Saturday, 07 April 2018 00:00

የእንቆቆ ‘ናፍቆት’---

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

“--የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ህመሙ እንደይከብድ እያሾፍንም፣ ባስ ሲል ‘እያቧለትንም’ ክብደቱን ልናቃልለው የምንሞክረው የምግብ ፍጆታዎች ዋጋ ነገር እየዋለ እያደረ፣ የት እንደሚያደርሰን ለመገመት እንኳን ያስቸግራል፡፡
 

    እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንግዲህ ያው ዛሬ ዋዜማ ላይ ነን፡፡ መልካም ዋዜማ ያድርግልንማ! እንግዲህ እንደሌላው ጊዜ ቢሆን ኖሮ… “እባካችሁ፣ ቅባት አታብዙ፣ ደርቆ የከረመ አንጀት በአንድ ጊዜ ብዙ ቅባት ሲያገኝ ጥሩ አይደለም፡፡ ደግሞ ቀይ፣ ቀዩን እንጂ ጮማው ጤና አይሆንም” ምናምን እያልን እንመካከር ነበር። ‘ነበር’ የሚባሉ ነገሮች እየበረከቱ፣ እየበዙ በሄዱ ቁጥር አሪፍ አይደለም፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ድሮ፣ ድሮ እኮ…አለ አይደል… “ባጣ፣ ባጣ ዶኬዬን የሚወስድብኝ የለም” የምንላት ነገር ነበረችን፤እናም…በጊዜዋ ‘ለሁሉም ተደራሽ’ የነበረችው ‘ዶኬ’፤ ለረሀባችን እንደ አምቡላንስ ነገር ነበረች፡፡
“ዛሬ እዚህ ቤት ምሳ የለም እንዴ?!”
“በቤቱ ምግብ የታለና!”
“ትንሽ የተራረፈ ስጋ ቢጤ እንኳን የለም?”
“እውነት! ስጋ አማረህ! ስማ፣ አይደለም ቤት ውስጥ ስጋ ሊኖር፣ አምሮቱ እንዳይገድለኝ በሉካንዳ በራፍ በኩል ማለፍ እንኳን ትቻለሁ፡፡”
“በጣም ነው የራበኝ፣ በቃ  የሚበላ ነገር ከሌለ ሹሮ ቢጤ ስጪኛ…”
እናላችሁ…ሹሮ መደብ የማትለይ፣ ‘ኮሚኒስታዊ’ አይነት ምግብ ስለነበረችና “ሹሮ የለም፣” አይነት ነገር ስላልነበር፣ “ምግብ ከሌለ አቅርቡልኝ…” የምትባል ነበረች፡፡ አሁን…ዘመኑ ወዳጅ የማይበረክትበት ሆነና ‘ካፒታሊስት’ የሚሉትን ነገር አድርገዋታል መሰለኝ…ተራራቅን፡፡ ይቅርታ፣ “እንተዋወቅ ነበር እንዴ!” የሚባልበት አይነት መራራቅ፡፡
አሁንማ… ‘እከሌ ሉካንዳ’ ‘እከሊት ክትፎ ቤት’ ይባል እንደነበረው፣ አሁን ፋሺኑ “እከሊት ሹሮ ቤት” ሆኗል፡፡ “ሹሮ እንኳን አልፎላት ቦሌ ትግባ!” ያላችሁ ወዳጆቻችን… ስጋታችሁ ለቦሌዎቹ ነው፣ ለራሳችሁ!?
የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ህመሙ እንደይከብድ እያሾፍንም፣ ባስ ሲል ‘እያቧለትንም’ ክብደቱን ልናቃልለው የምንሞክረው የምግብ ፍጆታዎች ዋጋ ነገር እየዋለ እያደረ፣ የት እንደሚያደርሰን ለመገመት እንኳን ያስቸግራል፡፡ አልፎ፣ አልፎ እንደ ‘ሴሌበሬሽን’ አይነት ነገር፣ ወጣ ብሎ ‘ጎረስ ማድረግ’ም ሜሞሪ ነገር እየሆነ ነው፡፡
“ማሬ፤ ዛሬ እስቲ ደህና ምግብ ቤት ሄደን እራት እንብላ” የሚባባሉ ጥንዶች ወይ እሱ እቁብ ደርሶታል፣ ወይ እሷ በሆነ ነገር ‘ዊንድፎል’ ትርፍ አግኝታለች (ቂ…ቂ…ቂ…) የእውነት ግን… የመመገቢያ ቤቶች ሂሳብ ንረት ለኤኮኖሚ ባለሙያዎችም ሳያስቸግር አይቀርም። በመቶ ብር ጥግብ ተብሎ ‘የአንበሳ ሊመስል የተቃረበ ግሳት’ እያሰሙ፣ የሚኬድበት ዘመን እኮ ይህን ያሀል ርቀት አልነበረውም! (በሀያ ምናምን ብር ጨልጦ፣ ጨልጦ ከመንግሥት እስከ መንደር ሁሉንም ሙልጭ አድርገው እየሰደቡ፣ በውድቅት ሌሊት ቤት የሚገባበት ጊዜ ይህን ያህል ሩቅ እንዳልነበር ለመጥቀስ ያህል ነው፡፡)
እናማ…ሁሉም ታሪክ እየሆነ መጥቷል፡፡ ዘንድሮ እኮ ሁለት ጓደኛሞች የጠረጴዛ ልብሱ ያልተቀደደ ምግብ ቤት እራት በልተው ቢሉ ሲመጣ፣ የአክስዮን ክፍያ ሊመስል ምንም አይቀረው! ያለማጋነን ለአስራ ምናምን ቀን የአባወራ ቀለብ ይበቃል!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ምንም ቢያቅት እኮ በቡድን እየተደራጁ ጥሬ ስጋ ‘የሚከሸከሽበት’ ጊዜ ነበር፡፡ ሉካንዳ ሲገባ እኮ ህዝቤ ቢላውን እያፋጨ ለ‘ምተራው’ ሲዘጋጅ…አለ አይደል…የኦሎምፒክ ሻምላ ውድድር የሚሳተፍ ቡድን ልምምድ ላይ ይመስል ነበር፡፡ እናላችሁ …አንዷን ኪሎ አራትም፣ አምስትም ሆኖ መቃመስ ይቻል ነበር… ‘ዋናው ፍቅሩ ነው’ ይባል በነበረበት ጊዜ፡፡ ዘንድሮ ስጋና የከብት ተዋጽኦዎች ጉዳይ የተመጣጠነ ምግብ ነገር ሳይሆን፣  የመደብና የ‘ለግዠሪ’ ጉዳይ ሆኗል፡፡
“አጅሬው፣ እንዲህ ጭምድድ ያልከው ምን ሆነህ ነው?”
“እባክህ ድክም ብሎኛል፤ አቅም አነሰኝ”
“አንተ በደንብ አትመገብማ፤ዶሮ ይመስል ጫር፣ ጫር እያደረግህ ታዲያ ምን ልትሆን ነበር!”
“መቼም የአቅሜን ያህል ምስሯንም፣ ጎመኗንም መብላቴ አልቀረም” (እግረ መንገድ...አሁንም “እርቦኝ ምስር ወጥ ከምበላ ሉካንዳ ሽንጥ ተደግፌ ፎቶ ብነሳ ይሻለኛል” የሚሉ ሰዎች አሉ እንዴ?!)
“የምን ምስር! የምን ጎመን! አንተ ራስህ ተምች የመታው አጠፋሪስ መስለህ እንደገና ጎመን!…ይልቅ ስማ፣ አንድ የሰባ ሙክት ግዛና እሱን ሸክ አድርገህ ሰባት፣ አስር ቀን መረቅህንና ጮማህን ከከሰከስክ ምን አለ በለኝ… ‘የቤቴ በር ይስፋልኝ፣ አላስገባ አለኝ’ ባትል!”
ሙክት! ያውም ለመረቅና ለጮማ የሚሆን የሰባው! በአሁኑ ጊዜ እንዲህ የሚመክር ሰው ካለ ወይ ‘ፌክ ኒውስ’ በማሰራጨት፣ ወይ ደግሞ “መካከለኛ ገቢ ስንደርስ እንኳን ለማሳካታችን እርግጠኛ ያልሆንነውን ተስፋ ለአንድ ምስኪን ዜጋ በመስጠት” በሚል ሊጠየቅ ይገባል። አሀ፣ ልክ ነዋ… ሙክት! ያውም ለመረቅና ለጮማ የሚሆን የሰባው!
ጤፍና ጄሶ እየተቀላቀለ ‘ማኛ፣ ሰርገኛ’ ምናምን የሚባልበት ዘመን እኮ ነው! …ዘይት ከቅቤ ጋር ቀልጦ… “ቅቤ ይጨመር እንዴ?” እየተባለ ክትፎ ላይ ይቸለሳል የሚባልበት ዘመን እኮ ነው! እናማ… በምግብ ብዙ ፎርጅድ የሚባሉ ነገሮች የመጡበት ዘመን ነው፡፡ (የተንጠለጠለና በምናምን መቶ ሻማ አምፖል የሚያብረቀርቅ ሽንጥ ሁሉ የ“አያ በሬ ሆይ” ላይሆን እንደሚችል ማሰቡ ጥሩ ነው፡፡ የምር ግን፣ ስሙኝማ…የመንግሥተ ሰማያት ሰነድ የሚሠራው ምድር ላይ ቢሆን ኖሮ… ይሄኔ ጉድ ፈልቶ ነበር። “በሀሰተኛ ማስረጃ መንግሥተ ሰማያት የገባችሁ የጦቢያ ልጆች በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ራሳችሁን እንድታጋልጡ” ምናምን የሚል ማስታወቂያ በቀን አስር ጊዜ ይነገር ነበር፡፡
በነገራችን ላይ…“ምን ግርም ይልሀል?” በሉኝማ… መቼም ንጭንጩ ላይ ሁላችንም እንደየአቅማችን አለንበት፡፡ “አገንፍተው ላመጡት ፓስታ ሰማንያ አምስት ብር!” “ይሄ ምኑ ጭቅና ነው፣ ጭቆና ነው እንጂ!” እያልን ስናማርር እንከርማለን፡፡ (በነገራችን ላይ… ከላይ ፓፓዬ፣ ከታች ፓፓዬ አድርገው ፍሪጅ ውስጥ ያሳደሩት ‘አኞ’ ስጋ በማግስቱ ምን የመሰለ ጭቅና ይወጣዋል የሚል ‘ሀሜት’ አለ…ለጠቅላላ እውቀት ያህል ነው፡፡)
እናም…ብዙዎቻችን  እንደዛ ስናማርር የከረምነው ቤት…ሳምንት ሳይሞላን ሄደን፣ “ሰዉ ቶሎ፣ ቶሎ በልቶ ቦታ አይለቅም እንዴ!” እያልን ተራ ስንጠብቅ እንገኛለን።…እንዲህ እየተነጫነጭንም… “ለእነሱ ምግብ ይሄን ያህል ከምከፍል እቁብ አልጥልበትም! እያልንም…ስንሰለፍ እንታያለን፡፡
እኔ የምለው…በስጋ እጦት ሊናፍቁ የማይገቡ ነገሮች ቢናፍቁንስ! ኮሶ ብትናፍቀንስ! እንደዛ እያሯሯጠ ሽቅብ፣ ቁልቁል የሚለን እንቆቆ ቢናፍቀንስ! አሀ…ሀበሻ ሆኖ “ኮሶ ይዞኝ አያውቅም” ማለት “የለየለኝ የአርሴናል ደጋፊ ብሆንም ጨጓራዬ ተልጦ አያውቅም” እንደማለት ሊሆን ይችላላ! (እኔ የምለው…ቬንገር የሚሏቸው ሰውዬ ያስቋጠሩት ነገር አላቸው እንዴ! አይ…የሆኑ ወዳጆች “እሱ የተነሳ እለት ውሎና አዳር ቺቺንያ ይሆናል አይነት ነገር ሲሉ ስለሰማኋቸው ነው፡፡)
እናማ…በስጋ እጦትና በአምሮት ብዛት…አለ አይደል… “መቼ ይሆን እንደገና ዲክሎሮፊል ለመውሰድ የሚያበቃኝ!” የምንልበት ጊዜ እንዳይመጣ!
ሰውየው ዳኛ ፊት ይቀርባል፡፡ የተከሰሰውም የፈረሱን ስጋ የጥንቸል ነው ብሎ ሸማቾችን አታሏል በሚል ነው፡፡
ዳኛ፡- ምን አይነት ሰው ነህ! እንዴት ምንም የማይጠረጥረውን ህዝብ የፈረስ ስጋ እየሸጥክ ታታልላለህ?
ነጋዴ፡- ጌታዬ፣ ሙሉ ለሙሉ የፈረስ ስጋ አይደለም። የፈረስና የጥንቸል ቅልቅል ነው፡፡
ዳኛ፡-  እሺ፣ የአንዱን ፈረስ ስጋ ከስንት ጥንቸል ጋር ቀላቀልክ?
ነጋዴ፡- ጌታዬ እኩል ለእኩል…ሀምሳ ከመቶ፣ ሀምሳ ከመቶ ነው፡፡
ዳኛ፡-  እንደሱ ስትል ምን ማለት ነው?
ነጋዴ፡- ጌታዬ፣ የአንድ ፈረስ ስጋ ከአንድ ጥንቸል ስጋ ጋር ነው የቀላቀልኩት፡፡
ሳያዳሉ ‘ካመጣጠኑ’ አይቀር እንዲህ ነው፡፡
በድጋሚ፣ እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው አደረሳችሁ፡፡
መልካም የፍስክ ሰሞን ይሁንላችሁ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2882 times