Sunday, 01 April 2018 00:00

ኢህአዴግ በኛ ጉዳይ፣ ከኛ ተደብቆ ይወስናል!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(43 votes)

 • ለወጣቶች ከተመደበው 10 ቢ.ብር ውስጥ 4 ቢ.ብር ሥራ ላይ አልዋለም
   • ገዢው ፓርቲ፤ “ከአገርህ? ከሥልጣንህ?” ተብሎ ይጠየቅልን
   • ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የምናተርፈውን በግልጽ እንወቀው
         
   በርግጥ ዛሬ ያመጣው አመል አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ነፍሴ ሁሌም እንዲሁ ነው! ላለፉት 27 ዓመታት የኖረበት ዘዬው ነው፡፡ በቃ ድብቅ ፓርቲ ነው - ምስጢረኛ! ድብቅነት ባህሉ ነው፡፡ ስብሰባውና ግምገማው ሁሉ በዝግ በር ነው፡፡ በፓርቲው ጉዳይ ብቻ ቢሆን ግዴለም ነበር፡፡ ግን የኛን ጉዳይ ጭምር (የህዝቡን ማለቴ ነው!) የሚወስነው ለብቻው ነው - በምስጢር!! በህዝብ ጉዳይ፣ ከህዝብ ተደብቆ ለብቻው ይወስናል - ኢህአዴግ ነፍሴ! ለምሳሌ አዲሱን የኢህአዴግ ሊ/ቀመንበር የመረጠው ከኛ ተደብቆ ነው - በምስጢር! (የኛን ጠ/ሚኒስትር፣ከኛ ተደብቆ ይመርጥልናል!) ከመረጠ በኋላም ምስጢሩ ይቀጥላል፡፡ ቀድሞ የሚነገራቸው ጥቂት ሚዲያዎች አሉ። (“ልማታዊ ሚዲያዎች”?!) ኢህአዴግ ነፍሴ፤እነሱን ብቻ በምስጢር ጠርቶ መረጃውን ያቀብላቸዋል፡፡ (“የባለቤቱ ልጆች” በሉዋቸው!)
አንዳንዴ ኢህአዴግ፤ የድሮ ወላጆችን ይመስለኛል - “ባህላዊ ወላጆች”! (የወላጅ አንጀት ግን ኖሮት አያውቅም!) የድሮ ወላጆች፤ ለልጆቻቸው ባል ወይም ሚስት የሚያጩት፣ ልጆቻቸውን አማክረው ወይም አሳትፈው አይደለም፡፡ በራሳቸው ፍላጎትና ምርጫ ብቻ ነው። ኢህአዴግም በህዝብና በአገር ጉዳይ፣በራሱ ፍላጎትና ምርጫ ብቻ ይወስናል፡፡ (ደስ ያለውን!) በርግጥ በአሁን ዘመን ለልጆቹ የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ የሚደፍር ወላጅ የለም፡፡ የሚደፍር እንኳን ቢኖር የሚቀበለው አይኖርም። በዚያ ላይ መሳቂያ ነው የሚሆነው። ኢህአዴግ ነፍሴ ግን አሁንም ኮስተር ብሎ በህዝብ ጉዳይ፣በምስጢር እየመከረ መወሰኑን ቀጥሎበታል። (ያለኛ ፈቃድ!) አንዳንዴ ሳስበው… ሥልጣን የህዝብ መሆኑን ሁሉ የረሳው ይመስለኛል፡፡ (ሲቆይ የራሱ መስሎት ይሆናል!)
ለምሳሌ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክትን ሲያስብና ሲያቅድ አላማከረንም፡፡ (የባቡሩን ቀለም ብቻ ነው ምረጡ ያለን!) ቢያማክረንማ ኖሮ፣አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ በገቢው ዕዳውን መክፈል እንደማይችል እየታወቀ፣ በአቦ ሰጡኝ አይገባበትም ነበር። ባቡሩ አገልግሎት መስጠት በጀመረ ማግስት፣ ከባቡር ኮርፖሬሽን ሃላፊነታቸው የለቀቁት (በፈቃዳቸው ይሁን ተገደው አይታወቅም?!) ባለሥልጣን፤ የዚያን ሰሞን ለፓርላማ ሪፖርት አቅርበው ነበር፡፡ ባቡሩ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም የፕሮጀክቱ ወጪ የተሸፈነው ከቻይና በተገኘ ብድር መሆኑን ጠቁመው፤ ብድሩን መክፈል ባለመጀመራችን ግን ወለዱ ብቻ እየተቆለለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ብዙዎቹ የፓርላማ አባላት ታዲያ ባቡር መጀመሩን በራሱ እንደ ስኬት ስለቆጠሩት፣ አድናቆትና ምስጋና እንጂ ጥያቄ አላነሱም፡፡ አንድ የፓርላማ አባል ግን፤ “የባቡር ፕሮጀክቱ ሲታቀድ ብድሩን እንዴት ለመክፈል ነበር የታሰበው?” ሲሉ ጠየቁ።
የባቡር ኮርፖሬሽን ሃላፊውም ሲመልሱ፡- “መጀመሪያም ከባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በሚገኘው ገቢ ብድሩን መክፈል እንደማይችል እያወቅን ነው የገባንበት፤ ይሰራና በምንወጣው እንወጣዋለን ብለን ነው!” አሉና  አረፉት፡፡ (“ኢህአዴግና ተጠያቂነት” አይተዋወቁም!)
ዛሬ እንግዲህ እኒህ የምላችሁ ሃላፊ፣ በሥራቸው ላይ የሉም፡፡ ዕዳው ግን የአገር ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ኢህአዴግ ነፍሴ፤ ለኛ ጉዳይ፣ከኛ ተደብቆ ብቻውን እየወሰነ ጉድ ይሰራናል፡፡
 ልማታዊ መንግስታችን፤በአንድ ጊዜ 10 የስኳር ፋብሪካዎችን እገነባለሁ ብሎ ሲወስንም ህዝብን አላማከረም፡፡ (“ሚስትህ አረገዘች ወይ?” ቢሉት፤ “ማንን ወንድ ብላ?” አለ አሉ!!) እውነቱን ለመናገር እኛ ስለ ጉዳዩ መስማት የጀመርነው ወደ ኋላ ላይ ነው። ፕሮጀክቱ ሲደነቃቀፍ! ለማመን የሚያዳግት ገንዘብ ከባከነ በኋላ ማለት ነው፡፡ (77 ቢ. ብር ነው ያሉት?!) እስካሁን ግን የት አደረስከው የተባለ ባለሥልጣን የለም። (ሳንሰማ ተብሎ ይሆን እንዴ?)
እንግዲህ ለአብነት ያህል ይበቃል እንጂ ኢህአዴግ ነፍሴ፣ የህዝብን ጉዳይ፣ ከህዝብ ተደብቆ፣ ለብቻው እየወሰነ እንዲህ ጉድ ሰርቶናል፡፡ (ያውም ተጠያቂ በሌለበት!)
በነገራችን ላይ በአሁኑ ወቅት (እንዳምናው ሁሉ) “ድርብ ጾም” ላይ ነን - የሁዳዴ ጾም እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ!! (አንዱ ለነፍሳችን፣ ሌላው ለሥጋችን!) ጾም ላይ ብንሆንም ግን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም፡፡ (ሃቅ ሃቁን ማለቴ ነው!) እናላችሁ … በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ሆነን፣ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እናወራለን። እንደሚታወቀው ኢህአዴግ ነፍሴ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንም ለሁለተኛ ጊዜ ያወጀው… ከእኛ ጋር ተማክሮ አይደለም፡፡ (ከመቼ ወዲህ ነው የሚያማክረን?) እንደተለመደው በምስጢር መክሮ ነው የወሰነው፡፡ (ግን እኮ ጦቢያ የጋራ አገራችን ናት!) እናም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሳያማክረን ቢያውጅም፣ ለምን እንዳወጀው ግን ደጋግመን መጠየቅ እንችላለን፡፡ (በእኛና በአገር ላይ ነዋ የታወጀው!!)
አዋጁ ለሁለተኛ ጊዜ የታወጀው… በራሱ በኢህአዴግ የአመራር ስንፍና ቢሆንስ ብለን ልንጠረጥር እንችላለን። (በእርግጥ ለመደምደም ጥናት ይፈልጋል!) ቢያንስ ለሦስተኛ ጊዜ እንዳይታወጅ ለመከላከል ግን በቀጣዮቹ 6 ወራት ምን ለመሥራት እንደታቀደ በዝርዝር መጠየቅ አለብን- ኢህአዴግ ነፍሴን!!
በነገራችን ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሁለተኛ ጊዜ መታወጁን ተከትሎ፣ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ይመስላል። በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ጭምር፡፡ (ክፋቱ ግን የአገር ገጽታችንን አበላሽቶታል!) አዋጁ ባልተለመደ መልኩ አወዛጋቢም አነጋጋሪም ነበር፡፡ በፓርላማ ከፍተኛ የተቃውሞ ድምጽ (88) በማስመዝገብም ሪከርድ ሰብሯል ተብሏል። (በፓርላማ ታሪክ!) የሚያኮራ ባይሆንም አጼ ምኒልክ ጣልያንን ድል ባደረጉበት የአድዋ በዓል ዕለት ነው፤ አዋጁ በፓርላማ የጸደቀው፡፡ ንጉሱ ከ100 ምናምን ዓመት በፊት ጣልያንን ጦርነት በመግጠም ዓለምን ያስደመመ ታሪካዊ ድል አስመዝግበዋል! ዛሬ በ21ኛው ክ/ዘመን፣ ኢህአዴግ ነፍሴ፤ የራሱን ህዝብ አግባብቶ መምራት አቅቶት ፣የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ተገዷል፡፡ (የታሪክ ስላቅ!)
በሌላ በኩል በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ (በተለይም የኢህአዴግ የጸረ-ሽብር አጋር በሆነችው አሜሪካ!) ባልተለመደ ሁኔታ ከረር ያለ ተቃውሞ አስተናግዷል- አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ! ያን ሰሞን የገረመኝ ታዲያ የአንዳንድ ምሁራን (“የፖለቲካ ሳይንቲስት” አለን እንዴ?) ትችትና ነቀፋ አሜሪካ ላይ ማነጣጠሩ ነው። (“አህያውን ትቶ…” አሉ!) ምዕራባውያኑ ለምን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አክርረው ተቃወሙት - የሚል ነበር ትችቱ። “ሉአላዊነታችንን መድፈር ነው … እጅ ጥምዘዛ ነው---መንግስት ደክሟል ብለው ስላሰቡ ነው” ወዘተ-ወዘተ-- በሚል ሙዚቃ ታጅቦ ነበር የቀረበው። እንደኔ ግን ይበልጥ አሳስቦን ልንወያይበት የሚገባው ጉዳይ… ራሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሆን ነበረበት፡፡ (በየዓመቱ እየታወጀ እኮ ነው!) እናም መንግስታችን… ምን ዓይነት የአመራር ቀውስ ውስጥ ቢገባ ነው ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የተጣደፈው? (ወይስ ባህል አደረገው?) ቆይ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውጭ፣ ሌላ አማራጭ አልነበረም? እሺ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ነው የታወጀው ብለን እንቀበል። ግን ዓምና ለ10 ወራት ከተተገበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዴትና በምን ይለያል? ወዘተ… ብለን መሞገት… ማብራሪያ መጠየቅ … መከራከር---ይገባናል፡፡ በቀጥታ ከህይወታችን ጋር የተቆራኘ ነውና! (የእነ አሜሪካን “እጅ ጥምዘዛ” እንደርስበታለን!)  
እናም… ኢህአዴግ መራሹ ልማታዊ መንግስታችንን (አሁንም ልማታዊ ነው አይደል!?) መገዳደር  ያለብን ዋነኛው ጉዳይ ምን መሰላችሁ? የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ የተነሳሳው ወይም የወሰነው ምን አስቦ ነው? (በይፋ ከተናገረው ውጭ ማለቴ ነው!) ምን ስጋት አድሮበት ይሆን? (እኛ ያላወቅነው!) ምናልባት  የቀድሞው ጠ/ሚኒስትሩ ድንገት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ሥልጣኔን በፈቃዴ እለቃለሁ ስላሉ ይሆን? የሥልጣን ክፍተቱ እስኪሞላ ድረስ ረብሻ እንዳይነሳ ሰግቶስ ይሆን? (አሁን እኮ ጠ/ሚኒስትሩ ተመርጧል!) ወይስ ኮማንድ ፖስቱ በቀጥታ እንደነገረን፤ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን? … ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማስጠበቅ? … ዜጎችን ብሄር ተኮር ከሆኑ ጥቃቶች ለመከላከል? … ከቦታ ቦታ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብትን ለማስከበር? …ወዘተ… ከምር በእነዚህ ምክንያቶች ነው ከተባልንም እንቀበለዋለን። ዓላማችን ለምን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  ታወጀ የሚል ሙግት መግጠም ሳይሆን እንዳለፈው ጊዜ ውጤት አልባ ሆነን እንዳንቀር ከወዲሁ ለማስጠንቀቅ---ለማሳሰብ---ለማነቃቃት---ለማትጋት ነው!!  
እናም ኢህአዴግ ነፍሴ… በቀጣዮቹ 6 ወራት ምን ለማከናወን እንዳሰበ በዝርዝር እንዲነግረን እንሻለን። (“የግጭት ጠንሳሾችን” ከማሰር ውጭ!) ያሰበውንስ በ6 ወር ውስጥ ያሳካዋል ወይ? ወይስ እንደተለመደው 4 ወር ይጨምራል? ይሄን ሁሉ ያለ ምክንያት አላነሳንም። መንግሥት ባለፈው ዓመት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከ10 ወራት በኋላ ሲያነሳ፣ተመልሰን ወደ ቀውስ ውስጥ ነው የገባነው?  (ያልተሰራ ሥራ ነበር ማለት ነው!) የአሁኑስ? ከቀድሞው እንዴትና በምን ይለያል? ልብ በሉ! ከ6 ወራት በኋላ የተባለው ውጤት ባይገኝ፣ ኪሳራ ላይ የሚወድቀው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ብቻ አይደለም፡፡ ሁላችንም ነን፡፡ ሙሉ ጦቢያ! (ዓለም ዓይኑ እኛ ላይ ነው!) ከዚያም በላይ ግን የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንገባለን። ይሄ እንዳይሆን---አሁኑኑ ብንፋጠጥ ነው የሚሻለው። እናም ልማታዊ መንግስታችን… በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለማከናወን የሻተውን ወይም ያቀደውን በዝርዝር ይንገረን።  ከምሬ ነው--- ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የምናተርፈው ምን እንደሆነ በግልፅ ማወቅ አለብን። በዚህ አዋጅ ምክንያት የምናጣቸው (የምንነጠቃቸው!) መሰረታዊ ህገ-መንግሥታዊ መብቶች ብዙ ናቸው፡፡ አንድ ነገር ስናጣ ደግሞ የምናገኘው ነገር መኖር  አለበት። ለምሳሌ ሰላምና መረጋጋት… መልካም አስተዳደር…ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት…የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት---ዲሞክራሲ..የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት--የታሰሩ ፖለቲከኞች መፍታት---ወዘተ--  
እንግዲህ ለዚህች አገር ልማትም ሆነ ጥፋት ተጠያቂው ሌላ ማንም ሳይሆን የሥልጣን መሪውን የሚዘውረው ልማታዊ መንግሥታችን ነው - ኢህአዴግ ነፍሴ! በተቃዋሚዎች አባባል፤ ”ኳሷ ያለችው በኢህአዴግ እግር ሥር ነው!” የዚህችን አገር ችግር ሊፈታም ሆነ ሊያወሳስብ የሚችለው ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ ይህችን አገር ለማዳን ኢህአዴግ ሥልጣኑን አሳልፎ እስከ መስጠትም ቢሆን (አያድርግበትና!) መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ (መቼም ከ27 ዓመት በኋላ አይቆጭም!) ነገር ግን  በአንድ ልቡ ስለ ስልጣኑ እያሰበ፣ በሌላ ልቡ ደግሞ አገሬ የሚል ከሆነ ግን ከንቱ ልፋት ነው፤ አይሳካለትም፡፡ (በራሱ ቋንቋ “ማጣቀስ” አይቻልም!)
እናም ኢህአዴግ ነፍሴ፤ ”ከህዝብህ? ከሥልጣንህ?” ወይም “ከአገርህ? ከሥልጣንህ?” ተብሎ ግልፅ ምርጫ (ጥያቄ) ሊቀርብለት ይገባል፡፡ አገሩን ወይም ህዝቡን ከመረጠ … ከሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መምከርና መወያየት፣ ለችግሮች መፍትሄ ማፈላለግ፣ አፋኝ ህጎችን መሰረዝ--- ህገ መንግስቱን ማሻሻል፣ ወዘተ-- አቀበት አይሆንበትም፡፡ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን (የዲሞክራሲ ተቋማትን) በጋራ ማቋቋምም አይጨንቀውም፡፡ (ሥልጣኔን አጣለሁ ብሎ አይሰጋማ!) ልብ በሉ! በምንም በማንም የማትተካ አገርን ከጥፋት ለማዳን የማይከፈል መስዋዕትነት የለም!! (አገር ከሥልጣን በላይ ናት!)
እመኑኝ፤ ኢህአዴግ በአንድ ልቡ ስለ ስልጣኑ እያሰበና እየተብሰለሰለ ግን ኢትዮጵያን ሊያድናት አይችልም። አገር ከፓርቲም ከሥልጣንም በላይ መሆኗን አምኖ ከተቀበለ ብቻ ነው፤ ይህችን አገር ከተጋረጠባት አደጋ የሚታደጋት። ከእነ ሶሪያና ሊቢያ ዓይነት ክፉ ዕጣ ፈንታ የሚያድናት! እውነቴን ነው … ለኢህአዴግ መቅረብ ያለበት ግልፅ ጥያቄ፤ ”ከአገርህ? ከስልጣንህ?” የሚል ነው፡፡ ከፈለገ “አገሬ ሥልጣን ነው!” ይበለን፡፡ ምርጫው የሱ ነው። እኛ ግን መጠየቅ አለብን። ይሄ ጥያቄ የሚያስፈልገው የግድ ከሥልጣን እንዲለቅ አይደለም። ወሳኝ የለውጥ እርምጃዎችን ለመውሰድ ድፍረት እንዲያገኝ ብቻ ነው፡፡  
ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ልመልሳችሁ…፡፡ ኮማንድ ፖስቱ፤ “የግጭት ጠንሳሾችን” በቁጥጥር ስር ማዋል መጀመሩን በዚያ ሰሞን ነግሮን ነበር - እነማን እንደሆኑ ግን ገና በትክክል አልታወቀም፡፡ ከዚህ አንፃር የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ብዙዎችን ሊያሳስብ ይችላል፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ሳምንት፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  የታሰሩት እንዲፈቱ መንግስትን መጠየቁ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ (ግን የታሰሩት ስንት ደርሰው ይሆን?) በነገራችን ላይ በቅርቡ ከእስር የተፈቱት እነ እስክንድር ነጋ እንደገና መታሰራቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ተቃውመውታል፡፡ (የፈራነው የቀውስ አዙሪት!)
በሌላ በኩል የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን ለመመርመር የተቋቋመው ቦርድ እስካሁን ድምፁን አላሰማም። (አቅሙና ሥልጣኑ ምን ያህል ነው? ተዓማኒነቱስ?) በነገራችን ላይ መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፤ አገር በቀውስ ማዕበል በምትናወጥበትና በግጭት ሰዎች ህይወታቸውን እያጡ ባሉበት ወቅት፤ ክፉኛ በሥራ እንደሚጠመድ ብንገምት፣ ተሳስታችኋል የሚለን አይኖርም፡፡ በሰሞኑ  የጋዜጣው ዘገባ ግን በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን “ያለ አግባብ ከሥራ ተባረን፣ ተንገላተናል” ያሉ ካህናትን ጉዳይ ለመፍታት ሲባዝን እንደሰነበተ ተረድተናል፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎቹንና የሚመለከተውን አካል አነጋግሮ፣ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት መሞከሩ ኮሚሽኑን የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም። ችግሩ ምን መሰላችሁ? በአገር ደረጃ በስፋት የሚፈፀም (ሊፈፀም የሚችል) የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ይቀድማል ወይስ የአንድ የሃይማኖት ተቋም ሰራተኞች  ውዝግብና አቤቱታ? ለመሆኑ ኮሚሽኑ በሞያሌ በስህተት (በተሳሳተ መረጃ) ስለተገደሉት ዜጎች ጉዳይ ምን አጣራ? (በትኩሱ ማለቴ ነው!) ግድያውን ተከትሎ፣ በፍርሃትና በስጋት ድንበር ተሻግረው፣ ኬንያ ስለገቡት ወገኖቻችንስ? ወይስ ነገርዬውን ለኬንያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ትቶለታል? (ለኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ድጋፍ ሲያደርግ የነበረው የኬንያ ቀይ መስቀል ማህበር መሆኑን ልብ በሉ!) በስህተት ተገደሉ ስለተባሉት ዜጎች ጉዳይ አጣርቶ እውነታውን ለህዝብ ማሳወቅ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ሥራው ይመስለኛል፡፡ የተቋቋመበት! (ከተሳሳትኩ አንተዋወቅም ማለት ነው?)
በሌላ በኩል ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰብስ ምን ታስቧል? (ከተለመደው “ሃዘናችንን እንገልጻለን” ውጭ ማለቴ ነው!) ለሟች ቤተሰቦች ካሣ መክፈል ተገቢ አይደለምን? (በደልን አለመካስ፤ስህተትን አለማረም፤ ተበዳይን ከልብ ይቅርታ አለመጠየቅ፣ህዝብን አለማክበር---አሁን ላለንበት ምስቅልቅል ዳርጎናል!)
አንድ ስማቸውን የማላስታውሰው ፕሮፌሰር፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ለኢቢሲ በሰጡት አስተያየት፤ በሰብዓዊ መብት ረገድ ካለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በእጅጉ ተሽለን መገኘት አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡ (ያለፈው የከፋ ነበር ማለት ነው!) ኮሽ ባለ ቁጥር መሳሪያ ከመተኮስ መቆጠብ እንደሚያስፈልግም በድፍረት ተናግረዋል፡፡ (ሃቀኛ ምሁራን አያሳጣን!)
አንድ የቢዝነስ ባለሙያ ደግሞ በኢህአዴግ አመራሮች ስንፍና የተነሳ ችግሮች ይበልጥ ሊባባሱና ሊወሳሰቡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል - እንደ ማሳሰቢያም እንደ ማስጠንቀቂያም፡፡ አንድ ሌላ ምሁር በበኩላቸው፤ አብዛኞቹ የአገሪቱ ችግሮች ህገ መንግስቱን በማክበር ብቻ ሊፈቱ የሚችሉ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ህግ ከተከበረማ መጀመሪያውኑም ላይፈጠሩ ይችላሉ እኮ! (ይሄን ኢህአዴግም ራሱ አይክደውም!)
ሁለት ነጥቦችን ላንሳና የፖለቲካ ወጌን ልቋጭ፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞና አመፅ መቀስቀሱን ተከትሎ በ2009 ዓ.ም መንግስት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ በሚል የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መመደቡ አይዘነጋም። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳ ባለፈው ሰሞን ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት፤ ከ10 ቢ. ብር ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው (ለወጣቶች የሥራ ዕድል) 6.4 ቢ. ብር ብቻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለምን? እንዴት? መቼም የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር ተፈቶ አይደል (በምን ተዓምር?!) ፈንዱ በሚፈለገው መጠን ሥራ ላይ እየዋለ እንዳልሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ በአንዳንድ አካባቢዎች አመራሩ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች በመጠመዱ (ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር በላይ በምን ሊጠመድ ይችላል!?) አንዱ ሲሆን በሌላ በኩል የአስፈፃሚ አካላት ቅንጅት ማነስና ፈንዱን ለማስተዳደር ከወጣው መመርያ ውጭ ቅድመ ሁኔታዎችን በተለያዩ አካባቢዎች በመቅረባቸው ምክንያት እንደሆነ ጠቁመዋል።
የኢህአዴግ ነፍሴ ዋና ችግር፣ አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ አለማተኮር ይመስለኛል፡፡ ለህዝብ ተቃውሞና አመፅ  ዋነኛው  ምክንያት የወጣቶች ሥራ አጥነት መሆኑ በግልጽ እየታወቀ እንዴት ችላ ይባላል፡፡ የኢህአዴግ አመራሮች ጉዳዩ ከልብ ቢያስጨንቃቸው፣ የ10 ቢ. ብር ተዘዋዋሪ ፈንዱን ሙጥጥ አድርገው ጨርሰው፣ ሌላ 10 ቢ. ብር እንዲሰጣቸው መንግስትን ማፋጠጥ ነበረባቸው።  ግን ከ10 ቢ. ብር ውስጥ  4 ቢ. ብር  ተርፏል ተብሏል። በነገራችን ላይ በቅርቡ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ያነሱትን ተቃውሞ ተከትሎ፣ በዞኑ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ሥራ ላይ ውሎ እንደሆነ የተጠየቁት አስተዳዳሪው፤ በአፈፃፀም ችግር ሳቢያ ሥራ ላይ አለመዋሉን መናገራቸውን እዚሁ ጋዜጣ ላይ አንብቤአለሁ።  በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የወጣቶቹ ተቃውሞው ቢቀጥል እንዴት ሊገርመን ይችላል?  ለመሆኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት (ህዝባዊ ተቃውሞው ከተቀሰቀሰ ወዲህ) የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ በተጨባጭ ምን  ተሰርቷል? (ከጥልቅ ተሃድሶና ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውጭ ማለቴ ነው!) ወደድንም ጠላንም የአገሪቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በስብሰባና በግምገማ ብቻ አይፈቱም፡፡ ተግባራዊ እርምጃ ይጠይቃሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ከተለመደው ውጭ (Out of the Box) ማሰብ መጀመር አለበት!! በጦቢያ ጉዳይ ላይ ሌሎችም ኢትዮጵያውያን (ሁላችንም) እንደሚያገባቸው ማመንም ይገባዋል--ኢህአዴግ ነፍሴ!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!!
ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት ነው!!

Read 8784 times