Saturday, 14 April 2018 16:08

ምስክርነት … ከእናት…››

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 በወሊድ ጊዜ የመድማት ሁኔታ ሲያጋጥም የህክምና እርዳታ ካልተደረገ በህይወት መቆየት የሚቻለው ለሁለት ሰአታት ብቻ ነው፡፡  
‹‹የመጀመሪያ ልጄን ነው አሁን የወለድኩት፡፡ ክትትሉን ስጀምር ግን የኤች አይቪ ቫይረስ በደምሽ ውስጥ አለ ስባል በመጀመሪያ በጣም ነበር የደነገጥኩት። አዝኛለሁም። በዚህ ላይ እርጉዝ ነበርኩ፡፡ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ ስጨነቅ ከቆየሁ በሁዋላ ሐኪሞቹ ባለቤትሽን ጥሪው ብለው ወረቀት ሰጡኝ፡፡ እሱም ያረገዝሽው አንቺ ነሽ እንጂ እኔ አይደለሁም፡፡ ለምን እሄዳለሁ ብሎ  በጣም ተቆጣ፡፡ ከብዙ ማግባባት በሁዋላ ሲሄድ እሱ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ ተነገረው፡፡ እኔ ይህን ስሰማ በጣም ተደሰትኩኝ። እሱ ግን በተገላቢጦሽ በጣም አዘነ፡፡ ሐኪሞቹ ግን ሁለታችንንም በጣም አረጋግተው እንድንግባባ አደረጉን፡፡ እንዴት ኑሮአችንንም መቀጠል እንዳለብን አስረዱን፡፡ አሁን በዚያ መመሪያ መሰረት ልጃችንም የእርግዝና ጊዜውን ጨርሶ ይሄው ተወልዶአል፡፡ በአሰላ ሆስፒታል ያሉ ሐኪሞችን እጅግ በጣም እናመሰግናለን፡፡ ሕይወታችንን ካለምንም ጭንቀት እንድንቀጥል ረድተውናል፡፡››
በአሰላ ሆስፒታል ወላዶች ክፍል ያገኘናት ወላድ፡፡  
በአሰላ ሪፈራል ሆስፒታል ያገኘናት ታካሚ ይህች ብቻ አይደለችም፡፡ በሆስፒታሉ ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ሌሎችም ታካሚ እናቶች በሆስፒታሉ ለሚሰሩ አዋላጅ ነርሶች ለሚሰጡት ክብር፤ ፍቅርና ከበሬታ ያለው ሙያዊ አገልግሎት ምስክርነት በመስጠት በእጅጉ አመስግነዋል፡፡
የማዋለጃ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሲ/ር ማሽላ አዲሴ በአዋላጅ ነርስነት ለ18 አመታት ሰርተዋል፡፡ እሳቸው እንደገለጹት ሙያቸውን በጣም ያከብሩታል፡፡ይወዱታልም፡፡ እናቶችን በሰላም ማዋለድ ማለት ሕይወት እንድትቀጥል ማስቻል ማለት ነው፡፡ አንዲት እናት በወሊድ ወቅት ተጎዳች ማለት ደግሞ በተቃራኒው ሕይወት እንዲቋረጥ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በላይ የሚያስደስትም ሆነ የሚያሳዝን አጋጣሚ የለም እንደ አዋላጅ ነርስ ማሽላ አባባል፡፡
የአሰላ ሆስፒታል በአርሲ ዞን ሪፈራል ሆስፒታል ነው፡፡ ስለዚህም እናቶች ከዲስትሪክት ሆስፒታል ፣ከጤና ጣቢያዎች በሪፈራል ለህክምና ይመጣሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአርሲ ዞን ዙሪያ ከከተሞችም ይሁን ገጠሮች አካባቢ በቀጥታ አሰላ ሆስፒታል ብለው የሚመጡ እናቶችም በርካታ ናቸው፡፡ አንዲት እናት የሆስፒታሉን አገልግሎት ፈቅዳ ከመጣች ተገቢውን አገልግሎት ታገኛለች፡፡
ከየጤና ተቋማቱ በሪፈር የሚመጡ ታካሚዎች ጉዳያቸው ይለያያል፡፡ ከሆስፒታሎች የሚመ ጡት እናቶች የኦፕራሲዮን አገልግሎት የማይሰጥባቸው አጋጣሚዎች ሲኖሩ… ለምሳሌም መብራት ሳይኖር… የጄኔሬተር ብልሽት ሲያጋጥም በአፋጣኝ ወደ አሰላ ሆስፒታል ይመጣሉ። ዲስትሪክት ሆስፒታሎች የደም አቅርቦት ከሌላቸው በተለይም ከወሊድ በሁዋላ የደም መፍሰስ ሲያጋጥም እናቶችን በአስቸኩዋይ ወደ አሰላ ሆስፒታል ይልካሉ። ጤና ጣቢያ ዎች ደግሞ አንዲት እናት የምጥ መራዘም ሲገጥማት ወይንም ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የደም ግፊት (ፕሪክላምፕስያ ኢክላምፕሲያ) ሲያጋጥም ወደሆስፒታሉ ይልኩዋታል፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ ብዙዎች አሰላ ሪፈራል ሆስፒታል ነው ከሚል ማንም ሪፈር ሳይላቸው ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ፡፡ የማዋለጃ ክፍሉ የኦፕራሲዮን ክፍሉን ጨምሮ ያለው 37/ ሰላሳ ሰባት አልጋ ብቻ ነው። ስለዚህም ሪፈር ሳይባሉ ወደሆስፒታሉ የሚመጡት ማለትም ጤነኛ የሆኑ ትና በጤና ጣቢያ መውለድ የሚችሉት እናቶች የጤና ቸግር ገጥሞአቸው ለሚመጡት እናቶች የአልጋ መጣበብ እንዲኖር ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህም ታካሚዎችን አንዱን ካንዱ ጋር እያስተያየን እያሸጋ ሽገን እንዲሁም አልጋ ከሌሎች ክፍሎች በመዋስ ጭምር ወላዶችን በኮሪደር ላይ ሳይቀር  በማስተኛት አገልግሎትን እንሰጣለን፡፡
የአሰላ ሪፈራል ሆስፒታል በአንድ ወር እስከ 550/አምስት መቶ ሀምሳ ወላዶችን ያዋልዳል፡፡ ወደሆስፒታሉ ከሚመጡት ወላዶች ውስጥ አብዛኞቹ በሰላም ተገላግለው ወደቤተሰባቸው የሚቀላቀሉ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ለምሳሌም በጤና ጣቢያ ቆይተው የተለያዩ የጤና ችግሮች ገጥመዋቸው ለሞት ሊዳረጉ የደረሱ እናቶች ሲላኩ እነሱን ለማትረፍ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ በ2007 እና 2008 ዓ.ም በሆስፒታሉ ያጋጠመ የእናቶች ሞት በርከት ያለ የነበረ ሲሆን በ2009/ዓም ግን 6480/እና ቶች የወለዱ ሲሆን በአንድ አመት ውስጥ 7/ሰባት እናቶች ሞተዋል፡፡ ከእነዚህም አብዛኞቾ በሪፈራል መጥተው ገና ከሆስፒታሉ ግቢ ሲደርሱ ወይንም መንገድ ላይ ሞተው የደረሱ ናቸው። እነዚህ እናቶች ለሞት ምክንያት የሆናቸውም በወሊድ ጊዜ የደም መፍሰስ፤ የደም ግፊት፤ የደም መርጋት ናቸው፡፡ አንዲት እናት ስትሞት ሆስፒታሉ የማጣራት ስራ ይሰራል፡፡ ለምን ሞተች፤ የትጋነው ችግሩ የተፈጠረው የሚለውን ሪፈር ካደረጉት ጤና ጣቢያዎችና እናትየው ከመጣ ችበት መንደር መረጃ በመሰብሰብ ስህተቱ እንዳይደገም ለማድረግ ጥረት ይደረጋል፡፡ በእርግጥ በአብዛኛው ከቤታቸው ሳይወጡ የተፈጠረ መዘግየት ሲሆን ሌላው ደግሞ ከደረሱበት ሆስፒታል ወይንም ጤና ተቋም በፍጥነት ሪፈር አለመደረግ፤ በበአምቡላንስ ተጉዋ ጉዘው ከሆስፒታል እስኪደርሱ በሚኖረው መዘግየት እንደህመሙ ሁኔታ እናቶች ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ በወሊድ ጊዜ የመድማት ሁኔታሲያጋጥም በህይወት መቆየት የሚቻለው ለሁለት ሰአታት ብቻ ነው፡፡ የደም ግፊትም እርዳታ በፍጥነት ካላገኘ እንደዚሁ በትንሽ ጊዜ ሊገድል ይችላል፡፡
ሲስተር ማሽላ እንዳሉት የእናቶችን ሕይወት በማትረፍ በኩል ሁልጊዜም ደግመን ደግመን የምንነ ጋገረውና ነገር ግን ዛሬም የሚያጋጥመው ችግር መዘግየት ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ህብረተሰቡ ሊረዳው የሚገባው ነገር አንዲት እርጉዝ ሴት የመውለጃ ጊዜዋ ሲቃረብ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ነው፡፡ መጉዋጉዋዣው፤ ገንዘቡ፤ ወደጤና ተቋሙ የማድረስ ኃላፊነት፤ የመሳሰሉትን ሁሉ ቀድሞ በማሰብ ምጥ በሚጀምርበት ጊዜ በፍጥነት በአቅራቢያ ወደሚገኘው ጤና ተቋም ማድረስ ተገቢ ይሆናል፡፡ እናቶች በምጥ በሚያዙበት ጊዜም ይሁን በክትትል ወቅት በቀረቡበት ጤና ተቋም ሊያገኙት ከሚችሉት እርዳታ በላይ የሆነ ችግር ሲገጥማቸው በፍጥነት ወደሚቀጥለው ደረጃ ማስተላለፍ ሙያዊ ግዴታ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን እናትየው ከሞት አፋፍ ስትደርስ ሪፈር ብትደረግም ሊያጋጥም ከሚችለው አደጋ ለማዳን ከማይቻልበት ደረጃ ሊያደርስ እንደሚችል መገመት ይገባል፡፡ በእርግጥ ይህ ሁኔታ በመሻሻል ላይ መሆኑ ባይካድም አሁንም ይህቺ እናት አትተርፍም እየተባሉ እየመጡ በብዙ መስዋእ ትነትና ትግል የተረፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም በ2010 ዓ/ም የእናቶች ሞት እስከአሁን አላጋጠመንም፡፡
‹‹…እኔ ጫልቱ እባላለሁ፡፡ የምኖረውም በዚሁ በአሰላ ከተማ ነው፡፡ አሁን እርግዝናዬ ዘጠኝ ወር ሆኖታል፡፡ ነገር ግን በሆስፒታሉ አልጋ ይዤ ከተኛሁ ሁለት ወር ሆኖኛል። ወደሆስፒታል መጀመሪያ የመጣሁት የደም መፍሰስ አጋጥሞኝ ነው፡፡ እኔ ባለሙያ ዎቹን በጣም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ምክንያቱም ሁልግዜ ቀንና ማታ ወይንም የበአል ቀን ሳይባል በጠራናቸው ወይንም በፈለግናቸው ጊዜ ካጠገባችን ናቸው፡፡ እናቶች እንደዚህ ያለ እንክብካቤ የሚየገኙ ከሆነ አይሞቱም ማለት ነው፡፡››
የመውለጃዋ ቀን እስኪደርስ በማዋለጃው ተኝታ የምትጠባበቅ እናት ምስክርነት…
ሲ/ር ማሽላ እንዳሉት ከላይ ሃሳብ የሰጠችው እናት በሆስፒታል የተኛችው እንግዴ ልጅዋ ከልጅዋ ስለቀደመና የደም መፍሰስ ስላጋጠማት ነው፡፡ ይህች ሴት ወደመጸዳጃ ለመሄድ ወይንም ለአንድ አፍታ ሰው ለማናገር ካልሆነ በስተቀር ከአልጋ እንድትወርድ አይፈቀድላትም፡፡ ሆስፒታሉ በእርግጥ የእናቶች ማቆያ የለውም፡፡ ነገር ግን እንደችግሩ ሁኔታ በቅርብ ሐኪም ሊከታተላቸው የሚገባ ሲሆን የመውለጃ ቀናቸው እስኪደርስ ድረስ በሆስፒታሉ እንዲቆዩ የሚደረግበት አሰራር ግን አለ፡፡ ለዚሁ አሰራር እንዲያመች ምክንያት ያላቸው እናቶች የሚተኙበት ተብሎ ሁለት ክፍል ተለይቶአል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ሁለት ወርም ሆነ ሶስት ወር ድረስ ተኝተው ሁኔታውን የሚከታተሉበት አሰራር አለ፡፡ ለወደፊቱ ግን ሆስፒታሉ አዲስ ፎቅ እያሰራ ስለሆነ ያንጊዜ እናቶች የሚቆዩበት የእናቶች መቆያ ቤት ይኖራል፡፡
ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ የሚሰጠው አገልግሎት ወደርና ገደብ የሌለው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ማናኛዋም እናት በቀጥታም ትምጣ ወይንም በሪፈር …ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ሙሉ የምክር አገልግሎትና አስፈላጊው ምርመራ ይካሄዳል፡፡ ለምስክርነት ቀድሞ የነበረውን ሁኔታ እና የአሁኑን ለማስተያየት ቢሞከር ልዩነቱ እጅግ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ከተወሰኑ አመታት ወዲህ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት የተነሳም በጣም የሚያስደስትና የሚያኮራ ሁኔታ አለ፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ላለ እናቶችና ልጆቹ ሲወለዱ ከሚደረገው የህክምና ጥንቃቄ በተጨማሪ ቫይረሱ በደማቸው ያለ እናቶች በሚያደርጉት የእርስ በእርስ ውይይት የተነሳ በአሰላ ሆስፒታል 99.9% የሚሆኑት ሕጻናት ከቫይረሱ ነጻ ሆነው ተወልደዋል ብለዋል ሲ/ር ማሽላ አዲሴ የአሰላ ሆስፒታል ማዋለጃ ክፍል ኃላፊ፡፡

Read 1791 times