Saturday, 07 April 2018 00:00

የጠ/ሚሩ ንግግር ተስፋዬን አለምልሞልኛል”

Written by  ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
Rate this item
(1 Vote)

  ጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ሲለቁ፣ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ሌሎችን አስተባብረው፣ ሀገራችንን ወደ ተሻለ መንገድ ሊመሯት የሚችሉት የኦህዴድ ወጣት አመራሮች ይመስሉኛል›› ብዬ አጭር ጽሁፍ ጻፍኩ፣ የተስማሙ ብዙ ቢሆኑም፣ በውስጥ መስመር ሳይቀር ስድብ አስተናግጄያለሁ፡፡ ዶ/ር አብይ ሲመረጡ ደግሞ፤ ‹‹እንኳን ደስ አለን፡፡ ቢያንስ በሁለት ምክንያት ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ዶ/ር አብይ በመመረጣቸውና በተመረጡበት መንገድ ደስ ሊለን ይገባል›› ብዬ በመጻፌም እንዲሁ፤ (አንድ ሰው፤ ‹‹ጥሩ ዘመቻ ይዛችኋል . . . አንተ ቅጥረኛ ካድሬ . . .›› በማለት አቅሉን ስቶ ሰድቦኛል፡፡ የሰደቡኝም ያመሰገኑኝም ሀገራቸውን ስለሚወዱ ነው (በነገራችን ላይ ይህንን ከአዲሱ ጠ/ሚ ንግግር ነው የተማርኩት)፡፡
አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ በረሀ ውስጥ አትክልት ለማልማት ወንዝ በመስኖ ለመጥለፍ ከስንት ምዕራፍ ቦይ እየቆፈሩ፣ ምንጭ ሲፈልቅላቸው፣ ዝናብ ሲጥልላቸው፣ ‹‹ለምን?›› ብለው ከፈጣሪ የሚጣሉ፡፡ አብዛኞቹ የዶ/ር አብይን መመረጥ የሚቃወሙት፣ ‹‹ለምን ከኢህአዴግ ውስጥ ወጣ? ለምን ከተቃዋሚ አልመጣም?›› ብለው ነው፡፡ ተቃዋሚ የሚሉት እኮ፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲ ወጣቱ በየቦታው እየሞተ እያለ፣ የኦህዴድና የብአዴን አመራሮች ከህዝብ ጎን ሆነው፣ የገዛ ድርጅታቸውን ወጥረው በያዙበት ወቅት፣ በአማረ አዳራሽ ከአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጋር፣ ስለ ምርጫና የምርጫ ቦርድ የሚነታረኩትን ነው፤ ተደርጎ ለማያውቅ ምርጫ፡፡ (በነገራችን ላይ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ‹‹የተመረጠው ኢህአዴግ ነው፤ መሪው ኢህአዴግ ነው›› ያሉትን በቲቪ ቀርበው ያስተካክሉ፡፡ ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ፣ በቤተመንግስት፣ ‹‹እኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ መሪ ነኝ›› ብለዋል)፡፡
የጠ/ሚሩ ንግግር ተስፋዬን የበለጠ አለምልሞልኛል፡፡ ለምን ቢባል ...
ለመሪ የሚመጥን ንግግር - ከራስ ጀብድ የፈቀቀ፣ ከስድብና ከማናለብኝነት የራቀ ንግግር ሰማን፡፡ ከአድዋ እስከ ባድሜ ለነጻነትና ለሀገር የተከፈለ መስዋእትነታችን እንጂ፣ የእርስ በርስ መገዳደላችን እንደ ጀብድ አልተዘመረም፤ እና ይህ ለውጥ አይደለም?  ማነው፣‹‹ሮጠው ስላልጠገቡ ህጻናት ሞት፣ ስለ ቤተሰቦቻቸው ሀዘን ይቅርታ ጠይቆ የሚያውቀው? እና ይህ ለውጥ አይደለም? አሸናፊነቱን ከየተዋደቀበት የጦር ሜዳ እየጠቀሰ እንጂ፣ ሰላማዊ ትግልን (ጋንዲን) እየጠቀሰ የተናገረ መሪ ማነው? ይህስ ለውጥ አይደለም? . . . . ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ብርሀን ለምንፈልግ፣ ጸሀይ እየወጣች ይመስለኛል፡፡ የእኛ ድርሻ ሙሉ ሆና እንድታበራ፣ ወደነበረችበት እንዳይመልሳት ዳመናውን መጥረግ ነው፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ዜጎቿን ይባርክ! (እውቀት ያለው መሪ ሲገኝ ብዙ መማር ይቻላል)

Read 1045 times