Print this page
Sunday, 01 April 2018 00:00

የበዓሉ ግርማ ሕይወት እና ሥራዎቹ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(3 votes)

 “መቃብሬ እንደ ሙሴ አይታወቅም”
                
     ቀይ ብስል ብላቴና ለሀገሩ ባዕድ በሆነ ቋንቋ፣ በሚያሳዝን ቅላጼ ተማጽኖውን ያቀርባል፡፡ ሥፍራው የሸገር የንግድ መናገሻ፣ በሰው ጫካ ከተወረረው መርካቶ፣ ከአንድ ህንዳዊ ባለጠጋ ሱቅ ደጃፍ ላይ ነበር። ምስኪኑ ብላቴና በቀዬው ናፍቆት እየተንገበገበ፣ የልጅ ገጽታውን ጣምራ ጣምራ ሆነው በሚወርዱ እምባዎቹ ያወረዛል። ይህ እንደ አልባሌ ፊት የተነሳ ጨቅላ የወደፊቱ ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ሰው በዓሉ ግርማ ነበር፡፡ ነገሩ የተፈጸመው ደግሞ ገና ጉተናው ሳይጠና፣ የትውልድ ቀዬውን ሱጴን ለቆ በነጋዴዎች አማካኝነት ወላጅ አባቱን ለማግኘት መርካቶ በመጣበት ጊዜ ነበር፡፡
ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ፤ የበዓሉ ግርማ ሕይወቱንና ሥራዎቹን በ440 ገጾች፣ የድርሳን ሞገስ አላብሶ፣ በ120 ብር የዋጋ ተመን ለአንባቢያን ካደረሰ ቆየት ብሏል። ደራሲው ይህንን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ለማሰናዳት ብዙ እንደደከመ ዋቢ ካደረጋቸው ተጨባጭ ማስረጃዎች መረዳት ይቻላል፡፡ በእየ ሰርጡ የተሸሸጉትን እውነታዎች ይፋ ለማድረግ ያለፈበት መንገድ ከደራሲነት ይልቅ የምርመራ ጋዜጠኝነት የገነነበት ነበር።
እውነታው  ሲገለጥ
የእንዳለጌታ ቅኝት ከዚህ ቀደም በበዓሉ ግርማ ላይ በተሳሳተ መንገድ ተይዞ የነበረውን እምነት ከሥሩ በመመንገል ይጀምራል፡፡ የበዓሉ ግርማ አሳዳጊ አቶ ግርማ ወልዴ፣ በዓሉን ከአብራካቸው ክፋያዎች ጋር በእኩል ዓይን ተንከባክበው ለማሳደግ የወሰኑበትን ምክንያት ከዚህ ቀደም በየትኛውም ሚዲያ ሰምተነው አናውቅም፡፡ ይህንን የጓዳ ምስጢር የበዓሉ አብሮ አደግ እህት ጽጌ ግርማ እንዲህ ትናዘዛለች፡-
የበዓሉ አመጣጥ እንደዚህ ነው፡፡ በቃ አሁን እንደነገርኩህ፡፡ እናቱ፣ ከሕንድ በመውለዷ ተጽእኖ የተደረገባትና ልጁም ተገልሎ ያደገ ይመስለኛል። ስለዚህ በነጋዴዎች በኩል፣ የአባቱን አድራሻ ሰጠቻቸውና ይዘውት መጡ፡፡ …..አስብ ስንት ጊዜ እንዳለቀሰ። ...መቼም ከሱጴ ሲወጣ እናቱን በእዬዬ ነው የሚሰናበታት፡፡ እዚህ ሲመጣ ደግሞ ተቀባይ አጣ፡፡ ደግነቱ አባቴ ተቀበለው፡፡ እንደዚህ ነው አስተዳደጉ ….በዓሉ ከእኛ ጋር ሲኖር፣ አባቱ ጂምናዳስ ሊያየው አይፈልግም ነበር፡፡ …ይሄ በየጋዜጣው በየሬዲዮኑ የሚነገረው ውሸት ነው፡፡
አቶ ግርማ ወልዴ ከበዓሉ ጋር ምንም አይነት የሥጋ ዝምድና የላቸውም፡፡ ከኢሉአባቦራ ሱጴ ከእናቱ እቅፍ ተነጥሎ በውል ወደ ማያወቀው መሀል ሃገር እንደመጣ አባቱ ጂምናዲስ ፊት ነሳው፤ ይህንን የተመለከቱት የጅምናዲስ ሠራተኛ የነበሩት አቶ ግርማ ወልዴ ሰብዓዊነት ግድ ብሏቸው አፋፍሰው ወደ እልፍኛቸው በመክተት፣ እቅፍ ድግፍ አድርገው፣ ለወግ ማዕረግ ሊያበቁት ችለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዓሉ በአቶ ግርማ ወልዴ ስም ለመጠራት የፈቀደው የዩኒቨርሰቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሳለ ነው፡፡ ፀሐፊው በዳሰሳ ጥናቱ እንደደረሰበት ከሆነ በዓሉ የአያቱን ስም በአቶ ግርማ አባት ወልዴ ፋንታ ኤጄርሶ ብሎ ነው የቀየረው፡፡ ለምን ይህን እንዳደረገ ግምቱን እንደሚከተለው ያኖራል።
እንደ እኔ ግምት፣ የሱጴን ምድር የረገጠና አንድ ሁለት ሽማግሌዎችን ያነጋገረ ሰው፣ ኤጀርሶ የሚለውን ስም መስማቱ አይቀሬ ነውና፣ በዓሉ ስሙን እትብቱ ከተቀበረበት መንደር ጋር ለማስተሳሰር ብሎ የዘየደው መላ ይመስለኛል። ለምን ቢባል፣ ያለ ኤጀርሶ ሱጴ ቦሮ የለችም፡፡ እንደሚታወቀው ሱጴን የቆረቆራት ነገዎ ቦሮ ነው፤ የነገዎ ልጅ ደግሞ ኤጀርሶ፣ የኤጀርሶ ልጆችም አያናና ኃይሌ ናቸው፡፡ እነዚህን ስሞች ሱጴ የተወለደ እና የኖረ ሁሉ ያውቃቸዋል፡፡
ሽቅርቅሩ ጋዜጠኛ
በዓሉ ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር በፍቅር የወደቀው ገና ኮሌጅ እንደበጠሰ ነበር፡፡ በኮሌጅ የተማሪነት ጊዜ ጠንቅቀው የሚያውቁት በሕይወት ያሉ ባልንጀሮቹ በአንድ ድምጽ እንደሚመሰክሩት ከሆነ፣ ለአለባበሱ ጠንቃቃ፣ አርቆ አስተዋይና ላመነበት ነገር እስከ መጨረሻው የሚፋለም ደፋር ወጣት ነበር፡፡ ይህ ደፋር ሰብዕናው በጋዜጠኝነት ሙያ  በተሠማራባቸው ጊዜያት ላይም አልከሰመም፡፡
በዓሉ ከተራ ጋዜጠኝነት እስከ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሥራ አስኪያጅነት ባገለገለባቸው በንጉሱ የሥልጣን ዘመን ብዙ እንግልት ደርሶበታል፡፡ አንዳንዴም በግሳጼ እየታለፈ ባስ ሲልም ቆንጠጥ ያለ እርምጃ እየተወሰደበት በሆድ ይፍጀው እንጉርጉሮ ያዘገመበት የሕይወት አጋጣሚ የተበራከተ ነው፡፡ የመጀመሪያ የጥበብ ሥራውን “ከአድማስ ባሻገር” የጻፈው ከሥራ ገበታው ታግዶ፣ ከመንግሥት ቀለብ እየተሠፈረለት ነበር፡፡
በቄሳሩ የአገዛዝ ወቅት የመነን መጽሔት አዘጋጅ ሆኖ ሳለ በወቅቱ እንደ ድፍረት የሚቆጠር ጀብዶ በመሥራት በቤተ መንግሥት ሰዎች ዘንድ የመወያያ ርዕስ ሆነ፡፡ የመነን መጽሔት የፊት ልባስ በቄሳሩ መንበር ዙሪያ የተሰባሰቡት የንጉሣዊያን ቤተሰብ ብቻ ነበር የሚፈራረቁባት፡፡ በዓሉ ግን በአንድ ዕትም ላይ  የመጽሔቱን ልባስ በአንዲት የፊልም ተዋናይት ገጽታ ሞላው፡፡ ይህም ድርጊት በቤተ መንግሥት ሰዎች ዘንድ እሳት አስነሳ፡፡ እናም በአስቸኳይ ከንጉሡ ፊት እንዲቀርብ ተደርጎ፣ስለ ጉዳዩ ሲጠየቅ እንዲህ ብሎ መለሰ፡-
የመጽሔቱ አንዱ ዓላማ ሙያተኞችን ማበረታት ነው፣ ያቺ በመነን የፊት ልባስ ላይ የወጣችው ሴት    ደግሞ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የፊልም ተዋናይ ናት፤ ድጋፍ ያስፈልጋታል ብዬ በማመኔ ነው፡፡---
ብሎ የንጉሱን ቁጣ ለማለዘብ ሞክሯል፡፡
ስለ ተዋናይቷ ማንነት ግን መጽሐፉ የገለጸው ነገር የለም፡፡ ፀሐፊው ይህንን እና መሰል ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ግርምትን የሚያጭሩ ገጠመኞችን በብዕሩ ለመከተብ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በራፍን ደጋግሞ ለመቆርቆር እንደተገደደ ይናገራል፡፡
በዓሉ ከሥነ ጽሑፍ ችሎታው ባሻገር ሴቶች በፍቅር ጠብ እርግፍ የሚሉለት አማላይ ወንዳወንድ ነበር። የዚያን ዘመን ኮከብ አቀንቃኝ ብዙነሽ በቀለ፤ በፍቅር ከወደቁት መካከል ትጠቀሳለች፡፡ ለዚህም በእማኝነት የቀረበው በ1950ዎቹ የራዲዮ ቴክኒሻን ሆኖ ይሠራ የነበረው ኪሮስ ወልደሚካኤል የተባለው ግለሰብ ነው፡፡
አስብ፣ በዚያ ዘመን፣ አንድ ታዋቂ ድምጻዊ ለአንድ ወጣት፣ ገና ስሙ ላልታወቀ ቆንጆ ጋዜጠኛ፣ በስልክ ዘፈኖቿን ስታንቆረቁለት …እና ዜናውን የሚያነብበት ሰዓት ከደረሰ እኔን በምልክት ጠርቶ የስልኩን እጀታ ይሰጠኛል፡፡ “አንብቤ እስክመጣ አዳምጥ፣ አዳምጥልኝ” ነው ነገሩ፡፡ ሊያነብ ይሄዳል። ዜናውን አንብቦ “ጃንሆይ ወደ ቁልቢ ገብርኤል ሄደው በዓሉን በሰላም አክብረው ተመለሱ”፣ “በልዕልት እገሊት ቀብር ላይ ተገኙ” …ምናምን ብሎ አጠር ፈጠን አድርጎ አንብቦ ሲጨርስ፣ ይመጣና ስልኩን ተቀብሎኝ፣ የእሷን ዘፈን ማዳመጡን ይቀጥላል፡፡
የበዓሉ የጋዜጠኝነት ሙያ ከሥርዓት ለውጥ በኋላ ጠንከር ባለ የፈተና ማዕበል እየተላጋ ቀጠለ። ከበላይ ሹሞቹ የሚሰጠውን ቀጭን ትዕዛዝ ያለ ምንም ማቅማማት እየተቀበሉ ማዝገም ዕጣ ፈንታው የሆነ መሰለ፡፡ ይህንን የሙያ ጭቆና ለማስተንፈስ ዙሪያ ገባውን አማትሮ ከአዕምሮው ብቅ ያለው ለጥበብ የተሰጠው መክሊቱ ብቻ ነበር፡፡ በማያፈናፍን ሥራ ውስጥ ሆኖ፣ ስድስት መጽሐፎችን ለሕትመት ማብቃት ችሏል፡፡
ኦሮማይ
በዓሉ በኦሮማይ የጥበብ ሥራው ደርግ ያሰመረውን ቀይ መስመር አለፈ፡፡ ጥቁር ነብር እያለ የሚያሞግሳቸው የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር አንጀት እንኳን ሊራራለት አልቻለም፡፡ መጽሐፉ ለሕትመት በበቃበት ሳምንታት ውስጥ ከሥራው ገበታ የመታገዱ ነገር ዕውን ሆነ፡፡ ነገሩን ያከፋው ደግሞ በበዓሉ ላይ ጥርስ የሚነክሱት የደርግ ቱባ ሹማምንቶች ከቀን ወደ ቀን ቁጥራቸው እየተበራከተ መሄዱ ነበር፡፡
ፀሐፊው ከገነት አየለ “የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች” መጽሐፍ ደራሲ ጋር ቅርርብ ቢኖረውም ስለ በዓሉ የአሟሟት ሁኔታ ከዚህ ቀደም በሰሚ ሰሚ ከሚነገረው የኮሪደር ወሬ የተለየ ነገር ለመተንፈስ አልደፈረችለትም፡፡ ከዚህ ይልቅ ለሦስተኛ ወገን ሹክ ያለችው ጠቃሚ መረጃ እጁ እንደገባ በሚከተለው መልኩ ይገልጽልናል፡-
“አየህ ፈርታሃለች ማለት ነው፤ ወይም የተጠራጠረችው ነገር አለ፡፡ እንደዛ ባይሆን ኖሮ ጄነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን እነ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ጋ ቀርቦ፣ “በዓሉ እርስዎን ስላንቆለጳጰሰ ነው ወይ በጦር መኮንኖች ላይ የሚዘባበት ልብወለድ ሲጽፍ በቸልታ ያለፉት? በኦሮማይ ሰበብ የጦሩ መንፈስ ታውኳል። ልቡ ተከፍሏል፡፡
ማጉተምተም ይዟል፡፡ እንዴት ከሥራ በማሰናበት ብቻ ይለቀቃል? በዚህም የተነሳ፣ብዙ የጦር መኮንን አቂሞበታል” ብሎ አሳብቋል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው በዓሉ የተያዘው፤ የተጨከነበትም። ይህንን፣ እራሳቸው ጓድ መንግሥቱ  ነግረውኛል ብላ ነግራኛለች፤ ለአንተም ልትነግርህ ይገባ ነበር፡፡”
በዚህም ትዕዛዝ አማካኝነት ፀሐፊው በሰበሰበው መረጃ መሠረት፤ በዓሉ ታስሮ የነበረበት ሞት እንደ ቅንጦት በሚናፈቅበት ቤርሙዳ ትሪያንግል ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን ተገድሎ የተቀበረበት ኹነኛ ሥፍራን በማመላከቱ በኩል አሁንም ጠብ ያለ ነገር ማግኘት አልተቻለም፡፡
በዓሉ ግርማ “ደራሲው” በሚለው የልቦለድ ሥራው “ሲራክ”  በሚባል መሪ ገጸ ባህሪ አማካኝነት “እንደ አብርሃም ቤት የለኝም፣ እንደ ሙሴ መቃብሬ ላይታወቅ” ብሎ የነብይ ቃል ተናግሮ ነበር፡፡ እርግጥ ነው ከበዓሉ መጠሪያ ጋር  ተሽቀዳድሞ ወደ አእምሮ ብቅ የሚለው ነገር የአገዳደሉ ፍንጭ አልባነትና የመቃብሩ ቦታ አለመታወቁ ነው። ምናልባት ይህ መጽሐፍ የበዓሉን ገዳይ ዱካ አነፍንፎ በማግኘቱ፣ አንድ የቤት ሥራ ለጊዜው ያቃለለ ይመስላል፡፡
ስሙ በመጽሐፉ ላይ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ግለሰብ፤ ከገዳዩ ሚስት በቀጥታ ቀዳሁት ያለውን አዲስ ነገር ለፀሐፊው በሚከተለው መልኩ ያጫውተዋል፡-
ማታ ነው፡፡ 2፡30 ኮሎኔል አርጋው እሸቴ የሳሎኑን በር ከፍቶ ገባ፡፡ ሳሎን ተቀምጣ የነበረች ሚስቱ በፊቱ ላይ ያልተለመደ ደስተኝነት አየችበት። ከዚያም፣ የጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪም ዓይነት የሚመስላትን ድፍረት ለብሶ፣ የጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያምን ዓይነት የሚመስላትን እብደት ይዞ፣ በጥቁረትም፣ በእጥረትም የእሳቸውን ዓይነት ገጽታ ወርሶ፣ በድል አድራጊነት ድምጽ አንዳች አስደንጋጭ ነገር ነገራት፡፡ “ያንን! በዓሉ ግርማ የተባለውን ሰው ጨርሼ መጣሁ!” አለ፡፡
ኦሮማይ!

Read 1669 times