Print this page
Saturday, 07 April 2018 00:00

“ሰውየው በቃል የመፈወስ ተሰጥኦ አለው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የጠ/ሚ አብይን ንግግር በጽሞና አደመጥኩት። ታሪካዊ ንግግር ነው። ሲጠቃለል፣ ሰውየው በቃል የመፈወስ ተሰጥኦ አለው። አይተናል። ሰምተናል። ቀጥልበት እንለዋለን።
ከ27 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያችን፣ በኢትዮጵያ ፓርላማ፣ በኢትዮጵያ መሪ በክብር ተዘከረች፣ የመጽናናትን ቃል ሰማች።
ኢትዮጵያ “መጪው ጊዜ የፍቅርና የይቅርታ ነው፤” ተዘጋጂ ተባለች። ድንቅ ነው።
ከመሪዎቿ መልካም ተግባርን ብቻ ሳይሆን መልካም ቃላትንም ተነፍጋ የሰነበተች አገር፤ በዚህ ንግግር በሐሴት ብትሞላ የሚያስደንቅ ሊሆን አይገባም። ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፏል። በአብይ ንግግሩ ቅር ሊሰኙ የሚችሉት ሰዎች ቢኖሩ በጣም ጥቂት ናቸው።
አሰባሳቢና ጋባዥ ንግግር ነው።
ለበዓለ ሢመት የተገባ፣ ጊዜውን የሚመጥን ንግግር ነው። (እርግጥ ከ35 ደቂቃ ማጠር ይችል ነበር። መሰል ንግግሮች የይዘት ዝርዝር ሳይሆን የመንፈስ ጉዳዮች ናቸው። አብይ ንግግሩን የገነባው በለውጥ፣ ተስፋና በአንድነት ዙሪያ ነው። ሁሉንም የንግግሩን ዘለላዎች እያነሣን ብንተነትን፣ ማሰሪያቸው የለውጥ ተስፋና አንድነት ሆኖ የምናገኘው ይመስለኛል። ስለ እናቱና ሚስቱ ባነሣበት የተዘክሮ ዘለላው ሳይቀር፣ ውለታቸውን በማስታወስ በኩል የሚጠራን ወደ ተስፋና ትብብር ነው። ኢትዮጵያውያን በየዳር ድንበሩ መሰዋታቸውን ያነሣበት አቀራረብም እንደዚያው ነው። ሌሎችም ይኖሩ ይሆናል። ያስቀመጠው የለውጥ ተስፋ የማያረካው ሰው ቢኖር፣ ስለ አንድነታችንና ስለ ጋራ ታሪካችን ያነሣው ያካክስለታል። በተገላቢጦሹም እንደዚያው። እንደ ቀዳሚዎቹ መሪዎች የኢህአዴግን ስኬቶች በማጋነን አልተጠመደም። እያንዳንዱን ስኬት ጠቅሶ የሚያስከትለው ጎዶሎ እንደነበረና ለውጥ እንደሚያስፈልገው ነው።
የአብይ ንግግር የሚለየው በአቀራረቡ ብቻ ሳይሆን በመንፈሱም ነው።
የራሱ የንግግር/አጻጻፍ ስልትም በጉልህ ተለይቶ የሚታይ ነው። እንደ ጭብጥ ብቻ ካየነው ግን ጥቂት የማይባሉትን ጭብጦቹን በሁለቱ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትሮች ንግግሮች ውስጥ የምናገኛቸው ናቸው። --- ጊዜው ያላቸው ሰዎች በስፋት ቢተነትኑት እመኛለሁ። ማሰሪያው ግን ተስፋው ወደተግባር የሚለወጥበትን ፍኖተ ካርታ ማቅረብ ነው። አብይ በቀጣዮቹ ቀናት፣ ቢበዛ ሳምንታት ውስጥ ዋና ዋና የትግበራ አቅጣጫዎቹን ማሳወቅ ይኖርበታል። የአፍህን ሰማን፤ እጅህ ከምን?!
መልካም ዕድል፣ ኢትዮጵያችን
(መስፍን ነጋሽ - ከፌስቡክ)

Read 919 times
Administrator

Latest from Administrator