Saturday, 07 April 2018 00:00

ዶ/ር ወረታው በዛብህ ስለ አዲሱ ሚኒስትር

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 “ዶ/ር አብይ የፖለቲካ ኢንተርፕረነር ናቸው”
                        
     ሁላችንም ካለንበት አጣብቂኝ ውስጥ መውጫ መንገድ አጥተን ተፋጠን ከርመናል፡፡ ስንነካከስ እንዳንጠፋፋ በሚያስፈራበት መልኩ ሁላችንም ግብግብ ስንገጥም እዚህ ደረስን። መንግስት በጉልበቱ ሲገፋበት፥ ሕዝብ በአመፁ ሲዘልቅበት፥ አማራጭ ኃይል በሁሉ አቀፍ ትግሉ ሲዘምትበት፥ አካሄዱ ሁሉ ሲያስፈራ፣ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን ያሰኝ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ በሁሉም አቅጣጫ ወደ አምላኩ ከመጮህ አልተቆጠበም። በአራቱም አቅጣጫ አንድነቷንና ብልጽግናዋን በማይወዱ ኃይሎች የተከበበችው ሀገራችን፥ ከውስጥ ደግሞ በነውጥ ስትናጥ ተስፋዋ እየመነመነ ጫፍ ደርሶ ነበር። ምን አልባት ታዲያ የማታ ማታ ፈጣሪዋ ኢትዮጵያን ከምጥ ሊገላግላት፣ ውጥረቷን አርግቦ ሰላምን ሊሰጣት አስቦ ይሆን ዶ/ር አብይን የሰጣት?
አሁን ከከበቡን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሙሉ በሙሉ ለመውጣት ረዥም መንገድ መሄድ እንዳለብን እሙን ነው። ዶ/ር አብይ፤ ለኢትዮጵያ ዘብ በመቆምና እኛም ለእርሳቸው ዘብ በመቆም፣ ይህን የተስፋ ጭላንጭል ጠላት እንዳያጨናግፍብን፣ ሁላችንም የየበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይገባናል። አሁን እኛ ተመልካች ሆነን፥ ዶ/ር አብይ ደግሞ ከፊታቸው የተጋረጠውን  ችግርና ፈተና ይወጡት ይሆን በሚል ለመታዘብና ብያኔ ለመስጠት፣ በጥርጥር ዓይን ቆመን እሳቸውን የምንመለከትበት ወቅት ላይ አይደለንም። አሁን እሳቸውን የምናዋክብበት ጊዜም አይደለም፤ ይልቁንም እኛም ሆንን እሳቸው የመፍትሄው አካል ከመሆን እንዳንጎድል ተጠንቅቀን፣ ሃላፊነታችንን መወጣት ያለንበት ጊዜ ላይ ነን፡፡
በአንደኛ ደረጃ፥ ህዝብ ካንዣበበት አደጋ አምልጦ፣ በሰላምና በመረጋጋት እንዲኖር፣ ዶ/ር አብይ ራስዎን ከአጣብቂኝ መውጫ አድርገው ለሕዝብ የተሰጡ ይሆኑ ዘንድ ያገኙትን የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ ተጠቅመው፣ ለኢትዮጵያ ዘብ ይቆማሉ ብዬ አምናለሁ። ከዚህ በፊት በተለያዩ መድረኮች ያደርጉ የነበረውን ንግግርዎትንና ሰብዕናዎን፣ አምላክ ወደ ብርሃን አውጥቶ በሕዝቡ ልብ ውስጥ እርስዎን አስቀምጧል። ሕዝቡ ትልቅ ተስፋም እንዲኖረው አድርጓል። እርስዎ ታማኝነትዎን ለመንግስት ዕድሜ ቅጠላ ሳይሆን ሰሚ ላጣው ሕዝብ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው። ለጠ/ሚ ስልጣንም ያበቃዎት በቀዳሚነት የሕዝብ ትግል ነውና። በመንግስት ዘንድ የሕዝብ ጆሮና ዓይን በመሆን፣ የሕዝብ ጠበቃ እንዲሆኑና የሚመሩትን መንግስት ወደ አዲሲቷ ኢትዮጵያ አዋላጅነት የማሻገር ታሪካዊ ተልዕኮዎን ከመወጣት ለአንዲትም ደቂቃ ቸል ማለት የለብዎትም።
ይህንንም ሃላፊነትዎን ሲወጡ  ፋታ ባገኘሁ ይሉ ይሆናል። ግን ፋታ እንዲያገኙ ማድረግ የሚችሉት እርስዎ  ራስዎ ነዎት፡፡ በማስተዋል በመመላለስ ሁለት ነገሮችን ቢያደርጉ ፋታ የሚያገኙ ይመስለኛል። በመጀመሪያ የሕዝብን ጥያቄ በየደረጃው ለመመለስ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግን በቁርጠኝነት ማከናወን ሲችሉ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የምንሄድበትን አዲስ አቅጣጫና ራዕይ እየነገሩንና መዳረሻችንን እየጠቆሙን፥ በአንድ ልብ፣ እንደ አንድ ቤተሰብ የምንጓዝበትን አካሄድ ለማስጨበጥ የሚተጉ ሲሆኑ ነው።
አባቶች ደማቸውን አፍሰው በመሞት ኢትዮጵያን አቆይተው፣ ዛሬ ለዚህች እናት ኢትዮጵያ ጠ/ሚ ለመሆን ታድለዋል። በተራዎ እርስዎ ራስዎ ለኢትዮጵያ በመኖር፣ ኢትዮጵያን ሁሉም በእኩልነት የሚኖርባትና የሚያርፍባት ሀገር እንድትሆን የበኩሉዎን ታሪካዊ ድርሻ መወጣት ይጠበቅብዎታል። ሁሉም መልካም ምኞቱንና በጎ ፍቃዱን እንደለገሰዎት በማወቅ፣ ለተሰጠዎት ለዚህ ታላቅ ፀጋ ታማኝ እንዲሆኑ ማስተዋል ይብዛልዎት። በሁሉ ነገር እንዲሳካልዎ የመላው ኢትዮጵያዊ ፀሎትና ሰላማዊ ትግል እንደማይለይዎት ጽኑ እምነቴ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ፥ ኢሕአዴግ ራሱን ለማትረፍ ከዶ/ር አብይ የበለጠ መውጫ አያገኝምና፣ ለአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዘብ በመቆም ህልውናውን በሀቅ ምርጫ ለማስቀጠል፣ ራሱን ካለው የጊዜው የሕዝብ ጥያቄ ጋር ማጣጣም ይኖርበታል።  የኢትዮጵያ ሕዝብ በቅንነት አገልጋይ ለሆነ ሁሉ የሃይማኖት፣ የጎሳና የፖለቲካ ፓርቲ አባልነቱ ማንነት ውሳኔውን ሳያዛባበት፣ በአስተሳሰቡ ምንነት ላይ ብቻ ተደግፎ፣ ፍቅሩን እንደሚለግስ፣ ዶ/ር አብይ በተመረጡ ጊዜ የታየው አገር አቀፍ ደስታ ያረጋግጣል። ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብን ቅንነትና ታላቅ ሰብዕና ያሳያል።
 እስካሁን መንግስት የሄደበት አካሄድ ስልጣንን በጉልበት እንጂ በእውነተኛ ምርጫ አላገኝም ብሎ ያመነ ይመስል ከዲሞክራሲ የተፋታ ነበር። ታዲያ ዛሬ በእነ ክቡር አቶ ለማና ክቡር አቶ ገዱ፤ ሕዝብን የማዳመጥና የማገልገል አስተሳሰብ ራሱን አጥምቆ ቢንቀሳቀስ፥ በእውነተኛ ምርጫ ለስልጣን የመታደል ዕድል ሊያገኝ እንደሚችል ጭላንጭል እየታየ ነው። የትኛውም በጦር የመጣ መንግስት፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ እንዲህ ያለ የመሸጋገሪያ ድልድይ ከራሱ አብራክ በወጣ ልጅ ዕድል ሲያገኝ አላየሁም፤ አልሰማሁምም። በጎም ሆነ ክፉ እያደረገ ለ27 ዓመታት እንደፈለገው ገዝቶ ሲያበቃ፥ እንደገና በዲሞክራሲ በመዳኘት በምርጫ ስልጣኑን ቢያጣ እንኳን እንደ ኢሕአዴግ ህልውናውን ከመጥፋት አድኖ ማስቀጠል የሚችልበትን ዕድል አግኝቷል። ታዲያ ለዚህ ምክንያት የሆኑት ዶ/ር አብይ፣ በሙሉ ስልጣን የመምራት ሃላፊነታቸውን ይወጡ ዘንድ የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላት በመረባረብ፣የውስጥ እንቅፋቶችን ሁሉ እያስወገዱ፣ ለሕዝብ አክብሮታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡   
በሦስተኛ ደረጃ፥ ተቃዋሚው ለኢትዮጵያ አማራጭ ሃይል ለመሆን፣ ዶ/ር አብይ ሁነኛ መውጫ ሊሆኑ ብቃት ያላቸው ይመስላሉና ለእሳቸው ዘብ በመቆም፣ ለሰላሙ ትግል ሃይሉን አጠናክሮና አቀናጅቶ መቅረብ ይኖርበታል። ተቃዋሚው እውነተኛ ምርጫ እንዲዳኘው የሚያስችል የዲሞክራሲ ምህዳር ቢኖርለት የአመፅ ናፍቆት የለውም። የዲሞክራሲው ምህዳር እንዲሰፋና እንዲንሰራፋ መድረኩ ክፍት ከሆነ፥ በውጭም ሆነ በውስጥ ያሉት ተቃዋሚዎች አማራጭ ሃይል ለመሆንም ሆነ ለመተባበር ዕድል ፈንታ ይሰጣቸዋል። ለዚህም ነው ተቃዋሚ ሃይሎች ዶ/ር አብይን ለዲሞክራሲ ጉዞ ከአጣብቂኝ መውጫ ይሆኑ ዘንድ ደጀን በመሆን፣ እውነት ራሷ ይህንን የዲሞክራሲ አካሄድ የሚቃወሙትን እንድትሞግትና እንድትረታ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መቀናጀት የሚያስፈልጋቸው።
ለማንኛውም የዛሬ ሁለት ዓመት የሚደረገውን አገራዊ ምርጫ ከቁጥር በማስገባት፣ ዶ/ር አብይ ለምርጫው ፍትሀዊነት ሁሉን እያሳተፉ፣ የለውጥ ዋዜማ ሽታ ማምጣት እስከቻሉ ድረስ ለሳቸው ፋታ መስጠት የግድ ይላል፡፡ አሁን ዶ/ር አብይን በተመለከተ በሁሉም አማራጭ ሃይሎች ዘንድ የሚታየው በጎ ፍቃድና የእምነት ተስፋ እጅግ የሚያበረታታቸው ይመስለኛል። ይህም መልሶ ለሕዝብ እንዲኖሩ ግፊት እያደረገ፣ የሕዝብ እውነተኛ አገልጋይ እንዲሆኑ ጉልበት ይሆናቸዋል።
ላለፉት 44 ዓመታት በወጀብ ስትናወጥ የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ደግሞ በአዲስ መንፈስ፣ መሪዋና ሕዝቡ በፍቅር እጅና ጓንት ሆነው፣ አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንድትወለድና ለመጀመሪያ ጊዜ እፎይ የምትልበት ዘመን እንዲመጣላት ሁላችንም እንሻለን፡፡ ይህ መለኮታዊ ዕድል ፈጽሞ ሊያመልጠንም አይገባም፡፡ ልባችን ለዚህ ውልደት ዘብ ለመቆም ይጨክን!!  
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ!!!
(ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻቸው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 1795 times