Saturday, 07 April 2018 00:00

ጊዜ የማይሰጡ የአብይ አጀንዳዎች፤

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)


    ብረትን የተፈለገውን ቅርጽ እንዲይዝ ማድረግ የሚቻለው እንደ ጋለና እንደ ጋመ በመቀጥቀጥ ነው፡፡ ከቀዘቀዘ ለማጋል የመጀመሪያውን ያህል ጊዜና ጉልበት ይጠይቃል፡፡ በፖለቲካ ጉዳይ ላይ የተመቻቸውን ሁኔታ በወቅቱ አለመጠቀም እጅግ ይጎዳል፡፡  ተቃውሞውን ተመልሶ እንዲቀጣጠል በማድረግ ላልታሰበና ላልተጠበቀ መስዋዕትነት ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የመጀመሪያ ሥራ፤ ይህን የሕዝብ ትግል መጠበቅ ይሆናል፡፡
ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የኦሮሚያ፣ የአማራ እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ኢሕአዴግ በሚመራው መንግሥት ላይ ከፍተኛ ሕዝባዊ አመጽ ሲያካሒድ ቆይቷል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ገብሯል፡፡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት ደግሞ በእስር ቤት ተሰቃይተዋል። በቢሊዮን የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡ አሁን የምናየው የለውጥ ምልክት ከዚህ መስዋዕትነት የተገኘ ፍሬ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡
ኢትዮጵያዊያን ፤ የአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የማይኖርባት፣ የፖለቲካ ችግሮች በኃይልና በመሳሪያ ሳይሆን በድርደር የሚፈቱባት፣ ዜጎች በነጻነት ሃሳባቸውን የሚገልፁባት፣ የመሰበሳብ የመደራጀትና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት የተከበረባት፣የሕግ የበላይነት የሰፈነባት፣ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ሃብት ማፍራት የሚችሉባት ኢትዮጵያን ለማየት ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ታግለዋል፤ እየታገሉም ናቸው፡፡
ይህ ትግል በሕዝብና በመንግሥት መካከል ተወስኖ የቀረ ሳይሆን በገዥው ጥምር ፓርቲ አባላት መካከልም ገብቶ ‹‹እስከ መቼ ከዳር ቆመን እናያለን?›› ብለው እራሳቸውን እንዲጠይቁ ያደረገ ሆኗል፡፡ እያንዳንዱ ሰው እራሱን እንዲጠይቅ መገደዱ ደግሞ ለለውጥ እሩቅ የሆነው ኢሕአዴግ፤ ትንሽም ቢሆን ለለውጥ እንዲጋለጥ ገፍቶታል። ዶ/ር አብይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀ መንበር አድርጎ በመረጠበት ጊዜ የተመዘገበው የድምጽ ልዩነት የሚያመለክተው፣ ይብዛም ይነስ ይህንኑ የለውጥ ጅማሮ ነው፡፡
ሕዝብ ታስሮም፣ ተደብድቦም፣ ተገድሎም ይህን ለውጥ አምጥቷል፡፡ ይህ ለውጥ ወደ ፊት ይገሠግሥ ዘንድ፣ ለውጡ ወደ ከፍተኛው የሥልጣን እርከን ማለትም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያበቃቸው ዶ/ር አብይ አህመድ በልበ ሙሉነት መራመድ፣ ሥልጣናቸውንም  በጊዜውና በቦታው መጠቀም መቻላቸውን በግልጽ ማሳየት ይኖርባቸዋል። በትልቁም በትንሹም መግባት የለመደውን የኢሕአዴግን  የቡድን አመራርና አሠራር፤ እንደ አቶ መለስ ጥግ ማሲያዝ  አለባቸው፡፡ ይህን እንዲያደርጉ የሚያስፈልገው ኢሕአዴግ በውድም በግድም ወደ ለውጥ መገፋት ስለአለበትም ጭምር ነው፡፡
ዶ/ር አቢይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ያልነበራቸው የሕዝብ ድጋፍ እንዳላቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ድጋፍ ጋሻና መከታ ብቻ ሳይሆን መዋጊያ ጦር  አድርገው መጠቀምም የእሳቸውን ቁርጠኝነት ይጠይቃል። በድርጅት ዲሲፕሊን ከታሰሩ ጉድ ይፈላል፡፡ የህዝብን ጥያቄዎች መመለስ አይችሉምና!!
አቶ ኃይለ ማርያም ሥልጣን  በያዙ ጊዜ እያንዳንዱን እርምጃቸውን ሊቆጣጠሩ የሚፈልጉ ሰዎች  የነበሩትን ያህል አሁን ይኖራሉ ብዬ አላስብም፤ ‹‹በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የእንቶኔ  ዘርፍ አስተባባሪ›› እየተባለ  ሰው ላይሾምባቸው ይችላል፡፡  እንደዚህ ዓይነት ሰንሰለት አይናቸው እያየ በእጃቸው ላይ  ያስገባሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ከገባ ደግሞ ለውጡ ከዳር ሳይደርስ መደናቀፉ ስለማይቀር  ያልተጠበቀ አመጽ ሊቀሰቅስ እንደሚችል  መናገር ነብይነት አይጠይቅም፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ሆኑ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ምክር ቤቱ እንዲሁም ተራው የኢሕአዴግ አባል ማወቅ ያለበት፤ ለዶ/ር አብይ እየተሰጠ ያለው የሕዝብ  ድጋፍ ለእሳቸው እንጂ ለኢሕአዴግ አለመሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ የዶ/ር አብይን መመረጥ ስደግፍ፤ የደገፍኩት በሀገርም በኢሕአዴግም ላይ ለውጥ ያመጣሉ ብዬ በማመን ነው፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ ሕዝብ እየሰጠ ያለው ድጋፍ ለእሳቸው እንጂ ለድርጅቱ አለመሆኑን ለይተው ይገነዘቡታል ብዬ አስባለሁ፡፡ መገንዘብም አለባቸው፡፡ ያለዚያ ክንዳቸውን  ያለ አግባብ ያዝሉታል፡፡
ዶ/ር አብይ ኢሕአዴግን እንደ ጋለ ብረት መቁጠርና ማየት፣ አዲስ ቅርጽ እንዲይዝ ለማድረግ መወሰንና ባለ ኃይላቸው ለተግባር ፈጥኖ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው ሊረዱ ግድ ይላል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ከዚህ ቀደም የገለጡት ሃሳብ እውነት ከሆነ፣ ኢሕአዴግን ከዘር ድርጅት ስብስብነት ለማላቀቅና ኅብረ ብሔር ለማድረግ ከዚህ የተመቸ ጊዜ አይኖራቸውም፡፡ ኢሕአዴግን ለመለወጥ አለመፍጠን፣ አሁን አንገቱን የደፋው አኩራፊ  አክራሪ ብሔርተኛ ኃይል እንዲያንሰራራ እድል የሚሰጥ  ከመሆኑም በላይ  የተገኘውንም ለውጥ የሚቀለብስ ይሆናል ብቻ ሳይሆን በድፍረት ለመናገር “መመታትም”  ያስከትላል፡፡ ይህ ደግሞ የታወቀ የድርጅቱ ባህል መሆኑ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡
ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠበቅ አድርገው፣ ጊዜ ሰጥተው ሊይዙት የሚገባው ጉዳይ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ ያደረጉላቸው ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም  ከሀገር ውጪና በሀገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ጉዳይ ነው፡፡
ከሁለት ሚሊዮን ያላነሱ ኢትዮጵያዊያን በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በኤሽያ እንደሚኖሩ የታወቀ ነው፡፡ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በጀርመን ወዘተ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን አብዝተው በሀገራቸው የፖለቲካ ጉዳይ የሚሳተፉ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ዶ/ር አብይ እንዳሉት፤ እነሱ ከሀገራቸው ከኢትዮጵያ ቢወጡም ኢትዮጵያን ከእነርሱ ልብ  ሊያወጧት ስላልቻሉ ያደረጉት  ነው፡፡ ስለዚህም ወደ አገራቸው እንዲመጡ መጋበዝ ብቻ ሳይሆን አገራቸው ሲገቡ  ችግር እንደማይደርስባቸው ማረጋገጫ ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ሁሉም ልበ ሙሉ ይሆን ዘንድም አስፈሪውን የአስቸኳይ  ጊዜ አዋጅ ማንሳት ይኖርባቸዋል፡፡
‹‹ሕወሓትም ሆነ ሌሎች ታጋይ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄዎቹን በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ እንጂ ጦርነትና ደም መፋሰስ መፍጠር ፍላጎታቸው አይደለም፡፡ ጠበንጃ ለማንሳት የተገደዱት የሰላምና የዲሞክራሲ መንገድ በደርግና በሳዳሪዎቹ በጠበንጃ ስለተዘጋባቸው ነው›› ሲል እ.ኤ.አ ሰኔ 21 ቀን 1989 ዓ.ም መግለጫ ያወጣው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)፤ በኢትዮጵያ መንግሥት ወሳኝ ኃይል ሆኖ ባለበት ጊዜ ሁሉ የውይይትና የድርድርን በር እሱና አጋሮቹ ግጥም አድርገው ዘግተውት  እንዲኖሩ አድርጓል፤ አድርገዋልም፡፡ይህንን ዶ/ር አብይ በድፍረትና በልበ ሙሉነት ሊሰብሩት ይገባል፡፡
መንግሥት ራሱ በአንዳንድ የአማራ፣ የቤኒሻንጉልና የኦሮሚያ አካባቢዎች ጥይት እየጮኸባቸው መሆኑን እየተናገረ ነው፡፡ ይህም መፍትሔ ይፈልጋል፡፡
ኦነግ የሽግግሩ መንግሥት መስራች ነበር፡፡ የግንቦት ሰባት መሪዎች በ1997 አገር አቀፍ ምርጫ ተወዳዳሪዎች ነበሩ፡፡ ሁሉም ወደ መሣሪያ ትግል የገቡት የሰላምና የዲሞክራሲ መንገድ ስለተዘገባቸው እንደሆነ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት በነዚህ ሁለት ድርጅቶች ላይ የሰጠውን ‹‹ የአሸባሪነት ›› ስያሜ ማስነሳትና ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ድርድር መጀመር፣ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር  አብይ መንግሥት  ቀዳሚ ሥራ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው ለማንም ተብሎ ሳይሆን ለአገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ነው፡፡ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን!!
በመጨረሻም፡- ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ መልካም የሥራ ጊዜ  ከልብ እመኛለሁ፡፡ መልካሙን ጊዜ ያምጣልን!!    

Read 911 times