Sunday, 01 April 2018 00:00

ሁዳዴ - አካል የሚወገዝበት ወር!!

Written by 
Rate this item
(3 votes)


          “--አካልን በሚጨቁነው በዚህ ሥልጣኔ ውስጥ ይበልጥ ተጎጅዎች ደግሞ በተፈጥሮ ከአካል ጋር ጥብቅ የሆነ ሥነ
ልቦናዊና ስሜታዊ ትስስር ያላቸው ሴቶች ናቸው፡፡ አካልና ስሜትን የሚጨቁን ሥልጣኔ፣ ‹‹የስሜት ምንጭ ናቸው›› ብሎ
የሚፈርጃቸውን ሴቶች የመጨቆኑ ነገር አይቀሬ ነው፡፡ በዚህም ሴቶች ለዘመናት ቂም ይዘው ኖረዋል፡፡--”

           መንፈሳዊነትን በማወደስ ከጥንት ጀምሮ እጅግ በጣም ብዙ ነገር ተብሏል፡፡ እስኪ ዛሬ ደግሞ የመንፈሳዊነት ሌላኛውን ገፅታ እናንሳ፤ መንፈሳዊነት በተሞገሰ ቁጥር ስለሚንኳሰሰው የሰው ልጅ ‹‹አካል›› እናውራ፡፡ በመሆኑም በዚህ ፅሁፍ ውስጥ በባህል፣ በሥነምግባር፣ በኪነ ጥበብ፣ በምሁርነትና በመንፈሳዊነት ስም ‹‹አካል›› ላይ ስለሚደርሰው ዘርፈ ብዙ ጥቃት እናነሳለን።
ይሄንን ፅሁፍ በማዘጋጅበት ወቅት አንድ ልብን በጣም የሚያራራ (በያሬድ ‹‹አራራይ›› ዜማ የተሰራ) መዝሙር ከርቀት ይሰማኛል፡፡ መዝሙሩ ‹‹ከንቱ ነኝ! የከንቱ ከንቱ ነኝ!!›› ይላል፡፡ በዚህ አምስት ቃላትን በያዘ አንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ‹‹ከንቱ›› የሚለው ቃል ሦስት ጊዜ ተደጋግሟል፡፡ በመቶኛ ስናሰላው 60 ፐርሰንት መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ከንቱ›› የሚለው ቃል በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ እንደዚህ ታጭቆ ጥቅም ላይ የዋለው ደግሞ ዓለማዊ ህይወትን ለማንቋሸሽና አካልን (የለበስነውን ሥጋ) ለማውገዝ ነው፡፡
በሰው ልጅ ሥልጣኔ ውስጥ ለዘመናት የሰውን ልጅ መከራና ሸክም ከተሸከሙ እንስሳት ውስጥ ዋነኛዋ አህያ ናት፡፡ የሰው ልጅ የሥራ መሳሪያዎቹን ማሻሻል አቅቶት በደነቆረበት ዘመናት ሁሉ የእሱን ድንቁርና የተሸከመችለት አህያ ናት፡፡ አህያ የሰውን ልጅ ድንቁርናውን ብቻ አይደለም የተሸከመችለት፣ ይልቅስ ከድንቁርናው የሚመነጨውን ጭካኔውን ጭምር እንጂ። ድንቁርና ላይ የተመሰረተ ጭካኔ ደግሞ አረመኔነቱ መኖርን ሁሉ ያስመርራል፡፡ አህያ ይሄንን ሁሉ የሰውን ልጅ ዕዳ ተሸክማ ኖራለች፡፡
ከአህያ በላይ የሰውን ልጅ ጭካኔ የተሸከመ አንድ ነገር አለ - እሱም አካል ነው፤ የለበስነው ሥጋ!! አህያ የሰውን ልጅ ጭካኔ ብትሸከም ሳሯን ግጣ፣ ውሃዋን ጠጥታ ነው፡፡ ከስድብ ጋር ዱላ ቢያርፍባት ዱላው እንጂ ስድቡ አይሰማትም፡፡ አካል ግን የእነዚህ ሁሉ ተጠቂ ነው፡፡ ‹‹አካል የመንፈሳዊ ህይወት ፀር ነው›› እየተባለ በርሃብ እንዲጠወልግ፣ በውሃ ጥም እንዲንገበገብ፣ በፍትወት እንዲቃጠል፣ በስድብ እንዲዋረድ ይደረጋል፤ ‹‹ከንቱ ነህ፣ የከንቱ ከንቱ ነህ!!›› ይባላል፡፡
‹‹ከመንፈሳውያኑ አንዱ…›› ይላሉ ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌም፤ ‹‹ደቂቀ እስጢፋኖስ›› በተባለው መፅሐፋቸው ውስጥ በገፅ 33፣
ከመንፈሳውያኑ አንዱ ስለ ፅድቅ የውሃ ጥም ሲያቃጥለው በፅዋ ቀዝቃዛ ውሃ ይሞላና ከፊቱ ያስቀምጣል፤ አእምሮቱ ይባሱኑ ያቃጥለዋል። “ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?” ቢሉት፣ “ዋጋዬ በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲበዛልኝ በስቃዬ ላይ ስቃይ መጨመሬ ነው፤” አላቸው፡፡

“ነፍሳችን እንድትድን ሥጋችንን እንጣላት”
የመንፈሳዊነት ማግኛ መንገዳችን በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ግብፃዊው አባ እንጦንስ፤ መንፈሳዊ ህይወት የቆመበትን ዋነኛ ምሰሶ ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹ከልብ ስንራብ፣ ስንጠማ፣ ስንራቆት፣ ስናዝን፣ በጣር ላይ ስንሆን ለእግዚአብሔር የተገባን እንሆናለን። እግዚአብሔርን እንድናገኘው ሐዘንን እናስቀድማት፣ ነፍሳችን እንድትድን ሥጋችንን እንጣላት፡፡››
በዚህ ሥልጣኔ ውስጥ ‹‹መንፈሳዊነት ያለ አካላዊ ስቃይ አይገኝም›› የሚል ቅቡል የሆነ አስተሳሰብ አለ፡፡ እውነት ታዋቂ የሚሆነው፣ እሴት የሚገኘው፣ መንፈሳዊነት የሚዳብረው በአካላዊ ስቃይ እንደሆነ ሁሉም ተቀብለውታል፡፡ በዚህም አካላዊ ስቃይ ማህበረሰብንና መንፈሳዊ ተቋማትን የማደራጃ መርህ ሆኗል፡፡ ባህል፣ ሥነምግባርና መንፈሳዊነት አካልን በማሰቃየት የሚገኙ ነገሮች ሆነዋል፡፡  
አካል ላይ የሚወርደው ይህ ጭካኔ፣ ውግዘትና ውርደት ደግሞ በረጅሙ የሁዳዴ ፆም ላይ ጠንከር ይላል። ሁዳዴ ከሊቅ እስከ ደቂቅ አካልን የሚያወግዙበት ወር ነው፡፡ አካልን ለማዋረድና ለማዳከም የቀን መቁጠሪያ ላይ ቀጠሮ ይያዝለታል። ምስኪን አካል!!
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ከዘርዓያዕቆብና ከወልደ ህይወት ሌላ ለአካል ጠበቃ የቆመ አንድም ኢትዮጵያዊ ምሁር እስከ ዛሬ ድረስ አለማግኘታችን ነው። ዘርዓያዕቆብ ለአካል ጠበቃ ሆኖ መገኘቱ ለኢትዮጵያ ፍልስፍና መነሻ ሆኗል፡፡
በጥንት ግሪካውያን ፍልስፍና የተጀመረው እግዜርን ልክ እንደ ሰው አድርጎ የሚያስተምረውን የነሆሜርን ተረት በመቃወም ነው። በኢትዮጵያ ፍልስፍና የተጀመረው ደግሞ በመንፈሳዊነት ስም አካል ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመቃወም ነው። ይሄንንም ጥቃት ለመከላከል በነዘርዓያዕቆብ በኩል የቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ፤ የነፍስንና የሥጋን ቅራኔ መፍታት ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ፍልስፍና ይሄንን ቅራኔ የማስታረቅ ፕሮጀክት ነው።
መንፈሳዊ ተቋማት አካል ላይ ብዙ ዓይነት ጥቃት ቢያደርሱም ለአካል ጥብቅና የሚቆም ግን አንድም ተቋም የለም፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አካልን ከሌላ ወገን ከሚመጣ አካላዊ ጥቃት የሚከላከሉ ተቋማት ቢሆኑም፣ በመንፈሳዊ ተቋማት በኩል ለሚመጣ አካላዊ ጥቃት ግን ጥብቅና አይቆሙም፡፡
ይህ ዓለም የአካል ነው፡፡ እግዚአብሔር የራሱን እስትንፋስ አካል (ሥጋ) ካለበሳት በኋላ (አዳም ከሆነ በኋላ) እንድትኖር የላካት ወደ ምድር ነው። በመሆኑም ምድር የአካል መኖሪያ ነች፡፡ ይበልጥ የሚያሳዝነውም አካል በራሱ መኖሪያ ላይ መገፋቱና መዋረዱ ነው። አካል በራሱ ዓለም ላይ በደስታና በፈንጠዝያ መኖር ሲገባው፣ ሥነ ምግባርንና መንፈሳዊነትን ውለድ እየተባለ እንዲሰቃይ ይደረጋል፡፡
በምድር ላይ ስደተኛው ሥጋ ሳይሆን ነፍስ ነች፡፡ በመሆኑም፣ በምድር ላይ ይበልጥ መብትና ተሰሚነት ሊኖረው የሚገባው አካል እንጂ ነፍስ አይደለችም፡፡ በዚህ ምድር ላይ ነፍስ ነች እንጂ ለአካል መታዘዝ ያለባት፣ አካል አይደለም ለነፍስ መታዘዝ ያለበት፡፡ በመሆኑም፣ ስደተኛውን ከቀደምት ነዋሪው የበለጠ መብትና ክብር የሰጠው የሰው ልጅ አስተሳሰብ ኢ-ፍትሐዊ ነው፡፡ እናም በዚህ ኢ-ፍትሐዊነት ውስጥ ስደተኛዋ ነፍስ፣ አካል የሚሰቃይበትን ሲዖል በምድር ላይ ፈጥራለች፡፡ አካል በራሱ ዓለም ላይ እየተሰቃየ ነው፡፡
ይበልጥ የሚያናድደው ደግሞ የእግዜሩ ነው። ገነትን ለአዳምና ለሄዋን በአካል እንዲኖሩበት ከእግዜር የተሰጣቸው ሉዓላዊ ስፍራቸው ነው። እግዜሩ ገነትን በአካል እንዲኖሩበት ከሰጣቸው በኋላ ተደብቆ መከታተልን ምን አመጣው? እግዜር የሰጣቸውን ስፍራ እንደፈለጉ በአካል እንዲኖሩበት ማድረግ ሲገባው፣ ስደተኛዋን ነፍስ በአካላቸው ላይ ሾሞባቸው ሄደ፡፡ ከዚያም አካላቸውን ሲኖሩ ለቅጣት መጣ፡፡
እናም እግዜሩ ሳይቀር ያለ ስፍራው መጥቶ አካልን በራሱ ዓለም ላይ ይቀጣዋል። ‹‹ደም ይፍሰስሽ››፣ ‹‹ምጥሽ ይብዛ›› የሚለው ሄዋን ላይ የተጣለው አካላዊ ቅጣት፣ እግዜር በራሷ በሔዋን ዓለም ላይ መጥቶ የጣለው ኢ-ፍትሀዊ ቅጣት ነው፡፡ ኢ-ፍትሃዊነቱ አልበቃ ብሎት ጭራሽ እንዲፀፀቱም አደረገ፡፡
ይበልጥ የሚያናድደውም ይሄ ‹‹ፀፀት›› የሚባለው ነገር ነው። እግዜሩ በሉዓላዊ መኖሪያቸው ላይ መጥቶ የራሱን እንደራሴ (ነፍስን) በአካላቸው ላይ መሾሙና አዳምና ሄዋን ላይ ያደረሰው አካላዊ ቅጣት አልበቃ ብሎት፣ ጭራሽ ‹‹ፀፀት›› የሚባል ዘላለማዊ የህሊና ስብራት፣ በሉዓላዊው አካላቸው ላይ አትሞባቸው ሄደ። ሉዓላዊ መብታቸው መደፈሩ ሳያንስ ‹‹ፀፀት›› የሚባል ዘላለማዊ (ከልጅ ወደ ልጅ የሚተላለፍ) የህሊና ስብራት ተሸካሚ ተደረጉ። ምስኪን ሔዋን!!
አካል፣ ይሄንን ስቃዩን የሚያቃልሉለት ምሁራን ሊኖሩት ሲገባ፣ ዓለም እስከ ዛሬ ድረስ ያፈራቻቸው ምሁራን ግን ጭራሽ በተቃራኒው ስቃዩን ደግፈው የሚፅፉትን ነው፡፡ ምሁራዊ ሽፋን እየሰጡ አካልን ከሚያስጠቁ ሰዎች ውስጥ ግንባር ቀደሙ ደግሞ ዚግመንድ ፍሮይድ ነው፡፡ ‹‹ይህ ስልጣኔ አካላዊ ስሜትን በመጨቆን የተገነባ ነው፤ ያለ አካላዊ ጭቆና፣ ሥልጣኔን ማምጣት አይቻልም›› የሚለው የፍሮይድ አስተሳሰብ፤ አካልን ማሰቃየት ለሚፈልጉና ‹‹የከንቱ ከንቱ ነህ›› እያሉ ለሚያዋርዱት ሰዎች ምሁራዊ ከለላ ይሰጣል፡፡
ይህ ዓለም፣ “ስሜታችንን ሳንጨቁን ስልጣኔን ማምጣት አንችልም” (Non-repressive civilization is impossible) በሚል በእንደዚህ አይነት ትእቢት በተወጠረ መርህ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በዚህ ትምክህታዊ መርህ ታዲያ ኒቸ እንደሚለው፡-
‹‹ደስታና ድሎትን የምትጠየፍ ፕላኔት፣ ከስሜቱ የተገነጠለና ከተፈጥሮ ስርዓትም ያፈነገጠ፣ ከማህበራዊ ህይወትም ተገልሎ በብቸኝነት የሚሰቃይ፣ ምድራዊ ሕይወትን አምርሮ የሚጠላ፣ ከስቃይ ውስጥም ደስታንና ተስፋን የሚፈልግ ከንቱ የሆነ ማህበረሰብንና ዓለምን ፈጥረናል፡፡››
እስከ ዛሬ ድረስ ዓለም ካፈራቻቸው ምሁራን ውስጥ ለአካል ጥብቅና በመቆም ፍሬድሪክ ኒቸን የሚያክል የለም፡፡ የኒቸ አብዛኛዎቹ ሥራዎቹ ለአካል ጥብቅና የሚቆሙና አካል ላይ የሚሰነዘረውን ምሁራዊና ማህበረሰባዊ ጥቃት የሚያጋልጡ ናቸው፡፡ ከመንፈሳዊ ተቋማት በኩል አካል ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት ፊት ለፊት የሚታይ ቢሆንም፤ በኪነ ጥበብ፣ በፍልስፍናና በፖለቲካ አማካኝነት የሚሰነዘረው ጥቃት ግን ስውር ነው፡፡ ኒቸን ከታላቁ ጀርመናዊ የሙዚቃ ቀማሪ ዋግነር ጋር ያጣላውም ይሄው ነበር -  ‹‹በሙዚቃ ውስጥ ብሕትውናን እያሞገስክ አካል ላይ ጥቃት ትሰነዝራለህ›› በሚል፡፡
ኒቸ፣ ‹‹በፍልስፍና ውስጥ ተደብቀው አካልን ያንቋሽሻሉ›› በማለት ከሚከሳቸው ምሁራን ውስጥ ግንባር ቀደሞቹ ፕሌቶና ካንት ናቸው፡፡ ካንት ‹‹የዚህ ዓለም ነገር ‹‹በህወስታችን›› መታወቅ አይችልም›› የሚለው አባባሉ ፀረ - አካል አቋሙን አሳብቆበታል፡፡
ፕሌቶ ለአካል ያለው ጥላቻ ደግሞ ጭራሽ የባሰ ነው፡፡ የፕሌቶ መሰረታዊ ችግር የሚነሳው ከዲበ አካላዊ (ሜታፊዚካል) ፍልስፍናው ነው፡፡ ገና ከመነሻው፣ ዓለምን ‹‹መለኮታዊና ቁሳዊ›› ብሎ ለሁለት መክፈል ሲጀምር ነው አካል ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ቆርጦ መነሳቱን ያሳየው። ‹‹በስሜት ህዋሳቶቻችን ተጭበርብረናል››፣ ‹‹ስጋዊ ፍላጎታችንን ከተከተልን አረመኔ እንሆናለን››፣ ‹‹ምድራዊ ሐብትን በሚመኙ ሰዎች ከተመራን እንነቅዛለን›› የሚለው የፕሌቶ ሥነ ዕውቀታዊ (epistemological)፣ ሥነ ምግባራዊና ፖለቲካዊ አስተምህሮው በሙሉ አካልን በማጥላላት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
በመንፈሳዊ ተቋማቱ፣ በኪነ ጥበቡ፣ በፍልስፍናው፣ በፖለቲካው፣ በባህሉ ... በኩል አካል ላይ የሚሰነዘረውን እንደዚህ ዓይነቱን ሁሉን አቀፍ ጥቃት የተመለከተው ኒቸ፤በስተመጨረሻ ‹‹አጠቃላይ ስልጣኔያችን የሰውን ልጅ በማስቃየት የተገነባ (Masochistic civilization) ነው፤›› ወደሚል መደምደሚያ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡
“በማሰቃየት” ብቻ ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ በተፈጥሮው ደስታን ፈላጊ ስለሆነ የሚያሰቃየውን ነገር አሽቀንጥሮ ይጥለው ነበር፡፡ ችግሩ ግን ማሰቃየት ውስጥ “ፈቃደኝነትን” እና “ተስፋን” ማስገባታቸው ነው፡፡
ምንም እንኳ አካል ሰብዓዊ ተሟጋች ባይኖረውም አንድ ሁነኛ ጠበቃ ግን አለው - የህመም ስሜት። አካል ጥቃት ሲደርስበት በደሉን የሚያስተጋባለት በህመም ስሜት በኩል ነው። ህመም አካልን የሚከላከለው ሰውየው ላይ ስቃይ በማምጣት ነው። ሆኖም ግን የመንፈሳዊ ተቋማት ‹‹ስቃይ›› የሚባለውን የአካል ተሟጋች የሚያሽመደምዱበት አንድ ዘዴ ዘየዱ- “መታገስና ተስፋ ማድረግ” የሚል፤ ለሚመጣው ዘላለማዊ ህይወት ሲባል አካላዊ ስቃይን መቻልና መታገስ።
ሰው ስቃይን በማስወገድ አካሉን ነፃ እንዳያወጣ፤በዚህ መልኩ ስቃዩን በተስፋ መረዙበት፤ “ይሄንን ስቃይና መከራ ከታገስክ ማርና ወተት ከምታፈልቀው ሰማያዊ መንግስት ውስጥ የዘላለም ህይወት ይኖርኻል፤ እንደ መላዕክትም እያሸበሸብክና አምላክህን እያመሰገንክ በደስታ ትኖራለህ፤” የሚል ተስፋ ሰጡት፡፡ እናም ለዚህ ሰማያዊ ተስፋ ሲል ራሱን በፈቃደኛነት ማሰቃየትን ተያይዞታል፡፡ ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ያስቸገራቸው ነገር ይሄ ‹‹በፈቃደኝነት ራስን ማሰቃየት›› የሚባለው ነገር ነው::
አካልን በሚጨቁነው በዚህ ሥልጣኔ ውስጥ ይበልጥ ተጎጅዎች ደግሞ በተፈጥሮ ከአካል ጋር  ጥብቅ የሆነ ሥነ ልቦናዊና ስሜታዊ ትስስር ያላቸው ሴቶች ናቸው፡፡ አካልና ስሜትን የሚጨቁን ሥልጣኔ፣ ‹‹የስሜት ምንጭ ናቸው›› ብሎ የሚፈርጃቸውን ሴቶች የመጨቆኑ ነገር አይቀሬ ነው፡፡ በዚህም ሴቶች ለዘመናት ቂም ይዘው ኖረዋል፡፡
ታዲያ ሴቶች በነፃነታቸው ማግስት ያደረጉት ነገር፣ “ያለ አካልና ስሜት ጭቆና ሞራላዊና መንፈሳዊ ዕድገትን ማምጣት አይቻልም፤” የሚለውን የዚህን ሥልጣኔ መርህ፣ ስሜታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ፣ አካላቸውን በማስዋብና ወሲብ ቀስቃሽ ልብሶችን በመልበስ መቃወም ነው፡፡
የፍሮይድ ተንታኝ የሆኑት ኤርክ ፍሮምና ማርኩዘም፤ ሴቶች አካላቸውን የደስታና የውበት ምንጭ አድርጎ በመሳል አዲስ ዓይነት ማህበራዊ አስተሳሰብ እያመጡ እንደሆነ እንዲህ በማለት ያስረዳሉ፣
‹‹አሁን ያለው ማህበረሰብ የሚመራበት መርህ፤ ፍሮይዳዊውን አስተሳሰብ የሚፃረር ነው፡፡ ይሄም አዲስ ማህበረሰብ አካልን የሚያየው የሞራልና የመንፈሳዊ እድገቱ ፀር አድርጎ ሳይሆን እንዲያውም ወደ ደስታና ነፃነት የሚወስድ ሃይል አድርጎ ነው፤ ይሄም የሚያመላክተው እስከ ዛሬ ድረስ በአካልና በስሜት ጭቆና ላይ የተመሰረተው ማህበረሰብ መሰረቱ እየፈራረሰ መሆኑን ነው፡፡››
እናም አዲሱ ማህበረሰብ አካልን የደስታ፣ የውበትና የነፃነት ምንጭ አድርጎ በመመልከቱ ውስጥ ‹‹መንፈሳዊነት ያለ አካላዊ ስቃይ አይገኝም›› የሚለውን የቀድሞውን መንፈሳዊ ሥልጣኔ እየተሰናበተ ነው፡፡ ኦሾም ‹‹ሴቷ ይበልጥ ደስተኛ፣ ውብና ጤነኛ እንድትሆን ይበልጥ አካሏ ላይ ትኩረት ማድረግ አለባት፤ የልስላሴና የአደጋ ተጋላጭነትን የመጨረሻ ከፍታ እየነካች ይበልጥ ስስ፣ ይበልጥ ለስላሳ፣ ይበልጥ ቆንጆ መሆን አለባት!!›› ይላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- (ጸሃፊው ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› መፅሐፍ ደራሲ ነው)

Read 1000 times