Saturday, 07 April 2018 00:00

የጠ/ሚኒስትሩ ዜማ ያረገዘው ተስፋ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

“ንግግር ይገድላል፤ ንግግር ያነሳል”
              
    የሺህ ዓመታት ታሪክ ልቃቂት ናት የምትባለው ሀገር፤ የዘመንዋ ልክ ቁልቁል ወርዶ መቶና ከዚያም በታች እንደሆነ፣ በአዲሱ የኢህአዴግ ስርዓት ስለተለፈፈ፣ የቀደሙ ሰነዶች አቧራ ለብሰው “ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት” በአሮጌ ሳጥን ተቆልፎበት ዓመታት በማስቆሩ፣ የብዙዎች ልብ በሀዘን ተሰብሮ፣ በትዝታ ቋጥሮ፣ ኖሯል፡፡
ይሁንና የቅርቡ ህዝባዊ ዐመፅ፣ ብዙ የተጠሉና አላግባብ የተወገዱ ሀገራዊ ጥያቄዎችንና የአንድነት ትእምርቶችን ከተጣሉበት ሸለቆ ወደ አደባባይ በማውጣት፣ ያልተለመዱና የተረሱ ነገሮችን ህያው አድርጓል፡፡
በተለይ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ፤ በሀገሪቱ ነውጥና ማዕበል መሀል እንደ ፈጣን አትሌት ተወርውረው በመውጣት “ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በህያው ቃላትና በታሪካዊ ኩነቶች በመዘከር፣ ትኩስና እሸት የሆነ ስሜት በህዝብ ውስጥ ፈጥረው፣ ይህንንም የሀገሪቱ አድማሳት በአራቱም አቅጣጫ አስተጋብተውታል። … ይህንን የኢትዮጵያዊነት ስሜትና ቁርኝት ከአማራ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር በመሆን ፀበሉን ለሁላችንም ረጭተዋል፡፡
የዚያ የለማና አጋሮቹ አብዮት መጨረሻና መድረሻ ቢሆንም በሀገሪቱ ታሪክ በአድናቆትና በፍቅር በሰከረ መንፈስ፣ ህዝብ የተቀበላቸውን አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር በክብርና በምርጫ ወደ ሥልጣን አምጥቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ካሪዝማ ያላቸው፣ ሞገሥ የጠገቡና ከፍ ያለ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ስለነበሩ፣ እንደ ያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ፣ ትንሹ የፍሬ ዛፍ የተባለላቸውና በብዙ የህይወት መንገድ ያለፉ ናቸው፡፡ እኒህ ጠቅላይ ሚኒስትር የኋላ ታሪካቸው በምስጋናና በአድናቆት የተሞላ፣ እማኝነት የተረፈው ሲሆን፣ በፓርላማ ተገኝተው ያደረጉት ንግግር ደግሞ ባልተለመደ ሁኔታ በህዝቡ ውስጥ ተስፋ የጫረ፣ በሀገሪቱ የደስታ እንባ ያራጨና ነገአችን ብሩህ ያደረገ ነበር፡፡ በርግጥም ንግግራቸው የተጠበቀውን ያህልና ከዚያም በላይ ነበረ፡፡
ንግግራቸው በናፍቆትና በጉጉት የተጠበቀው ከመሬት ተነስቶ አልነበረም፣ ሰውየው በቂ ችሎታታ ክህሎትና ዕውቀት (Competence) አላቸው በሚል ነው፡፡ በሞራልም ቢሆን እውነተኛ ታማኝ፣ ለህዝቡም ትኩረት ይሰጣሉ በሚል እምነት ነበረ፡፡
ስለዚህም Initial credibiluty የሚለውን ከንግግራቸው በፊት በህዝብ የመታመን ዕድል፣ አግኝተው ነበር፡፡ በንግግራቸው ሂደት ላይ (Derived credibility) እና ተናግረው ካበቁና ሃሳባቸውን ካጠናቀቁም በኋላ (Terminal credibility) የሚለውን ከተጠበቁ ወገኖች ካልተጠበቁ ወገኖች ሁሉ አግኝተዋል፡፡ ከላይ ከፕሮፌሰሮች ጀምሮ፣ ታች እስከ ተርታው ሰው ድረስ በአድናቆትና በአክብሮት የተሞላ ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ ምናልባትም ዳር ቆመው በጥርጣሬ ያዩዋቸው የነበሩ ሰዎችን እንኳን ወደ መርከባቸው አስገብተዋል፤ ማህበራዊ ሚዲያው ሣይቀር በፌሽታና ፈንጠዝያ ሰክሯል። አንገታቸውን የደፉ የሀገር ልጆች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ኢትዮጵያዊነት አልዐዛርን ሆነ!” ብለዋል፡፡ እውነትም ሀገር ከመቃብር የወጣች ያህል ከበሮ ተደልቋል፡፡  
በሠላሳ ስድስት ደቂቃ፣ ሠላሳ ዘጠኝ ጊዜ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ቃል መጠቀማቸው፣ ማለትም በአማካይ በየ55 ሰከንዱ “ኢትዮጵያ” በማለት ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር መግለጣቸው ሲታይ፣ የተጠቀሙበት ቁልፍ ቃላት (Key terms) በአግባቡ እንደመረጡ ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ የአድማጫቸውን የልብ ትርታና የውስጥ ፍላጎት የማወቅ ውጤት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ንግግራቸውን ያቀረቡበት መንገድም የተዘጋጀ ጽሑፍ እያነበቡ፣ (Reading manuscript) በሚቀርብበት መንገድ ነበር፡፡ የዚህ ዓይነቱ መንገድ ደግሞ እንደርሳቸው የሀገር መሪ ለሆነ ሰው ተመራጩና ትክክለኛው አቀራረብ ነው፡፡ ምናልባት የዚህ ዓይነቱ አቀራረብ፣ ወደ ፕሬስ፣ ወደ ሥራ ባልደረቦችና ምናልባትም አቃቂረኛ ባላንጦች ጋ ሊደርስ ስለሚችል በጥንቃቄ፣ የተከረከመና የተለቀመ ቢሆን የተሻለ መሆኑ በዘርፉ ሊቃውንት።
በተጨማሪም የተለያዩ ብሔሮችንና ሃይማኖቶችንና ባህሎችን በእኩል አይን በማየት ከዚያም ዘልቀው የሀገሪቱን ህዝቦች በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ቀለምና ትዕምርት ስር አካትተው ተናግረዋል። በተለይ Imagery (ምሰላ) የሚፈጥር ገለፃና ቋንቋን በመጠቀም የሀገሪቱን የኋላ ታሪክ በመጥቀስ ያቀረቡት ንግግር ሁላችንንም አስደምሟል፣ ሰውየው ከፖለቲከኝነት ባለፈ ጥበባዊ ቀለም ውስጣቸው እንዳለ የሚመሰክሩ ቃላትና ሀረጋት እንዲሁም ዐረፍተ ነገሮች ሾልከው ወጥተዋል፡፡
“አማራው በካራማራ ለሀገሩ ሉዐላዊነት ተሰውቶ፣ የካራማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል፡፡ ትግራዋይ በመተማ ከሀገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል፡፡ ኦሮሞው በአድዋ ተራሮች ላይ ስለሀገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዐላዊነት ለማስጠበቅ ከአድዋ አፈር ጋር ተዋህዷል፡፡ … ኢትዮጵያዊያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያን እንሆናለን፡፡”
ይህ አባባል ብዙዎችን መስጦ፣ ተጠቃሽ ጥቅሶች እየተወሰዱ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያሸበርቁ ሰንብተዋል፡፡
ስለ ሀሳብ ልዩነትም የተናገሩዋቸው ነገሮች አሳማኝና ልብ ነኪ ነበሩ፡፡
“በአንድ ሀገር ውስጥ የሀሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የሀሳብ ልዩነት ርግማን አይደለም፡፡ ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ በመደማመጥ በመርህ ላይ ተመስርተን መግባባት ስንችል የሀሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል፡፡ በሀሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሄ ይገኛል፡፡ በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ። ስንደመር እንጠነክራለን፡፡ አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርም፡፡ አገር ይገነባል፡፡ የኔ ሀሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን እንኳን አገርን ሊያቆም ቤተሰብን ያፈርሳል፡፡”
ከላይ የጠቀስኳቸው ሀሳች ለአንድ ሀገር ህልውና ጥንካሬ ወሳኞች ናቸው፡፡ የሀሳብ ልዩነት ከሌለ ለውጥ የለም፡፡ በየትኛውም ሀገር ለውጥ እንዲኖር የተለያዩ ሃሳቦች መንሸራሸር ይኖርባቸዋል፡፡ በአሜሪካ ምስረታ ወቅት ከመስራች አባቶች አንዱ የሆነው ቶማስ ጀፈርሰን በጊዜው “ፌደራሊስት” ከሚባለው ቡድን በሀሳብ ልዩነት አፈንግጦ ባይወጣና ምናልባት የአሜሪካ አንድነት እንደ ዛሬው ባልሆነ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ልዩነቱን ተቀብለው ስላስተናገዱት በሁለቱም ወገን የተሻለ ሀሳብ በማምጣት ተሟግተው ታላቅ ሀገር መሰረቱ፡፡ በርግጥም የሀሳብ ልዩነትን መጥላት የኋላቀርነትና ያለማወቅ ምልክቶች ናቸው ኮ! … ከዚህ ሳንላቀቅ! አሉ - ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ስለ ዲሞክራሲ አንስተው ለዴሞክራሲ አዲስ አይደለንም፤ በዓለም ሀገራት ዲሞክራሲ በቅጡ በማይታወቅበት ዘመን በገዳ ሥርዐት በመተዳደር ለዓለም ተምሳሌት መሆናችንን በማውሳት፣ የወደቀ ልባችንን ከፍ አደረጉት። አንጋፋው ገጣሚ ደበበ ሰይፉ እንደሚለው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደኋላ እየሄዱ አንድነታችንንና ክብራችንን አስታውሱን፡፡ ወደፊት ለማለት ወደ ኋላ አንገት ማዞር ይላል ይህ ነው፡፡
“እንደግ እንደዛፍ”
ጥቁር አፈር አቅፎን
ጥቁር ብርሃን ውጦን
ሥራ ሥር አንቁለን
አዝምተን እንደ ሀረግ፤
ውስጡን ዕመቃቱን
ጉራንጉን ጠገግ፣
ጭረንና አሽተን
እንደፋኖ ሶለግ፤
እንንቀስ አልሚውን
እንልቀም መልካሙን
እንደልባም ሰው ወግ፡፡
ከፍ ብለን እንድናኝ
አየሩን ልንመላ
ወደፊት ለመሮጥ እንሂድ ወደኋላ
እንደግ እንደዛፍ
ዋርካ እንሁን ሾላ፡፡
መንግሥትን በሚመለከት፡- ዴሞክራሲን ከዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴና ከመንግሥት መሪነት፣ ደጋፊነትና ሆደ ሰፊነት ውጭ ማዳበር አንችልም፡፡ በመሆኑም መንግስት የዜጎቹ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል በጽናት ይሰራል፡፡ … መንግሥት ህግን ማክበር አለበት፣ ማስከበርም ግዴታው ነው፣ ታጋሽነትም ኃላፊነት ነው። የመንግሥት ታጋሽነት ሲጓደልም ዴሞክራሲ ይጎዳል … ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ውስጥ እንደተገለፀው፤ መንግሥት የህዝብ አገልጋይ እንጂ ጌታ አይደለም፡፡ ህዝብን ማዳመጥ፣ ህዝብን ማገልገል የዚህ ነፀብራቅ ነው። ይህ የስነ አመራር ፍልስፍና (Servant leadership) መሪ ለራሱ ጥቅም የሚሮጥ ሳይሆን ለሚመራው ህዝብ ጥቅምና የተሳካ ህይወት በራዕዩ የሚሄድ ማለት ነው፡፡ የህዝብ አለቃ (boss) መሆንና የህዝብ መሪ (leader) መሆን ይለያያል፡፡
ከንግግራቸው ከቀደመ የሥራ ልምዳቸው ካገኘናቸው መረጃዎች በመነሳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትራንስፎርሜሽናል መሪ ባህርያት ይታይባቸዋል ልንል እንችላለን፡፡ አሳታፊነት፣ ፈጠራ፣ ልበ ሙሉነት፣ ባኑበት ነገር መቆም ወዘተ … በዚህም የተነሳ “The transformatuonal leadership style have an overlap with the servant leader” አገልጋይ መሪነትም ከዚሁ ጋር አንድ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡
የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ሌላው ሀሣብ፤ በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት ጥሪ ነበር፡፡ በተለይ፡፡
“እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለስራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክሟት ይዞራል፡፡ ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊነት ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባለውም ለዚህ ነው። ሁላችሁም በታታሪነታችሁ፣ በልቀታችሁ የትም በሚከተላችሁ የሀገራችሁ የጨዋነት ባህሪ- የኢትዮጵያና የእሴቶቿ እንደራሴዎች ናችሁ።” በሚል አክብሮት የተሞላበት ንግግር ብዙዎችን አስደምመዋል፡፡
ለተቃዋሚ ፓርቲዎች “የተለየ ሀሣብ ያላችሁ ወንድሞቻችን እንጂ ጠላቶች አይደላችሁም ብለዋል። “ከኢሕአዴግ ውጭ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነፅር እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሀሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብሰብ ነው” በማለት መጪውን ጊዜ ብሩክ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር ዐብይ አህመድ በአጠቃላይ ንግግራቸው ውስጥ የሚጠቀሟቸው ቃላት አዎንታዊና ቀና መልዕክት ያዘሉ እንጂ አሉታዊ አይደሉም፡፡ በተለይ በአሁኑ መንግሥትም ሆነ ዘመን በገዥው ፓርቲ የተለመዱት ፀረ-ሠላም፣ ፀረ-ልማት፣ አሸባሪ፣ ተላላኪ..ወዘተ የሚሉትና መሰል ቃላት በጥቅም ላይ አላዋሉም፡፡ ይልቁንስ ፍቅር፣ አንድነት፣ ይቅርታ የሚሉት ባብዛኛው ሚዛን ደፍተዋል፡፡
በሚገርምና ባልተጠበቀ ሁኔታ ባለፉት የህዝብ ተቃውሞዎችና አመፆች ህይወታቸውን ስላጡ ዜጎች፣ በተለይም ወጣቶች በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ፣ የጥሉን ግድግዳ አፍርሰውታል። ብዙ ጊዜ እንደተለመደው በህዝብ ላይ ዛቻና ማሥፈራሪያም- ከአንደበታቸው አልተሰማም፡፡ “ጠቢቡ ሰለሞን ሕይወትና ሞት የአንደበት ፍሬዎች እንደሆኑ ይናገራል ንግግር ይገድላል፤ ንግግር ያነሳል፡፡
ምናልባትም ንግግራቸው ሲጨመቅ “የእሳት ራት ነህ ተብሎ ለተፈረደበትና ሁሌ የእሳት ቀለብ ለሆነው ህዝብ፤ ‹አይ አድራሻህ እሳት አይደለም፤ ሀገርህ ላንተ እሣት ሳትሆን አበባ ትሆናላች፤ አንተም ራስህን ቢራቢሮ አድርግና በሠላም አበቦች ላይ ብረር፡፡” የሚል ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፡፡ ሙሉ ንግግራቸው እጅግ ሰላማዊና የሁሉን ቀልብ የሚስብ ሲሆን፤ ዜማው ማራኪና ልብ ሠራቂ ነበር፡፡ ተስፋም ያረገዘ ነው፡፡
“ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!” ያልተለመደ መዝጊያ!

Read 1027 times