Print this page
Sunday, 01 April 2018 00:00

ዶ/ር አብይ በሥራ ባልደረቦቻቸው አንደበት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

 - “ሰዎች እንዲያከብሩትና እንዲከተሉት የማድረግ ልዩ ተሰጥኦ አለው”
         - “ከዶ/ር አብይ ጋር ሰርቶ ከሌላ የሥራ ኃላፊ ጋር መስራት ስቃይ ነው”
         - “ልዩ የንባብ ልምድ ያለው፣ እረፍት የማይወድ ሰው ነው”
            
   
    ነሐሴ 9 ቀን 1968 ዓ.ም በጅማ ዞን አጋሮ ከተማ ውስጥ ተወልደው ያደጉት አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም የተከታተሉት እዛው አጋሮ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡
ዶ/ር አብይ አህመድ፤ በተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ በኃላፊነት ተመድበው በሰሩባቸው ጊዜያት ከፍተኛ የስራ ፍቅር ያላቸው ሰው መሆናቸውን አብረዋቸው የሰሩ ባልደረቦች ይናገራሉ፡፡
እኒህ ዘርፈ ብዙ የሙያ ሰው በሥራው ዓለም  በገቡባቸው የመንግስት ተቋማት ሁሉ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይመሰክራሉ-የሥራ ባልደረቦቻቸው፡፡ ዶክተሩ፣ ሠራተኛውን ለሥራ የማነሳሳት ልዩ ተሰጥኦን የታደሉ የሥራ መሪም እንደነበሩ አብረዋቸው የሰሩ ሁሉ ይናገራሉ፡፡
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ባለሙያው አብርሃም ተስፋዬ ስለ ዶ/ር አብይ የሚያውቀውን እንዲህ ይናገራል፡-
“ከዶክተር አብይ ጋር አብረሽ ከሰራሽ ከሌላ አለቃ ጋር መስራት አትችይም፡፡ በጣም አስገራሚ ተፈጥሮ ያለው ሰው ነው፡፡ አብረውት ስለሚሰሩት ሰዎች ማንነት አብጠርጥሮ ያውቃል፡፡ እሱ በሚመራው ቢሮ ውስጥ አንቺ የስራ ኃላፊም ሁኚ ተራ ሠራተኛ እሱ ግድ የለውም፡፡ በደንብ ያውቅሻል፡፡ ዶ/ር አብይ የሩቅ አለቃሽ ሆኖ፣ ከሱ ጋር የሚያገናኝሽ ሥራ ባይኖርሽም እንኳን ያውቅሻል። በስምሽ ጠርቶ ሲያናግርሽ ትደነግጫለሽ፡፡ በተለይ ትንሽ የማንበብ ፍቅር ካለሽና እሱ ይህን የሚያውቅበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ቢሞት አይረሳሽም፡፡ በሊፍት ወይም ኮሪደር ላይ ድንገት ብትገጣጠሙ ቆም ብሎ ለደቂቃዎች ያናግርሻል፡፡ ሥራ፣ ኑሮ፣ ህይወት… ሁሉን ይጠይቅሻል። ጠይቆሽ ብቻ አያበቃም፡፡ ምላሽሽን በትኩረት ሲሰማ ያስገርምሻል፡፡ ይህ ባህሪይው እጅግ ይገርመኛል፡፡
አንድ በትልቅ     የሃላፊነት ደረጃ ላይ ያለ ሰው ታች ወርዶ፣ ከተራው ሰራተኛ ጋር በዛ ሁኔታ ሲቀራረብ ማየቱ ያልተለመደ ነገር በመሆኑ ትንሽ ግራ ያጋባል። እኔ በመ/ቤቱ ተቀጥሬ ስራ በጀመርኩ ሰሞን የዶ/ር አብይ ባህርይ በጣም ግራ አጋብቶኝ ነበር፡፡ ለቅጥር አመልክቼ ለቃለ መጠይቅ በደረስኩ ጊዜ ቃለ መጠይቁን ካደረጉልኝ ሦስት ሰዎች መካከል አንዱ ዶ/ር አብይ ነበር። በተራና ቀላል ጥያቄዎች ቃለ መጠይቁን የጀመረውም ራሱ ነበር፡፡ ስለዚህ ሰውዬ ቀደም ሲል የማውቀውም የሰማሁትም ነገር ስላአልነበረኝ ነገሩ ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡ ምን እንደምጠላ፣ ምን እንደምወድ፣ ስለ ህይወት ያለኝን አመለካከት፣ ስለ ማንበብ ልምዴ፣ ስለ ወደፊት ራዕዬ፣ ሰለ ማልመው ነገር ሁሉ ጠየቀኝ፡፡ ለጥያቄዎቹ የምሰጠውን ምላሽ የሚሰማበት ሁኔታ በወቅቱ በጣም አስገርሞኝ ነበር፡፡ እውነቱን ለመናገር የተሰጠኝን የቃል ፈተና አልፌ በመ/ቤቱ እቀጠራለሁ የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ ምክንያቱም እኔ ለፈተናው ተዘጋጅቼ የሄድኩት ከስራዬ ጋር በቀጥታ ስለሚገናኙ ጉዳዮች ነበር፡፡ የተጠየኩት ግን በግላዊና ማህበራዊ ህይወቴ ዙሪያ ነበር፡፡ እናም ፍፁም ያላሰብኩትና ያልተዘጋጀሁበት ጉዳይ በመሆኑ በወቅቱ የተናገርኩት ወዲያው የመጣልኝን ሃሣብ ነበር፡፡ ከሦስት ቀናት በኋላ ተደውሎ ስጠራ ማመን አልቻልኩም፡፡ አስፈላጊውን ፎርማሊቲ አጠናቅቄ፣ በቋሚ ሰራተኝነት ተቀጠርኩ” ብሏል፡፡ የIT ባለሙያው፡፡ በመ/ቤቱ ውስጥ በቋሚነት ተቀጥሮ መስራት ከጀመረ በኋላም ከዶክተሩ ጋር በቅርበት የሚያገናኛቸው ስራ ባይኖርም፣ ሁልጊዜም ቅርቡ እንደነበር ይናገራል፡፡ ሥራ በጀመርኩባቸው ሣምንታት እንደ አንግድነቴ ከመ/ቤቱ ሠራተኞች ጋር ምንም አይነት ቅርርብ አልበረኝም፡፡ ከዶክተር አብይ ጋር ግን በተደጋጋሚ እንገናኝ ነበር፡፡
“ትዝ ይለኛል ሥራ የጀመርኩ ቀን ጠዋት 2፡20 ላይ መ/ቤት ስደርስ ዶክተር አብይ ቢሮው ውስጥ ነበር። የሥራ መግቢያ ሰዓት ገና በመሆኑ  እንኳንስ እሱ ተራ ሰራተኛም እንኳን ወደ ሥራ አይገባም ብዬ ነበር ያሰብኩት፤ እሱ ግን በሥራ ላይ ነበር፡፡ በጣም ገረመኝ፡፡ ቢሮዬ ገብቼ ራሴን ከአዲሱ ሥራዬና ከአዳዲሶቹ የሥራ ባልደረቦቼ ጋር በምን መንገድ ማላመድ አለብኝ እያልኩ ሳስብ፣ ዶክተር አብይ ቢሮዬን አንኳኩቶ ገባ፡፡ ደነገጥኩ። ስለ ስራውና ስራው ስለሚጠይቃቸው አንዳንድ ነገሮች ነግሮኝ፣ መልካም የሥራ ጊዜ ይሁንልህ ብሎኝ ሄደ፡፡ ይህ ሁኔታ በቀደምት የሥራ ህይወት ልምዴ አጋጥሞኝ የማያውቅ በመሆኑ በጣም ተገረምኩ፡፡ ሰውዬው ቀደም ሲል ስለ ቢሮ አመራር፣ ስለ ሠራተኛ አያያዝ፣ ስለ እልቅና የነበረኝን አስተሣሠብ በሙሉ ናደብኝ፡፡ እኔም በስሬ ላሉት የበታች ሠራተኞች እንዴት ያለ የሥራ መሪ መሆን እንዳለብኝ እሱ ሆኖ አሣየኝ፡፡ እናም ያቺ ቀን እኔን ምን ያህል እንደቀየረችኝ ለማመን ይከብዳል፡፡
“ለበታች ሠራተኞች የሥራ መሪያቸው እንጂ ማስፈራሪያ አለቃቸው መሆን እንደሌለብኝ የተማርኩት ከአብይ ነው፡፡” በማለት ከዶክተር አብይ አህመድ ጋር በነበረው የሥራ ጊዜ ያሳለፈውን የሥራ ግንኙነት ያስታውሳል፡፡
ዶ/ር አብይ አህመድ የኢንፎርሜሽን እና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ውስጥ ምክትል ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት በኤጀንሲው የኢንስፔክሽን ባለሙያ ሆኖ የሠራው አቶ ብሩክ አንዱአለም ስለ ዶክተሩ የሚናገረው ተመሳሳይ ነው፡፡ “ከዶክተር አብይ ጋር ሰርቻለሁ፤ ከሌላ የሥራ ኃላፊ ጋር መስራት በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ እሱ የአለቃን ትርጉም ይቀይርብሻል፤ የመሪነት ደረጃን ከለመድነው ከፍ ያደርግብሻል፡፡ እኔ እሱ ከሄደ በኋላ መ/ቤቱን ለመልቀቅ የተገደድኩት በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ በሱ ቦታ ላይ የተተኩትን የሥራ ኃላፊዎች፤ ከእሱ ጋር እያወዳደርኩ መስራት አቃተኝ፡፡ ለወራት በጣም ተቸገርኩ፡፡ ሲብስብኝ ቢቀርብኝስ ብዬ መ/ቤቱን ለቅቄ ወጣሁ፡ አሁን በምስራበት ቢሮ እንደገባሁ ከሱ የተጋባብኝን ባህርይ ይዤ ነበር የመጣሁት፡፡ ራስን ዝቅ ማድረግ፣ ለሥራ ጊዜ ያለመስጠትና የህብረት ሥራን ይዥ ነበር የገባሁት፡፡ ግን ለወራት ተሰቃየሁ፡፡ ማንም ሊረዳኝ አልቻለም፤ ወይንም እኔ አልቻልኩበትም፡፡ እሱ ተስጥኦ ያለው ሰው ነው፡፡ ሰዎች እንዲያከብሩትና በቀላሉ እንዲከተሉ ማድረግ ይችላል፡፡ ይህ ግን ለእኔ ከባድ ነገር ነበር፡፡
“ከዶክተር አብይ ጋር ስሠራ ያየሁትና ለእኔ በጣም አስቸጋሪ የሆነብኝ ጉዳይ የሚሰጠኝን ሥራ እሱ በሚፈልገው ፍጥነትና ጥራት ሰርቼ ማስረከብ ነበር፡፡ አንድ ስራ ሲሰጥሽ በምን ያህል ጊዜ እንደምትጨርሺው ይጠይቅሻል፡፡ አንቺ አጠገብሽ ቆሞ “መቼ ትጨርሺዋለሽ?” ሲልሽ ከአጠገብሽ እንዲሄድልሽ ወይም ከሱ ለመገላገል ብለሽ አሊያም የት ያስታውሰዋል ብለሽ ጊዜውን አጠር አድርገሽ ከተናገርሽ አለቀልሽ፡፡ እሱ ቢሞት አይረሣውም፡፡ በቀጠርሺው ሰዓት ስራውን አልቆ ማየት ይፈልጋል፡፡ እኔ በጣም የማልረሳውና ዶክተር አብይን በጣም የሚያስቆጣው ነገር ይሄ ብቻ ነው፡፡ በጊዜ ቀልድ አያውቅም፡፡ በቃልሸ መገኘት እንዳለብሽ ያምናል፡፡
“ዶ/ር አብይ እረፍት የሚባል ነገር አይወድም፡፡ ሌላ ከሱ ጋር በነበረኝ የስራ ዘመን የታዘብኩት ነገር ሰውየው ከፍተኛ የሥራ ፍቅርና ዲሲፒሊን ያለው መሆኑን ነው፡፡ በወታደራዊ ህይወት ውስጥ ማለፉ፣ ለዚህ ጥብቅ የሥራ ፍቅር፣ የአገር ወዳድነት ስሜትና ጥሩ ዲሲፒሊን ያበቃው ይመስለኛል” በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል-አቶ ብሩክ፡፡  

Read 1895 times