናቸው ጊዜም ይሁን “ህይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” የተሰኘውን ግለ-ታሪካቸውን በሚፅፉበት ወቅት፣ ስለ እናታቸው ስለ ወ/ሮ የሺመቤት አሊ አባ ጂፋር በአጥጋቢ ሁኔታ ሳይናገሩ አልፈዋል እየተባሉ ብዙ ጊዜ ይተቻሉ፡፡ ከዚያም በኋላ ቢሆን ሃገራችንን ያስተዳደሩ መሪዎች ብዙ ስለ ቤተሰቦቻቸውም ሆነ ስለ ሌላው፣ ሰዋዊ ስሜት ባለው (human interest) መልኩ ተናግረው ስሜት ሲኮረኩሩ ያስተዋልን አይመስለኝም፡፡
ስለ ሰው በመናገር፣ ስለ ሰው በማሰብ፣ ስለ ሰው (ተቃዋሚዎቻቸውን ጨምሮ) በመጨነቅ ሲናገሩና ሲያስተምሩ ያየነው በጣም ለጥቂት ጊዜ ይመስለኛል፡፡ ይህንን ስል የሚሰሩት ነገር ለሰው የሚጠቅም አልነበረም ለማለት እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ፡፡ የኔ ትኩረት በአብዛኛው ስለ አንደበታዊ ቃላቸው መሆኑን ያዙልኝ፡፡ እከሌ ከእከሌ ሳይሉ ስለ ሰው ዘር በሙሉ የሚናገሩበትን አንደበታቸውን መሆኑንም አትዘንጉብኝ፡፡
“መልካም ምላስ ቁጣን ታበርዳለች” እንደሚባል፣ መልካም ግንኙነት የሚጀምረውም ከመልካም አንደበት ነው፡፡ በመሆኑም ፍቅር መልካም ስሜትና ሰዋዊነት (human interest) ያለው ንግግርም የነገሮች ሁሉ አልፋና ኦሜጋ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የንግግር ጥበብ (public speech) ሊቃውንትም የሚመክሩት ይህንኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የንግግር ዶክተር ተብሎ የሚታወቀው አሜሪካዊው ዶ/ር ጂም አንደርሰን ስለ human interest ንግግር አስመልክቶ ሲፅፍ፤ “It is a story that will cause your audience to take interest in the people that the story is about” በማለት ቀልብን ለመሳብ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሞ፣ ለሚገጥሙ የአድማጭ እርካታ ችግር መፍትሄ ሲመክር፣ ይህንኑ ሰዋዊ ስሜት መፍጠር ጠቃሚ እንደሆነ “A simple solution is one that always seem to work: USE THE HUMAN INTEREST STORY.” ብሏል፡፡
በመሆኑም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን፣ ስለ እናታቸውና ስለ ቤተሰባቸው እሳቸው እንዳሉት፤ “ባልተለመደ ሁኔታ”
አንስተው ማመስገናቸው ከፍ ያለውን የሰዋዊነት እሳቤያቸውንና “ቤተሰብ የህብረተሰብ መሰረት ነው” የሚለውን
ፍልስፍና የሚያሳይ እንጂ የሳቸው ቤተሰብ ላይ ብቻ ያተኮረ አይመስለኝም፡፡ እናም ዶ/ር አብይ ንግግራቸውን ሰዋዊ በሆነ መንገድ እንደጀመሩት፣ በመጭውም ጊዜ ተግባራቸውንም ሰው ላይ ያተኮረ፣ሰውን የሚለውጥ፣ ሰውን የሚያከብር ይሆናል ብዬ እተማመናለሁ፡፡
 ሌሎቻችንም እስከ ዛሬ እንደነበረው በስማ በለው ሳይሆን ልክ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ስለ እናታቸዉ ታሪክ በሚያስደስት መልኩ እንደነገሩን፤እራሳችን የራሳችንን ታሪክ እየተረክን፣ የሌላውን እያደመጥን፣ ሰውን እያሰብን፣ ሰዋዊ እየሆንን እንደምንሄድም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡


--------------------------

Read 1502 times